“ ፕሮ ፖ ጋ ንዳ “ ስትነዳ እንዳትገለበጥ ፤ በ2015 እንኳን  ተጠንቀቅ – ሲና ዘ ሙሴ

September 11, 2022

+ፕሮ ፓ ጋንዳ ። ፕሮፖ ጋንዳ ። ፕሮ ፓጋን ዳ ። ፕሮፖ ጋን ዳ ። ፕሮ ፖ ጋ ንዳ ። ፕሮ … ወዘተ ።  ፕሮ ብቻውን እግር ኮስ ተጫዎች ነው ። ፕሮ ጎረምሳም ነው ። ፕሮ በአንድ  ሙያ የዘለቀ እውቀት ያለው ሰው መጠሪያ ነው ። pro (   Noun pro (plural pros) . A prostitute ሸርሙጣ ማለት ነው ።  እናም ደግሞ ፤   በፀሐፊው  ፣አገርኛ  ትርጉም ፣ ፕሮፖጋንዳ ማለት ፤ ፕሮ ፖጋ ንዳ ማለት ነው ። በትዕዛዝ ፖጋ መንዳት ። እንግዲህ ፖጋ መንዳት ማለት በወጉ ወይም ያለወጉ መበጥረቅ ማለት ነው ። መበጥረቅ ለጌቾ ምላሱ እና ለእንትና እና ለሥ ነው ። ለCNN እና ለመሳሰሉት ደግሞ በሴራ  የሚነዳ  ነው ።

እንግዲህ ፕሮ ማለት ሸርሙጣ ማለት ከሆነ  ። የሚነዳውም በቢዝነስ ነው ማለት ነው ።  አንድ ሰው ለጥቅሙ ሲል ፕሮ ሆኖ ፓ ን ለማጥፋት አቅሙን ሁሉ በመጠቀም ሲያጠቃ ፣ ወይም ወደ ፖ ሲነዳ የሚያሳብቅ ድርጊትም ነው ። በመላሱ ጉልበት እና በሐሰተኛ መረጃዎች ወይም ራሱ በፈበረካቸው ሰቆቃዎች ጠላቴ ያለውን ያለርህራሄ ለመጨፍለቅ ሲንቀሳቀስ ከየነው የ ፕሮ _ ፖ_ጋ _ ንዳ  ትርጉሙ ይገባናል   ።

በጥቂት ሰዎች በሚዘወር የፖለቲካ ፖርቲ ፣ በፈላጭ ቆራጭ ባለሥልጣን ፣ ( በመንግሥት ፣ በቡድን ፣ በግለሰብ ) ፕሮ ፖጋ ንዳ ሲጦጦፍ በየቀኑ ይስተዋላል  ። በአምሥቷ ቀን የ2014  ጳጉሜ እንኳን ፖጋ ሲነዳ አይተናል ። እናም በየቀኑ ” ፖጋ ይነዳል  ! ”

የሚገርመው ግን ፣ ርካሽ ተወዳጅነትን ለማግኘት   ከሚሊዮን በላይ በረንዳ አዳሪ  ( በወደቀ ቤት ፤ በየአሥፓልቱ ጥግ ፤ በአሥፖልት ማቋረጫ ፤ በየመሥጊዱና በየቤተክርስቲያኑ ዙሪያ ) በእርዛት እየኖረ በጣት ለሚቆጠሩ ቤት ተሠራ ተብሎ ፤ በግብዝነት ከበሮ ይደለቃል ። የመላዕክት ሥም ለግለሰቦች ይሰጣል ። የመንግሥተ ሠማይ አጋፋሪ መሆን አለባቸው ይባልልናል    ። ያሳፍራል ። መንግሥት ሥራውን ሥለሰራ ለምን ከበሮ ይመታለታል ። ለምን ፖጋ ንዱ ይባላሉ ። የመንግሥት ጋዜጠኞች ። ቴሌቪዢኖች እንደኢየሱስ የማያስበውን እንደ ፈሪሳውያን ሁሉ የከበሬታ ሥፍራ የሚፈልገውን ሰው ድርጊት እንደ ፅድቅ ድርጊት ያሥጮኻሉ ። የዛሬው መንግሥት በህዝብ ገንዘብ ጥቂት ምንዱባንን እና ባለፀጎችን በብዛት  ሰብስቦ ያበላል ። ይበላል ። የድሮ ነገሥታት ደግሞ አዲስ አበቤን  በግድ እየገረፉ ግብር ያበሉ ነበር ። ፍቅር እሥከመቃብር መፅሐፍ ላይ እውነቱ በደራሲው በሐዲስ ዓለማየሁ ተገልፆለሰ ። የንጉሥን ግብር መብላት ግዴታ ነበር ። ይኽንን እውነት የእኛ ጋዜጠኞች አያወሩም ። ሁሌም መሪን እግዜር አድርገው መሣል ግዴታቸው ሆኗላ ። ለዚህም ነው   “ አይ ኢትዮጵያ ጋዜጠኞችንም ወልዳለች ። “ ሲል በዓሉ ግርማ  በታላቅ ምፀት የተናገረው ። በኦሮማይ መፅሐፉ ።

