Sport: ፒዬር ኮሊና፡ ‹‹አርቢትር ተዋናይ ሊሆን አይገባውም››

May 30, 2014

በሸንቃጣ ቁመናቸው፣ በራስ በራነታቸው እንደዚሁም የሰውን ልብ ጠልቀው የሚመረምሩ በሚመስሉት ሰርሳሪ አይኖቻቸው ተለይተው ይታወቃሉ- ፒዬር ሉዊጂ ኮሊና፡፡ ወደ ፍፁምነት የቀረበው ዳኝነታቸው ደግሞ በተጨዋቾችም ሆነ አሰልጣኞች ክብር እና አመኔታን አስገኝቶላቸዋል፡፡ ቀጣዩ ዝግጅት ዝነኛው ጣልያናዊ ዳኛ ለቀረቡላቸው ከእግርኳስ ዳኝነት ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች የሰጡትን ምላሽ ነው፡፡
ጥያቄ፡- ዳኛ ዝነኛ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?
መልስ፡- ለዚህ ጥያቄ መልስ ያለኝ አይመስለኝም፡፡
ጥያቄ፡- በእግርኳስ ታሪክ ኮከብ መሆን የቻሉ የመጀመሪያው እና ብቸኛው ዳኛ እርስዎ ኖት፡፡ በብራዚሉ የዓለም ዋንጫ ለመዳኘት እየተዘጋጁ ላሉ የሞያ ጓደኞችዎ የሚሆን ምክር ይኖሮታል ብለን እናስብ…
መልስ፡- በዳኝነት ዘመን አደርግ የነበረው ዋነኛው ነገር ስራዬን ኮስተር ብዬ እና በንቃት ለመስራት መሞከር ነው፡፡
ጥያቄ፡- የዓመቱ ምርጥ ዳኛ ተብለው በስድስት ተከታታይ ዓመታት ተመርጠዋል፡፡ ይህ የምንጊዜውም ሪከርድ ነው፡፡ ከሌሎቹ የተሻለ የሚያከናውኑት ነገር ነበር?
መልስ፡- ከመጀመሪያ ጀምሮ ስራዬን እሰራ የነበረው በፕሮፌሽናሊዝም መርህ ስር ሆኜ ነበር፡፡ ምናልባት ከሚያስፈልገው በላይ ሰርቼ ሊሆን ይችላል፡፡ በ1990ዎቹ መጨረሻ ላይ የነበሩ ዳኞች መመሪያውን ጠንቅቀው እንዲያውቁ እና ብቁ የሆነ የአካል ብቃት እንዲኖራቸው ይጠበቅ ነበር፡፡ የሚፈለገው ይሄ ብቻ ከነበረ እኔ ብዙ ርቄ ሄጃለሁ፡፡ ከጨዋታ በፊት ስለ ቡድኖቹ በአጠቃላይ እና ስለ ተጨዋቾቹ በግል ለማወቅ ከፍተኛ ጥረት አደርግ ነበር፡፡ በጃፓን እና ኮሪያ የተዘጋጀውን የኣለም ዋንጫ ፍጣሜ ከመምራቴ በፊት ከባልደረቦቼ ጋር በመሆን ቡድኖቹ ከዚህ በፊት ያደረጓቸውን ጨዋታዎች የሚያሳዩ የቪዲዮ ምስሎች ተመልክቼያለሁ፡፡ እንቅስቃሴቸውን እና ከሌሎች የሚለያቸውን ነገር አጥንቼያለሁ፡፡ ይህንንም በዕለቱ አብረውኝ ከሰሩ ረዳቶች ጋር ተወያይተንበታ፡፡ የቤት ስራህን በአግባቡ ከፈፀምክ እንግዳ የሚሆንብህ ነገር በሜዳ ውስጥ አይፈጠርም፡፡
ጥያቄ፡- በመሆኑም ጥሩ የሚባል ዳኛ ምንም ነገር በአጋጣሚ እንዲከሰት አይፈቅድም ማለት ነው?
