ጠቅላይ ሚንስትሩ እና ውሸቶቻቸው በፖለቲካ መነፅር! – ወንድይራድ ኃይለገብርኤል

March 3, 2022

በሊብራል ዲሞክራሲ የፖለቲካ መስተጋብር ውስጥ ውሸት ለመንግስታዊ ስራ ስኬታማነት ቁልፍ መሳሪያ ነው (a useful tool of Statecraft). በአንፃሩ በአቢዮታዊ ዲሞክራሲ መንግስታዊ አገዛዝ ውስጥ ጉልበት እና ሀይል እንጅ ውሸት ለፖለቲካ ግብዓትነት እምብዛም አያገለግልም።

አቢዮተኞቹ እንደሚገድሉህ እየነገሩህ ይገድሉሀል። እረፍት እንደሚነሱህ እየነገሩህ እረፍት ይነሱሀል። ይህንን ለመረዳት በህወሓት የአገዛዝ ዘመን በአማራ ህዝብ ላይ የደረሰውን ግልጽ ጥፋት ማሰብ በቂ ነው። ህወሓት አማራን የጨፈጨፈው ማንፌስቶ ቀርፆ በግልፅ እየተናገረ ነው። ስልጣን ላይ በነበረበት ጊዜ ያደረሰው በደል አላረካው ብሎ ዛሬም ቢሆን “የቀረ ሂሳብ አለ” በማለት የሚፎክረው በግልጽ ነው። ተመልሶ መጥቶም የቻለውን ያክል “አወራርዶ” ሄዷል። ክፉን በሩቁ እንጅ እንደገና ከመጣ ደግሞ ሊሆን የሚችለውን ከአዶናይ በቀር አዋቂ የለም።

እራሳቸውን እንደ ሊብራል የፖለቲካ ደቀመዝሙር በሚቆጥሩት በጠቅላይ ሚንስትር አብይ ላይ ብዙዎቻችን “ይዋሻሉ — ዛሬ የተናገሩትን ነገ አይደግሙትም” የተሰኙ ትችቶችን ስንሰነዝር ይደመጣል ይነበባልም ጭምር። እውነት ነው እንዲህ ብንታዘብ ትክክል ልንሆን የምንችልበት አጋጣሚ ሰፊ ነው። በተለይ በተለይ ፖለቲካን በሓይማኖታዊ ስነልቦና (religiopolitical) ለሚያስተናግደው ለእኛ ማህበረሰብ የጠቅላይ ሚንስትሩ ወጥነት የሚጎድላቸው ንግግሮች ቢያስበረግገው ሊፈረድ አይገባም። “አትዋሽ” ለሙሴ ከተሰጡት ክርስቲያናዊ የተፈጥሮ/ግብረገብ ህጎች (Natural Law) ቀዳሚው መሆኑን አንስተውም። ጠ/ሚንስትሩ በዋሹ ቁጥር የተፈጥሮ ህግ ተደረመሰ ብለው የሚያስቡት የዩቲዩብ ዲያቆናት እና ቀሳውስት ሃያሲዎቻችን ሸህሬታቸው ከፍ ያለ ነው።

ከፍ ብለን እንደ ጠቆምነው ዘመናዊው ፖለቲካ በባህሪው ውሽትን እንደ ቀዳሚ ግብዓት ይጠቀማል። መሪዎች ይዋሻሉ። ካልዋሹ ፖለቲካቸው ይበላሻል። ዋናው ነገር መዋሸታቸው ሳይሆን አወሻሸታቸው ነው። ታዲያ ለትችት እና ለነቀፌታ ከመነሳታችን በፊት መሪዎች የሚዋሿቸው ውሸቶች የግል ፖለቲካዊ ስብዕናቸውን ለመገንባት (selfish/dirty lies)? ወይንስ ብሔራዊ ጥቅሞችን ለማረጋገጥ (strategic/noble lies) ናቸው? ብሎ መመርመር አስፈላጊ ጉዳይ ነው። ከዚሁ ጋር አያይዞም የወሸቶቹን ወጥነት (consistency) ከጊዜ እና ሁኔታዎች ጋር በማዛመድ መፈተሽ ጠቃሚ ይሆናል። እንዲህ ከመረመሩ በኋላ የመሪዎችን ወሸት በፈርጅ እና በአውድ መተቸት ቢቻል መልካም ነው።

የጠቅላይ ሚንስትሩን ሁለት ወሸቶች በምሳሌነት እንመልከት!