ለመሆኑ በዛሬው ሥልጡን ዘመን ፣ አንድ መንግሥት የኢትዮጵያ መንግሥት መሆኑንን ተረድቶ አቅም ያለውን ዜጋ በማሥተባበር    ለመላው በረንዳ አዳሪ ያውም ለበዛው ወጣት ዘላቂ ብልፅግና ከልቡ ካልሰራ መንግሥትነቱ ምን ላይ ነው    ? የመንግሥት አጀንዳ ሰው መሆን የለበትም እንዴ ? ድንቡሎ ሣያወጣ ፣  ኪሱ ሣይጎድል ፣  ምድረ ባለሥልጣን በመንግሥት ሀብት  እየተዘባነነ ፤ በሚሊዮን የሚቆጠር ዜጋ በቀን አንዴ እየቀመሰ ኑሮን እየገፋ ፤ ጥቂት የማይባለው ከተሜ ነጋ ጠባ ድንች በዳቦ እና የበቀሎ ቂጣ ፣ በቀን አንዴ እየበላ እያደረ ፤ በግብዝነት በየቴሌቪዥኑ ፅድቅ ያልሆነ ተግባርን በማሣየት በየቤቱ ያለውን ደሃ ማሥገምጀት ተገቢ ነው እንዴ ? የምን አትርሱን ነው ?   መቼ ይሆን  ከዚህ የግብዝነት ገብያ የምንላቀቀው !? መቼ ይሆን ፕሮ ፖ ጋ ንዳውን ሉጋም የምናሥገባለት ?

ድሮ “ በቄላ አሮብናል ። “ ይባል ነበር ። ዘንድሮ ደግሞ በቆሎ በአቅሙ ለደሃ አሮበታል ። ሸምቶ መብላት አልቻለም ። …

ጠ/ሚሩ በአዲስ አበባ ለጥቂት ግለሰቦች ያማረ ቤት ሥለሰሩላቸው የኢትዮጵያ ህዝብ እንደ ህዝብ ምን ተጠቀመ ። እርሳቸው እኮ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒሥቴር እንጂ የአዲስ አበባ ከንቲባ አይደሉም ።   ለብዙሃኑ ምሥኪን ህዝብ  ፤ ለጠቅላላው ዜጋ ማሰብ እና ተግባራዊ እንቅስቃሴ ማድረግ መንግሥታዊ ኃላፊነታቸው ነው ። ወጥ እያወጡ ማሥተናገድ ለፅድቅ ያበቃኛል ብለው ካሰቡ ተሣሥተዋል ። ሥንትና ሥንት ጨላፊ በዚች አገር ላይ እንዳለም በቅጡ ይረዱት ። ይኽቺ አገር የጨላፊ ችግር የለባትም ። ዋናው መደገሱ ላይ እንጂ እጅን ታጥቦ ለመጨለፍማ ማን ያንሳል ????

በጣት የሚቆጠሩ አዲስ አበቤዎች ፣ አጋጣሚው እረድቷቸው ፣ ከወደቀ ቤት ወደ ቪላ ቤት መሸጋገራቸውሥ የኢትዮጵያን መንግሥት የሚያሥሞግሰው ነው እንዴ  ?

ጠቅላዩ ፣ በግል ያደረጉት መልካም ሥራ ከሆነ ፤ ያ ይጠቀስ እና ይሞገሱ ። ከኪሳቸው እንጂ ከመንግሥት ካዝና ( ከከተማ መሥተዳድሩ ወይም ከአካባቢው ካለ ባለሀብት ) ድንቡሎ ሳይቀበሉ የገነቡት እና ለድሆች በግል ሠርተው የሰጡ ከሆነ በእውነቱ ሊመሰገኑ ይገባቸዋል ። ከዚህ ውጪ ከሆነ እና የሌሎች ተሳትፎ በዚህ ጉዳይ ከለበት ግን ቢያንስ እነዚህ ግለሰቦችን መጥቀስ ተገቢ ነው   ። አለበለዚያ ይሄ “ ፕሮ ፖጋ ንዳ “ እንጂ ሌላ ትርጉም አይሰጠውም   ። …

የሚገርመው ፤ በመንግሥት  ሚዲያዎች ዓመት በዓል በመጣ ቁጥር ደግነት ይሰበካል ። ሰው አንድ ቀን በልቶ ይሞት ይመሥል ፣ ለአንድ ቀን ደስታ ለዋለ ገንዘብ ፣ “ በተነ ሠጠ ፅድቅም ሆኖ ተቆጠረለት ። “ ይባልለታል ። 365 ቀናትን በችጋር ና በችግር የሚኖረውን በሚሊዮን የሚቆጠር ኢትዮጵያዊውን ህይወት በዘላቂነት ለመቀየር በፕሮግራም ፣ በተፃፈ ዕቅድ ፣ ዓላማ እና ራዕይ የሚንቀሳቀስ ፣ በፊደራል ደረጃ የሚመራ አንድ ማዕከል ያለው  በህዝብ የሚደገፍ ተቋም መመሥረትን ግን ማንም አያስበውም ። …