መልስ፡- በትክክል፡፡ ጥሩ ዳኛ ከጨዋታው አንድ እርምጃ መቅደም አለበት፡፡ ምን ሊከሰት እንደሚችል ቀድሞ መገመትም ይኖርበታል፡፡ ጨዋታው ወዴት ሊያመራ እንደሚችል ግንዛቤው ያላቸው ዳኞች ብቻ ናቸው፡፡ በትክክለኛው ጉዞ ትክክለኛው ቦታ ላይ መገኘት የሚችሉትም እነርሱ ናቸው፡፡ ይህን በማድረጋቸውም የሚፈጠሩትን ክስተቶች የመመልከት ዕድል ያገኛሉ፡፡ ትክክለኛ ውሳኔም ያስተላልፋሉ፡፡ ይህን የሚያደርግ ዳኛ ግን ለከፋ ስህተት ይዳረጋል፡፡
ጥያቄ፡- ጥሩ ዳኛ የሚባለው ለዘብተኛ የሆነ ወይስ ጥብቅ?
መልስ፡- ጥሩ ዳኛ ትክክል የሆነ ነው፡፡ እኔ ሁሉ ነገሬን ለሙያው አሳልፌ ሰጥቼ ነበር፡፡ በዚያ ላይ ለሁሉም ፍትሃዊ ለመሆን ሞክሬያለሁ፡፡ እነዚህ ባህሪያት የጥሩ ዳኛ መገለጫዎች እዲሆኑም እመኛለሁ፡፡
ጥያቄ፡- በኋላ ላይ የተፀፀቱበትን የተሳሳተ ውሳኔ አስተላልፈው ያውቃሉ?
መልስ፡- ፀፀት የሚለው የተሳሳተ ቃል ነው፡፡ የተሳሳተ ውሳኔ በማስተላለፌ ግን አዝኜ አውቃለሁ፡፡
ጥያቄ፡- ለእንደዚህ አይነቶቹ ስህተቶች የሚሰጡት ምን አይነት አፀፋዊ ምላሽ ነበር?
መልስ፡- በጥልቀት እመረምረው እና እንደህ ያለውን ስህተት የሰራሁት ለምንድን ነው? ብዬ ራሴን እጠይቃለሁ፡፡ የትኛውም ስህተት ማብራሪያ አለው፡፡ ራሴን የምጠይቀው ለምን ስህተቱን ፈፀምኩ? በበቂ ሁኔታ አልተዘጋጀሁም ነበር ማለት ነው? የሚሉ እና መሰል ጥያቄዎችን ነበር፡፡ በመጨረሻ ግን ስህተት ስለተፈፀመባቸው ውሳኔዎች መርሳት አስፈላጊ ነው፡፡ ከስህተት በኋላ መደረግ ያለበት ወሳኙ ነገር ከመቼውም ይልቅ ጠንካራ ሆኖ ወደ ሜዳ መመለስ ነው፡፡
ጥያቄ፡- ጥሩ ዳኛ ለፈፀመው ስህተት ይቅርታ መጠየቅ ይጠበቅበታል?
መልስ፡- ይቅርታ የምጠይቀው ለምንድነው? ይቅርታ የምጠይቀው ሆን ብዬ የፈፀምኩት ነገር ካለ ነው፡፡ በተረፈ የቻልኩትን ያህል ጥረት አድርጌ፣ ትክክለኛውን ውሳኔ ለማስተላለፍ በምውተረተርበት ወቅት ስህተት ብፈፅም ይቅርታ እንድጤቅ አልገደድም፡፡
ጥያቄ፡- ጠንካራ ጎኖ ምንድነው?
መልስ፡- ለኃላፊነቱ ራሴን መስጠቴ እና ሁልጊዜም የምችለውን ሁሉ ለማበርከት መሞከሬ፡፡
ጥያቄ፡- ደካማ ጎኖስ?
