![](https://cdn.statically.io/img/amharic.thehabesha.com/wp-content/uploads/2022/03/1646165721_As-Russias-Ukraine-war-intensifies-some-warn-nuclear-escalation-is.jpg?quality=100&f=auto)
ዓለም ወደ አደገኛው የኑክሌር ጦርነት ፍጥጫ ገብቷል። አሜሪካ በትዕግስት የኖሩትን ሩስያ፤ ቻይና እና አጋሮቿን ቆስቁሰው ጦርነቱ በዩክሬን እንዲፈጠር አድርገዋል። ምዕራቡ ዓለም በእብሪትና በማናለብኝነት የተወጠረ ሆኖ ቆይቷል። የምስራቁ ዓለም የሚመራበትን የፖለቲካ ፍልስፍና “ኮሚኒዝምን” ከምድረ ገጽ ለማጥፋት ያልፈነቀሉት ድንጋይ፤ ያልማሱት ጉድጓድ የለም።
እነርሱ በማን አለብኝነት የሰው ሃገር ወረው ሰላማዊ ሕዝብ ሲጨፈጭፉ፤ አገሮችን ሲአፈርሱ፤ ሲተክሉና ሲበትኑ ኖረዋል። የውሸት ትርክትና ምክንያት ሰጠው ግፍ ሲፈጽሙ እራሳቸውን ሐቀኛ፤ የዓለም ሰላም ጠባቂና ተቆፕርቋሪ መስለው ተኮፍሰዋል። በአፍጋኒስታን፤ ኢራክ፤ ሊቢያ፤ ሶማሊያ፤ ሶሪያ፤ ኢትዮጵያ ላይ የፈፀሙት ግፍ፤ ያደረሱት ሰቆቃ ቃላት አይገልፀውም። እና በምን መስፈርት ነው እነዚህን ሃገራት ያለገደብ ሲአወግዙና ሲሳደቡ የሚውሉት።
ዴሞክራሲ ሰላም ፈጣሪ እንጅ ቀውስ ፈጣሪ አይሆንም እያሉ ሲመፃደቁ ስንቱን ቀውስ እንደፈጠሩት ዓለም ይቁጠረው።አሁን ሩስያ ዩክሬንን ስትወር፤ ቻይና የራሷ ግዛት የሆነችውን ታይዋንን ለማጠቃለል ስታስብ በምዕራቡ ዓለም ጩኸት በርክቷል።
የሌባ ዓይነ ደረቅ መልሶ ልብ ያደርቅ እንዲሉ ሲአሳድዷቸውና ሲበድሏቸው የኖሩትን የሶስተኛው ዓለም ሃገራትን (ኢትዮጵያን ጨምሮ) ሩስያንና ቻይናን አውግዙልኝ እያሉ ተማፅኗቸውን ሲአቀርቡ ይሰማል። ከሚማፀኗች አንዷ ኢትዮጵያ እንደመሆኗ መጠን ኢትዮጵያ የምትወስደውን አቋም እራሷ ታውቃለችና አትልፉ ሊባሉ ይገባል።
አሁን ባለው የሃገራችንና የዓለም ፖለቲካ አንፃር ኢትዮጵያ መደገፍ አለመደገፍ ከሚባል አተካራ ውስጥ መግባት አይጠበቅባትም። በራሳችን እንቅብ ላይ በቂ ችግር ስላለ በዚያ ላይ ትኩረት ሰጠን እንስራ። ደግሞስ ኢትዮጵያ ድጋፏን ሰጠች አልሰጠች በዩክሬን ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ስለማይቀይረው በጥንቃቄ መጓዝ ያስፈልጋል። በለፈለፉ ይጠፉን እያስታወስን አብረን ዝም እንበል። አንዳንዴ ዝምታም ወርቅ ነውና አብረን ዝም እንበል (in politics abstention is wisdom ).
ሰማነህ ጀመረ
ኦታዋ፤ ካናዳ
የካቲት 23 ቀን 2014