1፡ “የፅሞና ጌዜ ለመስጠት አስበን ነው ከመቀሌ የወጣነው”

ከፍ ብሎ የተጠቀሰው ንግግራቸው በባህሪው ስትራቴጅክ ውሸት ሆኖ ሲያበቃ የፈጠራ ድርሰቱን ተከትለው በሌሎች ባለስልጣኖችና በእርሳቸውም ጭምር የተነገሩት ተከታታይ ተጣራሽ/ተላታሚ (inconsistent/conflicting) ንግግሮች የውሸቱን ስትራቴጂካዊነት አበላሽተውታል።

ሌላ ሌላውን ትተን አሁን በቅርብ ጠ/ሚንስትሩ ለእንደራሴዎቹ ምክርቤት ያደረጉትን ንግግር ብናስታውስ “ለትግራይ መልሶ መቋቋም ያወጣነውን 100 ቢሊዮን ብር የመከላከያ ሀይላችን አጠናክረንበት ቢሆን ኖሮ ሰኔ ላይ የደረሰብን ጉዳት አይደርስብንም ነበር” በማለት ሲናገሩ ሰምተናቸዋል። “ባልጠበቅነው መንገድ ተደብድበን ወጥተናል ነው” የጭብጡ ብልት። ይሄ ደግሞ “የፅሞና ጊዜ ለመስጠት አስበን ትተንላቸው ወጣን” የሚለውን የቀደመ ስትራቴጅክ ውሸታቸውን በራሳቸው አንደበት አፈር ደሜ አብልቶ ወደ ቆሻሻ ውሸትነት ለውጦታል። ጠ/ሚንስትሩ ሁነኛ የሁኔታ/የውሸት አማካሪ (lie advisor) ያላቸው አይመስለኝም። ለዚህም ይመስለኛል በተደጋጋሚ ጊዜ ሳይገደዱ (unforcedly) ትናትና የዋሹትን ስትራቴጅክ ወሸት ዛሬ ላይ ወደ ቆሻሻ ውሸትነት የቀየሩት። ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ፤ ጄነራል ባጫ ደበሌና ጀነራል አበባው ታደሰም በተለያዩ ጊዚያቶች ባደረጓቸው ንግግሮች የጠ/ሚንስትሩን የቀደመ ስትራቴጅክ ውሸት እራቁቱን እንዳስቀሩት ታዝበናል።

2፡ “ባለፉት መቶ አመታት ውስጥ ውስጥ ያልነበረንን የመከላከያ ሀይል እየገነባን ነው። ጁንታዋን መማሪያ ነው የምናደርጋት”

አውድና ጊዜን እንደቀዳሚ መስፈርት ተጠቅመን ስንመዝነው ይሄኛውም “ስትራቴጅክ ውሸት ነበር” ብሎ ማለት ይቻል ይሆናል ብየ አስባለሁ። መሬት ላይ በታዩ ድርጊቶች ሊታገዝ ባለመቻሉ ግን የፈጠራ ድርሰቱን ሰልፊሽ ቀደዳ አድርጎታል። ጠ/ሚንስትሩ ይህንን በተናገሩ በጥቂት ወራቶች ውስጥ “መማሪያ” የተባለው የጁንታ ሀይል ደብረብርሀን ተጠግቶ እንደ ነበር የምናስታወሰው ጉዳይ ነው። ቢሆንም ግን እዚህ ላይ የኢትዮጵያን ደህንነት እና ህልውና ከልብ የሚመኙ ወገኖች የህወሓትን ተመልሶ መምጣት የሚመኙ ካልሆነ በቀር ጉዳዩን ያላግባብ ማጦዝ አልነበረባቸውም። የጠ/ሚንስትሩን ድርሰት ከብሔራዊ ህልውና እና ጥቅሞች ጋር አያይዘው መመልከት ነበረባቸው።

እንደ ማንኛውም የሀገር መሪ ጠቅላይ ሚንስትሩ ሀገረ እስከመሩ ድረስ ወደፊትም አጠናክረው መዋሸታቸው አይቀርም። ካልዋሹ ሀገርን ባግባቡ ሊመሩ አይችሉም። ቢሆንም ግን እያሰቡ እና በጥናት ላይ ተመስርተው ቢዋሹ በጊዜና በሁኔታ እየተጠለፉ መጫዎቻ ከመሆን ይድናሉ። “በሻሻ አድርገናታል” አይነት ነገር ውሸቶችም ለተቀመጡበት ወንበር አይመጥኑም። ትናትና መቀሌን “በሻሻ አድርገናታል” ብለውነ ሲያበቁ ዛሬ ደግሞ “ሆን ብለው በሻሻ” ላደረጓት መቀሌ የእንደራሴዎቹን ምክርቤት ተገቢ የሆነ ሀዘኔታ አላሳየም በማለት ሲወቅሱት ሰምተናል። ይህ አይነቱ አወሻሽ ጠ/ሚንስትሩን አመኔታ ያሳጣቸዋል። አሳጥቷቸዋልም።