መልስ፡- (ረዘም ላለ ጊዜ አሰቡ) ስህተትን አምኖ ለመቀበል አስቸጋሪ ይሆንብኛል፡፡ አንድ ተጨዋች የፍፁም ቅጣት ምት ሲስት የቡድን ጓደኞቹ ያፅናኑታል፡፡ ነገር ግን በ10 ሺ የሚቆጠሩ ሰዎች ዳኛው ላይ ቢጮሁበት እና ተቃውሞ ቢያሰሙ ከጎኑ የሚሆን የለም፡፡ ዳኛ ወፍራም ቆዳ ያስፈልገዋል መባሉ እውነት ነው፡፡ ቀድሞ ነገር ዳኛ መሆን ከፈለግክ መሟላት ከሚገቡህ ነገሮች አንዱ እርሱ ነው፡፡ በሜዳው ውስጥ ከተፈጠረ አሊያም ሊፈጠር ከሚችል ማንኛውም ነገር ራስን ገለልተኛ ማድረግም አስፈላጊ ነው፡፡ በስራው ላይ መቆየት የምትችለው ይህንን ካደረግክ ብቻ ነው፡፡ ውጥረትን መቋቋም መቻልም የግድ ነው፡፡
ጥያቄ፡- አንዳንድ ዳኞች ጫናውን መቋቋም አቅቷቸው ስራውን ለማቆም ተገድደዋል፡፡ በዚህ ላይ ምን አስተያየት አለዎት?
መልስ፡- በየትኛውም የስራ መስክ ከሌሎች በተሻለ ጫናን መቋቋም የሚችሉ ሰዎች አሉ፡፡ አንድ ዳኛ በከፍተኛ ደረጃ ላይ እንዲዳኝ ከተመደበ ጫናውን መቋቋም እንደሚችል አስመስክሯል ማለት ነው፡፡
ጥያቄ፡- በስታዲየም ተገኝተው ጨዋታውን ከሚከታተሉት ከ80 ሺ በላይ ተመልካቾች በተጨማሪ በመላው ዓለም በቢሊዮን የሚቆጠሩ የእግርኳስ አፍቃሪያን ጨዋታውን በቴሌቪዥን መስኮት በቀጥታ እየተከታተሉት መሆኑን እያወቁ ጨዋታን በተረጋጋ ስሜት መምራት አይከብድም?
መልስ፡- ይህ ሀሳብ ለአፍታም ቢሆን በአዕምሮህ ውል እንዲል ልትፈቅድለት አይገባም፡፡ የማስበው ሁሉም ጨዋታ ከወትሮው ያልተለየ ጨዋታ እንደሆነ አድርጌ ነበር፡፡ በዚያው ልክ እያንዳንዱን ጨዋታ የምመራው የዓለም ዋንጫ ፍፃሜ እንደሆነ አድርጌ ነበር፡፡ የኋለኛው የበለጠ አስቸጋሪ መሆኑ ግን ግልፅ ነው፡፡
ጥያቄ፡- ስለዚህ ተፈጥሯዊ ከሆነው መንገድ ወጣ ብሎ መጓዝ ያስፈልጋል ማለት ነው?
መልስ፡- ሁልጊዜም በሙሉ ትኩረት ጨዋታዎችን ለመዳኘት እሞክር ነበር፡፡ አንድ ወቅት ማንቸስተር ዩናይትድ ከሪያል ማድሪድ ጋር ያደረገውን ጨዋታ ረቡዕ ዕለት አጫውቼ ከሶስት ቀን በኋላ በጣልያን ሴሪቢ ሌላ ጨዋታ መምራቴን አስታውሳለሁ፡፡ ለመጀመሪያው ጨዋታ የሚያስፈልገውን ትኩረት ማግኘት በጣም ቀላል ነበር፡፡ የሴሪቢውን ጨዋታ ግን በተመሳሳይ ትኩረት ለመምራት ተቸግሬ ነበር፡፡ ለማሻሻል ጥረት አደርግ የነበረውም ያንን አይነቱን ነገር ነበር፡፡
ጥያቄ፡- የተሻሉት ተዋንያኖች የትኞቹ ናቸው? ተጨዋቾች ወይስ ዳኛው?