በየዓመቱ ጳጉሜን በሥብከት ማሳለፍ ፣ “ በፕሮ ፖጋ ንዳ “ መንከውከው እንጂ ለደሃው ብዙሃን ጠብ ያደረጉለት ነገር የለም ።

የሠላም ቀን ብሎ በሰላማዊ ሠልፍ ፍለጠው ቁረጠው ሲሉ መዋል ። መንገድ በመዝጋት ዜጎችን ማበሳጨት ፣ ሠላማቸውን ማደፍረስ እንጂ ፤ በወጉ በአዳራሽ ተቀምጦ ሥለ ሠላም መወያየት ፤ ሃሳብ መለዋወጥ የለም ።

በበኩሌ ፤“ዛሬም  በደርግ የግዳጅ  የሰልፍ መንገድ ቀበሌዎች መጓዛቸው ያርፋል ወይ ? “ ብሎ ይኽ ፀሓፊ ይጠይቃል ። “ አያርፍም ። “ እንደህነ መልሱ ያውቃል   ። ብልፅግና በዚህ የግዳጅ ሠልፍ እንደ ኢህአዴግ እና እንደ ደርግ የሚቀጥል ከሆነ ገና አምሥት ዓመት ሳይሞላው ጀዘበ እንዴ ?!  ያሰኛል ።

ይህ ፀሐፊ በጥገናዊ ለውጥም ሆነ ለጥቂቶች ሎቶሪ መሠል ዕድል በመሥጠት በአገር ለውጥ ለሚጣ ከቶም እንደማይችል ይገነዘባል ። ለውጥ የሚመጣው “ በተደራጀ ተቋም ፣ በተፃፈ ፕሮግራም ፤ በሚመለከታቸው ምሁራን በወጣ እቅድ እና እቅዱን ለመፈፀም በሚከናወን ተከታታይነት ባለው ተጨባጭ ሥራ ነው  ። “ ብሎም ይመክራል ። ዜጎች ከድህነት ሊወጡ የሚችሉት “ በፕሮ ፖ ጋ ንዳ “ አይደለም ። እናም ሁሉንም ዜጋ ፣ ላብአደሩን ፣ የመንግሥት ሠራተኛውን ፣ ገበሬውን ነጋዴውን ፣ መከላከያውን ፣ ፖርቲዎችን ፤ ወዘተ ። በማሥተባበር የድሃ፣ደሃ ፣ ደሃ የሆኑትን እና በየከተሞቻችን  በየአሥፓልቱ  ማሥታሽ በመሳብ ፣ እየጦዙ ያሉትን ፣ በተጨባጭ በመርዳት ነው ታላቅ አገራዊ ለውጥ ለማምጣት የሚቻለው ። እናም ብልፅግናዎች በ 2015 ዓ/ም በአዲሱ ዓመት ህዝቡን ለማበልፀግ ከልብ መነሳሳት ይጠበቅባችኋል  ። አንዳንዶቻችሁም የራሳችሁ ሥግብግብነት ሊያሳፍራችሁ ይገባል ። ሌብነት ይብቃችሁ ። በህዝብ ፣ በደሃው ሥም ከቀበሌ ጀምሮ ሣንቲም እየሰበሰባችሁ ከፊሉን ኪሳችሁ በመጨመር መብልፀጉ ያሳፍራችሁ ።  ሼም ይግባችሁ ። ባካችሁ አርፉ ። አራዳ ሁኑ ። ከተኛችሁበት ንቁ ። የመንግሥት ባለሥልጣን ያውም ህዝብን ለማገልገል የተመረጠ ባለአደራ  ሆኖ መሥረቅ ፣ በዛሬው ዘመናዊ ጊዜ በቁም መሞት ነው ። እናም በአዲሱ ዓመት “ ፕሮ _ ፖ_ጋ _ ንዳ “  ውን ፤ ቀነሥ  አድርጉና  ወደ ገደለው ግቡ ። ለታይታ ፣ ለሾ ፣ ለፖ ጋ መንዳት ፣ የራሳችሁን መልክ በቴሌቪዢን ለማየት አትጣደፉ ። ካለፉት መንግሥታት ያለማሥተዋል በጊዜ ተማሩ ። የኢትዮጵያን ህዝብ የልብ ኩራት ከእናንተ ይልቅ ነጮች አሣምረው እንደሚያውቁትም ተረዱ ።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Previous Story

አዲሱን አመት ከወለጋ ተፈናቃዮች ጋር – ገለታው ዘለቀ (ደብረ ብርሃን_ኢትዮጵያ)

Next Story

መልካም አዲስ ዓመት

Go toTop