- የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ለድርድር እና ለሰላም አማራጮች ቅድሚያ የሚሰጥ፣ እና ያልተቆጠበ ድጋፍ የሚያደርግ ቢሆንም ፣ የሽብር ቡድኑ የድርድር እና የሰላም አማራጮችን የጦርነት ማራመጃ እና የሽብር ማሳለጫ መሳሪያ አድርጎ የሚጠቀመምበትን አግባብ በጽኑ ያወግዛል፡፡
- በዚህ አጋጣሚ ፓርቲያችን አብን መመዘኛውን ለሚያሟሉ የአማራ እና ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውን ወጣቶች በሙሉ ፣ ጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ያወጣውን የምልመላ ጥሪ በመቀበል ሠራዊቱን እንድትቀላቀሉ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡
______
ተስፋፊው ፣ ሽብርተኛው እና ራሱን የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጭ ግንባር (ትሕነግ) እያለ የሚጠራው የዘር ማጥፋት “ፖለቲካ” አራማጁ የወንጀለኞች ቡድን ፣ በጦር ግንባር የደረሰበትን ከፍተኛ ሽንፈት ተከትሎ መስከረም 01 ቀን 2015 ዓ.ም ምሽት ላይ ባወጣው የማደናገሪያ መግለጫ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ለመደራደር ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል፡፡ ይሁንና መግለጫው የተጻፈበት ቀለም ሳይደርቅ በማግስቱ መስከረም 2 ቀን 2015 ዓ.ም ማለዳ ላይ ከሱዳን ድንበር በኩል በምእራብ ጎንደር ዞን መተማ ወረዳ ልዩ ስሙ ቲሃ ተብሎ በሚታወቀው አካባቢ አዲስ ጥቃት ከፍቶ በጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት እና ጥምር ኃይላችን ጥቃቱ የተመከተ ሲሆን ፣ ቡድኑ ከፍተኛ ኪሳራ አስተናግዶ ተመልሷል፡፡ አብን ለድርድር እና ለሰላም አማራጮች ቅድሚያ የሚሰጥ እና ያልተቆጠበ ድጋፍ የሚያደርግ ንቅናቄ ሲሆን አለመግባባቶች ሁሉ በሰላም መፈታት አለባቸው የሚል ጽኑ አቋም አለው:: ከዚህ ጽኑ አቋሙ በመነሳት ጦርነቱ በሰላማዊ መንገድ በድርድር እና በሽምግልና እንዲፈታ ልባዊ ጥረት ለሚያደርጉ አካላት ሁሉ አድናቆቱን እና አክብሮቱን መገለጽ ይወዳል:: ነገር ግን አሸባሪው እና ተስፋፊው የትግራይ ነጻ አውጭ ግንባር የድርድር እና የሰላም አማራጮችን የጦርነት ማራመጃ እና የሽብር ማሳለጫ መሳሪያ የሚያደርግበትን አግባብ በጽኑ ያወግዛል ፣ ይቃወማል ፣ ይታገላል፡፡
የሽብር ቡድኑ በኢትዮጵያ ፍርስራሽ ላይ እና በአማራ ሕዝብ መቃብር ላይ “ታላቋን” ትግራይ ማቆም በሚል ቅዥት የሚባክን ፍሽስታዊ ድርጅት ሲሆን ፣ ሰይጣናዊ ዓላማውን አሳካለሁ በሚል በኢትዮጵያ ሰማይ ስር ያልፈጸመው እና ያላስፈጸመው ወንጀል የለም፡፡ ቡድኑ በጠረጴዛ ዙሪያ በሚደረግ ድርድር እና ሰላማዊ አማራጮች የጥፋት አላማውን ሊያሳካ እንደማይችል ስለሚያውቅ ለአምስት አስር ዓመታት በዘለቀው የውንብድና እና የሽብር ታሪኩ ፣ ድርድር እና ሰላማዊ አማራጮችን ለበጎ የተጠቀመበት አጋጣሚ ኖሮት አያውቅም፡፡ የሽብር ቡድኑ የማደናገሪያ የ”ሰላም ጥሪ” መግለጫውን ከማውጣቱ በፊት ባወጣቸው ተከታታይ መግለጫዎች እና ለሽብር ቡድኑ ሚዲያዎች በሰጣቸው ጋዜጣዊ መግለጫዎች የተኩስ አቁሙ መፍረሱን ፣ የሰላም በር መዘጋቱን እና ፍላጎቱን በኃይል እንደሚያስፈጽም አረጋግጦ መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ የከፈተ ሲሆን ፣ ከሽብር ቡድኑ እና ስፖንሰሮቹ ግምት ውጭ ከፍተኛ ወታደራዊ ሽንፈት በመከናነቡ እና ወታደራዊ መዘናፍ በማስተናገዱ ፣ ሲያራክሰው እና ሲዘባበትበት የነበረውን በአፍሪካ ሕብረት የሚመራውን የሰላም ጥረት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተቀብያለሁ በማለት ጊዜ ለመግዛት እና የዲፕሎማሲ ትርፍ ለማጋበስ ጥረት አድርጓል፡፡