መልስ፡- ዳኛ ተዋናይ ሊሆን አይገባውም፡፡ መሆን ያለበት እውነተኛ ነው፡፡ አንድ ዳኛ ያልሆነውን ነገር ለመሆን ቢሞክር ወዲያውኑ ታውቁበታላችሁ፡፡
ጥያቄ፡- አንድ እግርኳስ ተጨዋች በሜዳው ውስጥ ሊያደርግ የሚችለው እጅግ የከፋ ነገር ምንድነው?
መልስ፡- ጥፋት ሳይፈፀምበት አስመስሎ መውደቅ፡፡ ይህም አላማን በማጭበርር ለማሳካት መሞከር ተብሎ ሊገለፅ ይችላል፡፡ ያንን የምታደርግ ከሆነ የምታታልለው ዳኛውን እና ተጋጣሚህን ብቻ አይደለም፡፡ በድርጊቱ የእግርኳስ ተመልካቾችንም ታጭበረብራለህ፡፡ ሆነ ብሎ የጨዋታን ውጤት በተሳሳተ መንገድ መቀየር ከማሸነፍ ጋር የሚያያይዘው ነገር የለም፡፡ ይህ ጉዳይ የበለጠ ትኩረት ሊቸረው ይገባል፡፡
ጥያቄ፡- በጨዋታ ወቅት ተጨዋቾች በተደጋጋሚ ሳይነኩ ሲወድቁ ሲመለቱ በብስጭት ደምዎ ይፈላ ነበር?
መልስ፡- በጭራሽ፡፡ የሚገባው ደምህ ሊፈላ ሳይሆን ለተጫዋቹ ቢጫ ካርድ ልታሳየው ነው፡፡
ጥያቄ፡- አሁን አሁን እርስዎን ማግኘት ይበልጥ አስቸጋሪ ሆኗል፡፡ ትክክል ነኝ?
መልስ፡- አውቃለሁ፡፡ በዚህም ጥፋተኝነት ይሰማኛል፡፡ ነገር ግን ይህ እንዲሆን ያደረጉት አንዳንድ ሁኔታዎች ናቸው፡፡
ጥያቄ፡- እንዴት ያሉ ሁኔታዎች?
መልስ፡- መጥፎ የሚባሉ ተሞክሮዎችን ያለፍኩባቸው አጋጣሚዎች ነበሩ፡፡ በተደጋጋሚ ዛቻ ተሰንዝሮብኛል፡፡ ከዚያም አልፎ እኔን ለማስፈራራት ጥይቶች ሁሉ ተልከውልኛል፡፡ ፖሊስ ጥበቃ ያደርግልኝ የጀመረው ከዚያ በኋላ ነው፡፡ እያንዳንዱ እንቅስቃሴዬም ክትትል ይደረግበታል፡፡
ጥያቄ፡- በጣልያን ለእርስዎ የሚደረገው ጥበቃ ከአንድ የወንበዴዎች ቡድን ጋር የተያያዘ ጉዳይን ከያዘ አቃቤ ህግ ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ መናገር እንችላለን?
መልስ፡- ከሞላ ጎደል አዎን፡፡ የሚያስደስት ተሞክሮ ግን አይደለም፡፡ በሁለት የፖሊስ መኮንኖች ታጅቦ ከቤት መውጣት የሚያኮራ አይደለም፡፡
ጥያቄ፡- የሚያስፈራሩዎት እነማን ናቸው?
መልስ፡- ያንን የሚያደርጉት ሰዎች ተይዘው አያውቁም፡፡ ዛቻውም በሂደት አቁሟል፡፡ ነገር ግን በእግርኳስ እንዲህ ያለው ነገር መከሰቱ ያሳዝናል፡፡
ጥያቄ፡- በዳኝነቱ በኩል ኮከብ መሆን ችለዋል፡፡ ሌላ ተጨማሪ ስራ ነበረዎት?
