ለ18 አመታት ያህል በትግራይ ክልል ታስሮ የቆየው ካሳሁን ሲሳይ ‹‹በትግራይ የሚታሰር አማራ የከፋ ግፍ ይፈፀምበታል›› አለ

November 11, 2018

በጎንደር ወልቃይት ተወለልዶ ያደገው ሲሳይ በአዲስ አበባ ከሚታተመው ጊዮን ከተባለው መፅሄት ጋር ባደረገው ቃለምልልስ የታሰረው መስከረም 11 ቀን 1986 እንደነበር አስረድቷል፡፡ መጀመሪያ በትግራይ ሽሬ ከተማ ከጓደኛው ጋር መታሰሩን የገለፀው ሲሳይ ጓደኛው ከአምስት አመት እስር በኋላ እዛው እስር ቤት መሞቱን ገልፆዋል፡፡ ስለጓደኛው አሟሟት ተጠይቆም፡-
‹‹ታሞ ቢሞትም ለህመሙ መንስኤ የሆነ መድሃኒት ሰጥተው የገደሉት ግን ወያኔዎች ናቸው፡፡ በመድሃኒት ገድለውታል ብዬ ነው የማምነው›› ብሏል፡፡ በእስር ቤት የነበረውን ሁኔታ ሲያስረዳ ደግሞ ‹በጣም ከባድና ስቃይ የበዛበት ነው ማለት ይቻላል፡፡ የሻይ መጠጫ በሆች ትንሽ የፕላስቲክ ኩባያ እየተለካ የማሽላ ገንፎ ነበር የሚሰጠን፡፡ መኝታችን በእስኪሪብቶ ተለክቶ በተሰመረልን ጠባብ ክፍል ውስጥ ነው፡፡ በእንድ ክፍል ውስጥ ብዙ እስረኛ ከመኖሩ የተነሳ ሶስት እስረኛ በሰንሰለትና በቦንዳ አንድ ላይ ተጠላልፎ ነው የሚታሰረው፡፡ በዚህ አሰቃቂ ሁኔታ ውስጥ ነው 24 ሰአት ሚሉ የምትታሰረው›› ብሏል፡፡

ለዘጠኝ አመታት ያህል ፍርድ ቤት ሲመላለስ ከቆየ በኋላ በትግራይ ውስጥ ሞት ተፈርዶበት እንደነበርም ለመፅሄቱ አስረድቷል፡፡ ሞት ከተፈረደበት በኋላ ይግባኝ ጠይቆ ምንም ምላሽ አለማግኘቱንም ገልጧል፡፡ ሲናገርም ‹‹ዘጠኝ አመት ከታሰርኩ በኋላ ነው ሞት የተፈረደብኝ፡፡ ያኔ መቀሌ ይግባኝ ብዬ ነበር፡፡ እዛም ከስድስት ወር በኋላ ውሳኔው ይፅና ብለው ተስማሙ፡፡ በጣም የሚገርመው ቀን ሰብረው፣ አቃቤ ህግ በሌለበት፣ እኔ ባልቀረብኩበት፣ ያለክርክር ነው ውሳኔው መፅናቱ ይፋ የተደረገው፡፡›› ብሏል፡፡ ነገር ግን የተፈረደበት የሞት ውሳኔ ተግባራዊ ሳይደረግ በ2003 መስከረም ወር በምህረት እንደተለቀቀ ተናግሯል፡፡

ስለወ/ሮ አዜብ መስፍን የተጠየቀው ካሳሁን ሲሳይ ‹‹ከአዜብ ጋር ዝምድናችን የቅርብ ብቻ ሳይሆን እህቴ ማለት ናት፡፡ ግን እሷ እንኳን ለኔ ለእናቷም አትሆንም፡፡ እንኳን ቤተሰብ የአገር ሰው የሚባል እንዲቀርባት አትፈልግም›› የሚል ምላሽ ሰጥቷል፡፡ ግዮን መፅሄት ‹‹ወ/ሮ አዜብ የትግራይ ተወላጅ ናቸው?›› የሚል ጥያቄ ያነሳለት ካሳሁን ሲመልስ
‹‹አንድም ትግሬ የለባትም፡፡ ይልቅ የትግራይ ሙሽራ ናት ብትል ያስኬዳል፡፡ የወልቃይት ተወላጅ የጎንደር ሰው ናት፡፡ የእሷ አያት ደጃዝማች ጎላ ጣሊያን ለመጀመሪያ ጊዜ ሲመጣ በተደረገ ውጊያ ያኔ ሰባት መድፍ ማርከዋል፡፡ መድፉ ከባድ ስለነበርና ከቦታው አልነሳ ሲላቸው እያንዳንዱ መድፍ ላይ ጎላ ጎሹ እያሉ ስማቸውን ፅፈውበታል፡፡ እኚህ ሰው ጥርት ያሉ ጎንደሬ፣ የእናቷ አባት ናቸው›› በማለት አስረድቷል፡፡
https://www.youtube.com/watch?v=f9ZDJjIZNkI

Previous Story

ፕሮፌሰር መረራ ‹‹የጠመንጃ ፖለቲካ ማብቃት አለበት›› አሉ

Next Story

የቀድሞው የፌዴራል ፖሊስ አዛዥ ታሠሩ | ቀድሞው የማእከላዊ ምርመራ ምክትል አዛዥ እየታደኑ ነው

Go toTop