የቀድሞው የአክሰስ ሪል ስቴት ስራ አስኪያጅ አቶ ኤርሚያስ አመልጋ በተከሰሱበት የደረቅ ቼክ መስጠት ወንጀል የ600 ሺህ ብር ዋስትና ተፈቀደላቸው።
ዓቃቢ ህግ ግለሰቡ የተከሰሱት በስድስት ክሶች መሆኑንና የገንዘቡ መጠንም ከ4 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር በላይ በመሆኑ ቢለቀቁ ሊሰወሩ ይችላሉ በሚል ዋስትናቸው ውቅድ እንዲሆን ጠይቆ ነበር።
የተከሳሽ ጠበቆች በበኩላቸው የቀረበው ተቃውሞ ተጨባጭ ማስረጃ የሌለውና የክሱ አንቀጽ ዋስትና የሚያስከለክል ባለመሆኑ ደንበኛቸው ዋስትና ሊፈቀድላቸው ይገባል ሲሉ ተከራክረዋል።
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ 1ኛ የወንጀል ችሎትም የግራ ቀኙን መርምሮ ተከሳሽ ከተጠረጠሩበት ቀን ጀምሮ ከ3 ዓመት በኋላ እዚሁ አገር ውስጥ የተገኙ በመሆኑና በዓቃቢ ህግ የቀረበው መቃወሚያ በህጉ ዋስትና የሚያስከለክል ባለመሆኑ ዋስትናው ሊፈቀድላቸው ይገባል ብሏል።
በዚህም የክሱን ጭብጥና ወርሃዊ ገቢያቸውን ከግምት በማስገባት የ600 ሺህ ብር ዋስትና ተፈቅዶላቸዋል።
ከሀገር እንዳይወጡም እገዳ ተፅፎባቸው ለሚመለከተው ሁሉ እንዲላክ ትዕዛዝ ተላልፏል።
አቶ ኤርሚያስ ከእምነት ማጉደል ወንጀል ጋር ተያይዞ የስር ፍርድ ቤት ለፈቀደላቸው ዋስትና የፖሊስ ይግባኝ ላይ መርምሮ ብይን ለመስጠት ለመጋቢት 30 ቀን 2008 ዓመተ ምህረት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
በሀይለየሱስ ስዩም