መልስ፡- ለበርካታ ዓመታት ለአንድ ባንክ በትርፍ ሰዓቴ የፋይናንስ አማካሪ ሆኜ እሰራ ነበር፡፡ ከዳኝነት ስራዬ ጋርም ይጣጣም ነበር፡፡
ጥያቄ፡- ዳኞች ከተጫዋቾች ጋር ተቀራራቢ የሆነ የአካል ብቃት እንዲኖራቸው ይጠበቃል፡፡ የስታትስቲክስ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት አንድ ተጨዋች በየጨዋታው በአማካይ ከ10 እስከ 11 ኪሎ ሜትሮችን ይሸፍናል፡፡ ዳኞች ደግሞ ከ10 እስከ 12፡፡ ዋነኛው ልዩነት ተጫዋቾች በየዕለቱ ልምምድ የሚሰሩ መሆኑ እና ዳኞች ግን ብዙውን ጊዜያቸውን የሚያጠፉት ቢሮ ውስጥ መሆኑ ነው፡፡ ይህ አግባብ እንደሆነ ያስባሉ?
መልስ፡- ዳኞች የመዘጋጃ ጊዜ የሚያስፈልጋቸው በአካል ብቃት በኩል ብቻ አይደለም፡፡ በብዙ አገራት ዳኞች የሚከፈላቸው ጨዋታዎችን ሲመሩ ብቻ ወን፡፡ በአንዳንድ አገራት ክፍያው ከፍተኛ ነው፡፡ አንዳንዶች ጋር ደግሞ ያንሳል፡፡ ነገር ግን ዳኛው ጨዋታውን በቻለው አቅም በጥሩ ሁኔታ ለመምራት የሚያስችል በቂ ጊዜ ያስፈልገዋል፡፡ ዝግጅት የሚጀምረው ከጨዋታው ቀደም ብሎ መሆኑ ደግሞ ግልፅ ነው፡፡ በመሆኑም አንድ ዳኛ በዝግጅት ለሚያሳልፈው ጊዜ ሊከፈለው ይገባል፡፡
ጥያቄ፡- አሁን 54 ዓመትዎ ነው፡፡ ነገር ግን የሚገኙት በሚያስገርም የአካል ብቃት ደረጃ ላይ ነው? ምስጢሩ ምንድነው?
መልስ፡- ቅርፄን ሳላጣ ለመቆየት እሞክራለሁ፡፡ ነገር ግን በየጊዜው ስለምጓዝ ያንን ማድረግ አስቸጋሪ ሆኖብኛል፡፡ የምኖረው በባህር ዳርቻ አካባቢ ነው፡፡ ብዙውን ጊዜም የባህር ዳርቻውን ተከትዬ በሶምሶማ እሮጣለሁ፡፡
ጥያቄ፡- የአውሮፓ እግርኳስ ማህበር የዳኞች ኮሚቴን በመምራት ላይ ይገኛሉ፡፡ ይህ መሆኑ የፊፋን የዳኞች ልማት እንደሚመሩት ማሲሞ ቡሳካ ከመሳሰሉ የቀድሞ የስራ ባልደረቦችዎ ጋር መቃቅርን አስከትሏል?
መልስ፡- በጭራሽ፡፡ ማሊሞ እና እኔ መልካም ግንኙነት ነበረን፡፡ አሁንም ያ ግንኙነታችን እንዳለ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ ሁለታችንም በጋራ ከቤተሰቦቻችን ጋር ለእረፍት ሽርሽር የምንጓዝባቸው ጊዜያት አሉ፡፡ ይህም ከእርሱ ጋር በቀላሉ ሃሳብ መለዋወጥ እንድችል አድርጓል፡፡ በዚህ ደግሞ ደስተኛ ነኝ፡፡
ጥያቄ፡- መሻሻል የሚገባው ክፍተቶች በዳኞች የመመሪያ ሰነድ ላይ አለ?
