ከዳዊት በጋሻው
ብራዚል 20ኛውን የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ልታዘጋጅ ስምንት ወራት ቢቀሯትም የሚመ ጡባትን እንግዶች በዓለም አቀፉ እግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ማህበር(ፊፋ) አማካኝነት እየለየች ትገኛለች። እስካሁንም ሦስት የአፍሪካን አገራት ጨምሮ ሌሎች የአውሮፓ፣ የደቡብ አሜሪካ፣ የሰሜንና ካሪቢያን አገሮችን ፊፋ ለይቶላታል።
ኃይል የተቀላቀለበት ጨዋታ የሚበዛባት አፍሪካ ለ2014ቱ የብራዚል ድግስ ሦስት የምዕራብ አፍሪካ አገራትን ማሳለፏን አሳውቃለች። በአንጻሩ የእግር ኳስ ኃያላኑ አልጄሪያ፣ ሞሮኮና ቱኒዚያ ለዓለም ዋንጫ ወደ ብራዚል አይጓዙም።
ግብጽም ብትሆን በአክራ ኩማሲ ስታዲየም ላይ በጋና 6ለ1 ተሸንፋለች። ይህን ግማሽ ደርዘን ግብ ቀልብሳ ወደ ብራዚል የማለፏ ነገር አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል። ምስራቅ አፍሪካም ከዋሊያዎቹ የካላባር ሽንፈት በኋላ ተወካይ እንደሌለው ተመልክቷል።
አፍሪካ በአምስት አገራት ብትወከልም ብራዚልና የዓለም ህዝብ ግን ለመጀመሪያ ጊዜ አዳዲስ ፊቶችን ለመመልከት ሳይታደል ቀርቷል። በአፍሪካ ዞን በተደረጉት የማጣሪያ ጨዋታዎች ላይ ድንቅ እንቅስቃሴ ያሳዩትን ዋሊያ አይቤክሶችን ብራዚልና ዓለም አለማየታቸው እግር ኳስ ፍትሐዊ አለመሆኑን ያመለክታል።
በእርግጥ የዓለም ህዝብ በብራዚል፣ በሆላንድ፣ ስፔን፣ ጀርመንና የመሳሰሉት አገራት በሚያደርጉት ፉክክር ቢዝናናም ብዙ ያልተባለላቸውና እምብዛም በዓለም ህዝብ ዘንድ ያልታዩት ዋሊያዎቹ የማራካኛና የሳኦፖሎ እንዲሁም የሪዮ ዲጄኔሪዮና ብራዚሊያ ስታዲየም ድምቀቶች ሳይሆኑ መቅረታቸው የሚጎዳው ኢትዮጵያውያንን ብቻ ላይሆን ይችላል።
ምንም እንኳን በአውሮፓና እስያ እንዲሁም በደቡብ አሜሪካ ምርጥ ጨዋታ የሚጫወቱ አገራት ቢኖሩም በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ከድንቅ ጨዋታ በተጨማሪ በማራኪው ድጋፋቸው የሚታወቁትን ኢትዮጵያውያንን ማጣቷ ብራዚልን ዕድለኛ አያደርጋትም። ምክንያቱም ኳስን ይዞ መጫወት ብዙ ባልተለመደባት አፍሪካ ዋሊያዎቹ ምርጥ ጨዋታ በመጫወት ምርጦች መሆናቸውንና የአገሪቱን የኳስ ታሪክ በወርቅ ቀለም ያስጻፉ ፈርጦች መሆናቸውን ካለፈው ዓመት ጥቅምት ጀምሮ አስመስክረዋል።
ከእዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ወደ ውጭ አገራት ሄዶ ሲጫወት የሚገባበትን የግብ መጠን መቀነስ ላይ ያተኩር የነበረው ዕቅድ አሁን ማሸነፍ ወደ ሚለው ከመቀየሩም በላይ በተጨባጭ እየተተገበረ ነው።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአዲስ አበባና በሌሎች አገራት ተጫውቶ በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ላይ 13 ነጥቦችን በመሰብሰብና 10 ግቦችን በማግባት የምድብ መሪ ነበረ።