ጠ/ሚንስትሩ ለህዝባቸው ሰላምና ለሀገራቸው ህልውና መረጋገጥ አስተዋፅዖ ሊያደረጉ የሚችሉ ስትራቴጅክ ውሸቶችን እየመረጡ እንዲዋሹ ይጠበቃል። ሉቫ የሆኑ የውሸት አማካሪዎች ቢያገኙ ደግሞ የበለጠ ጭዋ ውሸታም ይሆናሉ። ለምርጥ የአወሻሽ አማካሪነት የሚመጥኑ በርካታ ኤክስፐርቶች ባሉበት ሀገር ጠ/ሚንስትሩ አድሮ የማይገኝ ውሸት እየተናገሩ እራሳቸውን ማስገመት የለባቸውም። ክቡርነታቸው ቆሻሻ ውሸቶችን ሊጠየፉ ግድ ነው።

ለምሳሌ ያክል “በጦርነት ውስጥ ብንሆንም ኢኮኖሚያችን ተመንድጓል” ቆሻሻ ውሸት ነው። በህዝቦች ረሀብና ስቃይ አጥብቆ የቀለደ ሰልፊሽ ውሸት። እንዲህ አይነት ቆሻሻ ወሸቶች የጠ/ሚንስትሩን የአዕምሮ ጤንነት ሳይቀር የጥያቄ ምልክት ውስጥ እንዲገባ የሚያደርጉ አሳፋሪ ውሸቶች ናቸው።

በመጨረሻም ከጠቅላይ ሚንስትሩ መልካም ምግባሮች አንዱን አስታውሰን የዛሬውን ፋይል እንዝጋ። “በህይወት እያለሁ ኢትዮጵያ አትፈርስም። ከፈረሰችም እኔ ከፈረስኩ በኋላ ነው” — ጠ/ሚንስትሩ ይህንን ሲናገሩ “ከተለመደው ውሸታቸው ተከታዩ ድርሰት ነው” ብለው ያሰቡ ብዙሀን ነበሩ። “የማርቆስ መንበር አይሰደድም” ከተሰኘው የተለመደ እሳቤታቸው ላይ እየተንደረደሩ ዲያቆናቱ እና ቀሳውስቱ ሀያሲያን በመጨረሻው ሰዓት ጠ/ሚንስትሩ ሀገር ጥለው ሊሄዱ እንደሚችሉ ቅድመ ውንጀላ ጀምረው እንደ ነበር እናስታውሳለን። እንዲያ ቢተነበይም ቅሉ የመጨረሻው ሰዓት መጨረሻ ደርሶ ጠቅላይ ሚንስትሩ ለቃላቸው ታምነው ወደ ግንባር መክተታቸውን ተመልክተናል። ይህንን በማድረጋቸው ስማቸውን ከፍ ካለው የታሪክ መዝገብ ላይ ማስቀመጥ ችለዋል። ይህንን ማድረግ በመቻላቸው ሀገራቸውን እና ህዝባቸውን ከውርደት አድነዋል። የጠ/ሚንስትሩን ወደ ግንባር መዝመት ተከትሎ የታየው ህዝባዊ መነሳሳት እና አንድነት ታሪካዊ ነበር። እውነታውን መካድ አንችልም። ቢሆንም ግን ተገኘ የተባለውን “ጊዚያዊ ድል” ተከትሎ አገዛዙ የፈፀማቸው ፖለቲካዊ ህፀፆች እና ተከታታይ ቆሻሻ ወሸቶች ሀገራዊ ህብረቱን አፈር አስልሰውታል። “እኔም ስሰማ ደንግጫለሁ” አይነት ሰልፊሽ ውሸቶች በህዝብ እና በመንግስት መካከል ከፍ ያለ ውጥረት አስከትለዋል።

ለጊዜው ጠ/ሚንስትሩ ጥሩ ጥሩ ስትራቴጅክ ውሸቶችን እያመጡ በህዝብ እና በመንግስት መካክል የተፈጠረውን ውጥረት ያረግቡታል ብለን ደግ ደጉን እናስብ።

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Previous Story

በስጋትና በግራ መጋባት መካከል የሚገኙት ኢትዮጵያዉያን በዩክሬይን

addis ababa zehabesha
Next Story

አዲስ አበቤ ሆይ! “ዝምታና ፍርሃት”  እስከ መቼ? – ፊልጶስ

Go toTop