(ዘ-ሐበሻ) “ሰላማዊ ትግል ፈተናው ከባድ ነው። እንደዚህ ቢፈታተኑንም እኛ ተስፋ አንቆርጥም። ይህ የትግላችን መጀመሪያ እንጂ መጨረሻ አይደለም። እየወደቅንም እየተነሳንም ቢሆን ትግሉን ከዳር እናደርሳለን።” ነበር ያለችን ወ/ሪት መሠረት የዛሬው የሰማያዊ ፓርቲ የተቃውሞ ሰልፍ በአዲስ አበባ እና በፌደራል ፖሊስ ከታገተ በኋላ። “መንግስት ሰልፉን ለምን በመስቀል አደባባይ እንዳይደረግ እንደፈራ ይገባናል። በጃንሜዳ አድርጉ የሚል የሰልፍ ፍቃድ የሰጠን ጃንሜዳ የጥምቀት ማክበሪያ ቦታ እንጂ የተቃውሞ ሰልፍ ማድረጊያ ቦታ አለመሆኑን እያወቀ ጃንሜዳ በግቢ የታጠረ ስለሆነ መንግስት ድምጽን ለማፈን እና ተቃውሞውን ለመቆጣጠር በማሰብ ይህን ቢያደርግም እኛ ድምጻችንን መንግስት ብቻ ሳይሆን የነፃ ሚዲያ ዘገባ የማያገኘው ሕዝባችን እንዲሰማ በማሰብ ጭምር ሰልፉን መስቀል አደባባይ ለማድረግ ቆርጠን ነበር። ሕገመንግስቱን ለማስከበር የቆሙት ፌደራል ፖሊሶች የኢሕአዴግን ሥርዓት ስለሚያስከበሩ ሰልፋችንን ቢያግቱትም ሰላማዊ ተቃውሟችን ግን አሁንም እንዳስበረገጋቸው ተረድተናል፡” ብላለች ወ/ሪት መሠረት።
በደማቅ ሁኔታ የተጀጀመረው የሰማያዊ ፓርቲ የዛሬው የተቃውሞ ሰልፍ በአዲስ አበባ እና በፌደራል ፖሊሶች እገታ ከአራት ኪሎ ወደ መስቀል አደባባይ እንዳይሻገር ቢታገድም ለተቃውሞ የወጣው ሕዝብ ግን ድምጹን ሳያሰማ አልቀረም። መቶ ሜትር ሳይሻገር በመንግስት ኃይሎች የታገተው ይኸው የተቃውሞ ሰልፍ ላይ የፌደራል ፖሊሶች ሕዝቡን ካሜራ እንዳያነሳ ከመከልከል በተጨማሪ ቪድዮና ፎቶ ግራፍ የቀዱ ሰዎችን ካሜራውን እየተቀበሉ ፎቶ ግራፉን ማስጠፋታቸውን የዘ-ሐበሻ ዘጋቢዎች ከአዲስ አበባ ዘገበዋል። ይሁን እንጂ አልፎ አልፎ ከፌደራል ፖሊስ ያመለጡ ፎቶ ግራፎች ፌስቡክን በመሳሰሉ የማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ተለቀዋል።
ተቃዋሚው ሰልፈኛ በ እስር ቤት ያሉ ጋዜጠኞች እና ፖለቲከኞች እንዲፈቱ የጠየቁ ሲሆን
“ፍትህን መጠየቅ አሽባሪነት አይደለም!
ነፃነት እንፈልጋለን!
እኛ አሽባሪ አይደልንም!
ፍትሕ እንፈልጋለን!
የሙሰሊም ኮሚቴ ይፈቱ!
ዜጎችን ማፈናቀል አግባብ አይደለም!
አንለያይም!
አንለያይም!
ፍትህን ያሉ ቃልቲ ገቡ!
ፍትህ ናፈቀኝ!
የሚሉና ሌሎችንም መፈክሮችን ሲያሰሙ ተደምጠዋል። ለተቃውሞ የወጣው ህዝብ በፌድራል ፖሊሶች ተከልክሎ ወደ መስቀል አደባባይ እንዳይሄድ ቢታገትም ወደ ሰማያዊ ፓርቲ ቢሮ በመመልሰ እንዲሁም በአራት ኪሎ አደባባይ ላይ ድምጹን በማሰማት የሰላማዊው ተቃውሞ ሰልፍ በሰላም ተጠናቋል።
“ሰላማዊ ትግል የሚጠይቀውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ ነን” ያለችው ወ/ሪት መሠረት “ትግሉ ተጀመረ እንጂ አላለቀም፤ በመንግስት ወከባ የሚደነግጥ የለም” ስትል ለዘ-ሐበሻ የሰጠችውን አስተያየት አጠናቃለች።
የፊታችን እሁድም እንዲሁ አንድነት ፓርቲ እና 33ቱ ፓርቲዎች በጋራ በመስቀል አደባባይ የተቃውሞ ሰልፍ መጥራታቸው ይታወሳል።