የሽብር ቡድኑ ከማደናገሪያ መግለጫው ጎን ለጎን ጦርነቱን አፋፍሞ የቀጠለ ፣ በተቆጣጠራቸው አካባቢዎች በሚገኙ ንጹሃን ዜጎች ላይ ጭፍጨፋን ጨምሮ ከፍተኛ የሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እና በሲቪልና ሕዝባዊ ተቋማት ላይ ውድመት እና ዝርፊያ እያደረሰ ሲሆን ፣ ይህ መግለጫ በሚጻፍበት ሰዓት እንኳ የተለመደውን የሰው መዓበል አስከትሎ በቆቦ ግንባር ሌላ ዙር ጦርነት ለመክፈት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ የሽብር ቡድኑ ቁሜለታለሁ የሚለውን የጥፋት ዓላማ ለማሳካት ሰብዓዊ እርዳታን እንደ ስንቅ እና ትጥቅ ማሟያ ፣ ድርድር እና የሰላም አማራጮችን እንደ ጊዜ መግዣ እና ማወናበጃ ፣ ክህደት እና ማጭበርበርን እንደ ሁነኛ የትግል ስልት የሚጠቀም የለየለት ፋሽስታዊ ቡድን ነው፡፡ ፓርቲያችን የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ የሀገራችን ኢትዮጵያ እና የመላው ኢትዮጵያውያንን ዘላቂ ሰላም ፣ ጥቅም እና ኅልውና ማረጋገጥ የሚቻለው የሽብር ቡድኑ ኅልውና የሚከስምበትን የጦር ፣ የኮሚኒኬሽን፣ የፖለቲካ እና የዲፕሎማሲ ስልቶች በተሟላ ሁኔታ ስራ ላይ በማዋል ብቻ ነው ብሎ ያምናል፡፡
የሽብር ቡድኑ ስሪት ፣ ባህሪ እና ታሪክ በማናቸውም ሁኔታ ለድርድር እና ሰላማዊ አማራጭ እውነተኛ ዝግጁነት እንዲኖረው የማያስችለው በመሆኑ ፣ ቡድኑ ኅልውናውን እስከቀጠለ ድረስ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ማኅበራዊ እረፍት የማያገኝ እና ቡድኑ ቁሜለታለሁ የሚለውን የትግራይ ሕዝብም ቡድኑ እያደረሰበት ካለው ሰቆቃ መታደግ የሚቻል አይሆንም፡፡ ስለሆነም ፥
፩. መላው ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በሙሉ የሽብር ቡድኑ ባወጣው የማደናገሪያ መግለጫ ሳትዘናጉ ፣ ለጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት እና ለጥምር ጦሩ እያደረጋችሁ ያላችሁትን የማቴርያል እና የሞራል ድጋፍ አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡
፪. የፌዴራሉ መንግስት ከሽብር ቡድኑ ጋር ሰላም ለማውረድ በሚል በሶስተኛ ወገኖች በኩል ወይም በቀጥታ በሚያደርገው ጥረት ፣ የሽብር ቡድኑን ሙሉ በሙሉ ትጥቅ ከማስፈታት ያነሰ ግብ እንዳይዝ እና የሽብር ቡድኑን ኅልውና ለማክሰም የሚያስችሉ ሁሉንም አማራጮች አሟጦ እንዲጠቀም ጥሪያችንን እያስተላለፍን ፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ አባላት ፣ ደጋፊዎች እና በየደረጃው ያለን አመራሮች የሽብር ቡድኑን ኅልውና ለማክሰም ለሚደረግ ማናቸውም ጥረት ሙሉ ድጋፋችንን የምንሰጥ መሆኑን እናስታውቃለን፡፡
፫.. በዚህ አጋጣሚ ፓርቲያችን አማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ፣ መመዘኛውን ለሚያሟሉ መላው የአማራ እና ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውን ወጣቶች በሙሉ ፣ ጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ያወጣውን የምልመላ ጥሪ በመቀበል ሠራዊቱን እንድትቀላቀሉ ጥሪውን ያስተላልፋል፡:
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)
አዲስ አበባ ፣ ሸዋ ፣ ኢትዮጵያ
መስከረም 3 ቀን 2015 ዓ.ም