ታላቅ የተቃውሞ ሰልፍ በጀርመን ፍራንክፈርት ከተማ ተካሄደ

August 17, 2013

እ.ኤ.አ በኦገስት 17 ቀን 2013 ዓ.ም. በጀርመን ሀገር ፍራንክፈርት ከተማ የኢትዮጵያውያን የፖለቲካና ሲቪክ ማህበር አባላት አንድነት ድርጅት (ኢ.ፕ.ኮ.) በጠራው ታላቅ የተቃውሞ ሰልፍ ላይ ከተለያዩ የጀርመን ከተሞች የተሰባሰቡ ቁጥራቸው ከ400 በላይ የሆኑ ኢትዮጵያውያን፣ትውልደ-ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች የተገኙ ሲሆን የኢትዮጵያ ህዝብ አንድነት ፓርቲ /ኢሕአፓ/፣የሞረሽ ወገኔ የአማራ ድርጅት /ሞረሽ/ እና የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር አመራር እና አባላትም በሰልፉ ላይ ተገኝተዋል።

መነሻውን ”ሃውፕት ቫኸ” /Haupt Wache/ ከሚባለው የከተማው ክፍል በማድረግ በተለያዩ መፈክሮችና የኢትዮጵያ ባንድራ በማሸብረቅ ጉዞውን በተለያዩ የከተማው ክፍል በማድረግ ከሶስት ሰዓት የእግር ጉዞ በኋላ መዳረሻውን በዚያው በሃውፕት ቫኸ  አድርጓል።

የሰልፉ አላማ የሚከተለው ሲሆን ፦

  • ስልጣንን መከታ በማድረግ የደሃ ህዝባችንን ሀብት በሙስና በመዝረፍ በተለያዩ  የውጭ ሀገር ባንኮች ውስጥ የተቀመጡ ንብረቶች ባስቸኳይ እንዲመለሱና ወንጀለኛ የወያኔ ባለስልጣናት ለፍርድ እንዲቀርቡ ለመጠየቅ
  • በወያኔ እስር ቤት የሚሰቃዩ የፖለቲካ እስረኞች ባስቸኳይ እንዲፈቱ ለመጠየቅ
  • የወያኔ/ኢህአዴግ በሃይማኖት ጣልቃ ገብነት አብቅቶ የሙስሊም ወገኖቻችን የድምፃችን ይሰማ ጥያቄ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ጥያቄያቸው መልስ እንዲያገኝ
  • የሰማያዊ ፓርቲ ባለፈው ላደረጋቸውና ወደ ፊትም ለያዛቸው ህዝባዊ ንቅናቄዎች ደጋፊ መሆናችንን ለማረጋገጥና ሌሎችም እንደ መኢአድና መድረክ የመሳሰሉ ድርጅቶች እያደረጉ ያለውን ዴሞክራሲያዊ ትግል ከልብ የምንደግፍ መሆናችንን ለማሳወቅ ሲሆን

 

ከሶስት ሰዓት በላይ የፈጀው ሰላማዊ ሰልፍ ከመጠናቀቁ በፊት በኢ.ፕ.ኮ ሊቀ መንበር አቶ በላይነህ ወንዳፍራሽ እንዲሁም የተለያዩ የፖለቲካ አመራሮች አጠር ያለ ንግግር ያደረጉ ሲሆን ተሰላፊውም በሀገራችን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እውን እስከሚሆን ድረስ የሚያደርገውን ትግል አጠናክሮ እንደሚቀጥል በአቋም መግለጫው ቁርጠኝነቱን ገልጿል።

 

Beyene Mesfin

Germany.

Previous Story

ወቅታዊ ጥሪ – በስደት የኢትዮጵያ መምህራን ማሕበር አተባባሪ ኮሚቴ

Next Story

ታላቅ የተቃውሞ ሰልፍ በኦስሎ ኖርዌይ ተካሄደ

Go toTop