ቡድኑ በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ደቡብ አፍሪካን በሜዳው 2ለ1 ያሸነፈ ሲሆን፣ ቦትስዋናንና መካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክን በሜዳቸውና ከሜዳቸው ውጪ ማሸነፉ ይታወሳል፡፡ የቡድኑ ጥንካሬ ግብ አስቆጥሮ ጨዋታን ማሸነፍ ብቻ ሳይሆን ማራኪ ኳስን ለተመልካች በመቸር ነው።
ካይሮ በወጣው ዕጣ ከናይጄሪያ ጋር የደረሰው ቡድኑ አዲስ አበባ ላይ ናይጄሪያን ፈትኗል። ከመፈተኑም በላይ ለግብ የሚሆኑ ሙከራዎችን በመሞከርና ጨዋታውን በመቆጣጠር ለዓለም ህዝብ ምርጥ እግር ኳስን አሳይቷል።
በ24ኛው ደቂቃ የተሻረችው የሳላዲን ግብም የዳኝነት ስህተት የዓለም ህዝብና ብራዚል ዋሊያዎቹን እንዳያይ ካደረጉት ክስተቶች መካከል ዋነኛው ነው።
የሱፐር ስፖርት እግር ኳስ ተንታኞች ናይጄሪያና ኢትዮጵያ ያደረጉትን ጨዋታ በተመለከተ ዋሊያዎቹን «የሜዳ ላይ ጀግኖች፣ የአፍሪካ ባርሴሎናዎች» በማለት ያሞካሿቸው ሲሆን፤ ደቡብ አፍሪካ ላይ በተዘጋጀው 29ኛው አፍሪካ ዋንጫ ላይ ዋሊያዎቹን « ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ዋንጫ ሦስት አስርት ዓመታት መራቋ የዓለም ህዝብ ምርጥ እግር ኳስን እንዳይመለከት አድርጎታል» በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ከላይ የተሰጡት የተንታኞች አስተያየት የሚያመለክተው ቡድኑ በእግር ኳስ ክህሎቱና አጨዋወቱ አስደናቂ መሆኑንና ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ቢሳተፍ ምን ያህል የውድድሮች ድምቀት እንደሚሆን ነው።
ለማንኛውም ዋሊያዎቹ ወደ ብራዚል ሊያደርጉት የነበረው ጉዞ ካላባር ላይ ተገትታል። ናይጄሪያና ካፍም ያሰቡት ተሳክቶላቸዋል። ዋሊያዎቹም ፊታቸውን ወደ ምስራቅ መካከለኛው አፍሪካ ዋንጫ፣ ወደ ቻን፣ ወደ 2015ቱ የአፍሪካ ዋንጫና ወደ 2018ቱ የሩሲያ ዓለም ዋንጫ ማዞር ግድ ብሏቸዋል።
በእዚህ መሰረትም ከአሥር ቀናት በኋላ ናይሮቢ ላይ በሚካሄደው የምስራቅ መካከለኛው አፍሪካ ዋንጫ ላይ ዋሊያዎቹ ይሳተፋሉ። ዝግጅታቸውንም በቅርቡ ይጀምራሉ።
እዚህ ላይ አንድ ሁለት ነጥቦችን መጠቃቀስ አስፈላጊ ይሆናል። የመጀመሪያው ነጥብ ያንሠራራው የአገሪቱ እግር ኳስ ቀጣይነት እንዲኖረው የማስቻል ሥራዎች መሥራት ላይ የሚያተኩር ነው። ለእዚህ ደግሞ መሠረት የሚሆኑ ዝግጅቶች ማድረግ ያስፈልጋል። ከ17 ዓመት በታችና ከ20 ዓመት በታች የሚባሉ ቡድኖች ሊኖሩን ይገባል። ምክንያቱም እነ ደጉን፣ አዳነን፣ ሳላዲንንና ሌሎችን የሚተኩ ተጫዋቾች ያስፈልጉናል።
ሌላው ነጥብ ደግሞ ሕዝባዊ መሠረቱን ማጠናከር የሚገባ መሆኑን መገንዘብ ነው። እግር ኳሱን ለማሳደግ ባለሀብቱ፣ ማኅበራቱ፣ ተቋማቱ ወዘተ… ክለቦችን በማቋቋም በገንዘብ፣ በቁሳቁስና በዕውቀት በመርዳት የሚጠበቅባቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል።