አንድነት ፓርቲ የደቡብ አፍሪካ ኢምባሲ ተወካዩች በነገው መርሐ ግብር እንደሚገኙለት አስታወቀ

December 11, 2013

በዳዊት ሰለሞን
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ነገ ሐሙስ ቀበና መድሃኒዓለም ቤተ ክርስቲያን ፊት ለፊት በሚገኘው ዋና ጽህፈት ቤቱ የኔልሰን ማንዴላን ህልፈተ ህይወት ምክንያት በማድረግና በእስር ላይ የሚገኙትን የፓርቲውን አመራሮች ጨምሮ በአገራቸው መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን በሰላማዊ መንገድ በመታገላቸው የተነሳ ለእስር የተዳረጉ ኢትዮጵያዊያንን ያስታውሳል፡፡

የጸረ አፓርታይድ ታጋዩ ኔልሰን ማንዴላ ለአፍሪካዊያን የፍቅር፣የእርቅና ሁሉን የማሳተፍ ፖለቲካ መምህር ነው ያለው ፓርቲው በዕለቱ በሚያደርገው የሻማ ማብራት ስነ ስርዓት አዲስ አበባ የሚገኘው የደቡብ አፍሪካ ኢምባሲ ተወካዩን በመላክ የስነ ስርዓቱ ተካፋይ እንዲሆን በደብዳቤ ጠይቆ ቀና ምላሽ አግኝቷል፡፡

በኢምባሲው በተዘጋጀው የሐዘን መግለጫ ሰነድ ላይ ፊርማቸውን ያኖሩት የአንድነት ሊቀመንበር ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳና ዋና ጸሐፊው አቶ አስራት ጣሴ አምባሳደሩን በማግኘት ባነጋገሩበት ወቅት በነገው መርሐ ግብር እንዲሳተፍ ተወካይ እንደሚልኩ እንደገለጹላቸው ለፍኖተ ነጻነት ተናግረዋል፡፡

ፓርቲው በኔልሰን ማንዴላ ህልፈተ ህይወት ሐዘን የተሰማቸው ኢትዮጵያዊያን በመርሐ ግበሩ ላይ በመገኘት በተዘጋጀው የሀዘን መግለጫ ሰነድ ላይ በመፈረም ለደቡብ አፍሪካዊያን አጋርነታቸውን እንዲያሳዩ ጋብዟል፡፡ዜጎች ፊርማቸውን የሚያኖሩበት ሰነድም ለደቡብ አፈሪካ ኢምባሲ ተወካዩች እንደሚሰጥ ተገልጻል፡፡

 

Previous Story

የብሄር እኩልነት!

Next Story

ሰበር ዜና: ኢትዪጲያዊ ሙስሊም የችሎት ውሎ (ቢቢኤን ልዩ ፕሮግራም)

Go toTop