መልስ፡- የተወሰኑ ክፍተቶች አሉ፡፡
ጥያቄ፡- ቢያንስ አንዱን ለአብነት ሊጠቅሱልን ይችላሉ?
መልስ፡- አንድ ተጨዋች ጥፋት ፈፅሞ ቢ ካርድ ተመለከተ እንበል፡፡ ጥፋቱን ሲፈፅም ደግሞ በተጋጣሚው ቡድን ተጨዋች ላይ ጉዳት አድርሶ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ከሆነ ጥፋት የተፈፀመበት ተጨዋች የህክምና እርዳታ ለማግኘት ሜዳውን ለቅቆ ለመውጣት ይገደዳል፡፡ ልክ እርሱ ከሜዳ እንደወጣ ጨዋታው ይጀመራል፡፡ ይህም የጥፋት ፈፃሚው ቡድን ለጊዜውም ቢሆን የቁጥር የበላይነት እንዲኖረው ያደርጋል፡፡ በስፖርታዊ ጎኑ ካየነው አካሄዱ ፍትሃዊ አይደለም፡፡ ጥፋት ፈፃሚው ቡድን ተጨማሪ ተጫዋች ይዞ እንዲጫወት በመደረጉ ተጠቃሚ ይሆናል፡፡ የተሻለ ስሜት የሚሰጠው የተጎዳው ተጫዋች ወደ ሜዳ እስኪመለስ ድረስ ጥፋት ፈፃሚውም ከሜዳ ወጥቶ እንዲጠበቅ ተደርጎ ህጉ ቢሻሻል ነበር፡፡
ጥያቄ፡- ሁለት እግራቸውን ከመሬት ሳይነቅሉ እጃቸውን ከራሳቸው ኋላ አድርገው የመልስ ውርወራ የሚወረውሩ ተጨዋቾች ጥቂት ናቸው፡፡ ዳኞች በዚህ ረገድ ጥብቅ የማይሆኑት ለምንድን ነው?
መልስ፡- ህጎቹ ግልፅ ናቸው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ዳኞች ቸልተኛ የሚሆኑት የመልስ ውርወራዎች በጨዋታው ላይ ወሳኝ ሚና የላቸውም ብለው ስለሚያስቡ ነው፡፡
ጥያቄ፡- ስለዚህ የጨዋታውን ህጎች በትክክል ሜዳ ውስጥ ለመተግበርደ ዳኞች የተለየ ችሎታ ሊኖራቸው ይገባል ማለት እንችላለን?
መልስ፡- አዎን ያስፈልጋቸዋል፡፡
ጥያቄ፡- አንድ ጥሩ ዳኛ ሙሉ በሙሉ ራሱን ሊቆጣጠር እና የሌሎችን ስህተት ሊረዳ ይገባል?
መልስ፡- በትክክል፡፡
ጥያቄ፡- ጥሩ ዳኛ ጥሩ የስነ ልቦና ባለሞያ መሆን ይኖርበታል ማለት ነው?
መልስ፡- ይህ ትንሽ የተጋነነ ገለፃ ነው፡፡ ነገር ግን አንድ ዳኛ ስለ ሰው ልጅ ተፈጥሮ የተወሰነ ግንዛቤ ሊኖረው የግድ ነው፡፡ የተጫዋቾችን አካላዊ ቋንቋ ማንበብ መቻል እና ሰዎችን እንዴት በተገቢው ሁኔታ መያዝ እንዳለበት ማወቅ ይጠበቅበታል፡፡ ለምሳሌ ወደ ተጫዋች በጣም ተጠግቼ ብቆም አሊያም ብነካው የግሉ የሆነውን ቦታ እየተጋፋሁት ነው፡፡ ይህም የተጫዋቹን ውጤታማነት ሊቀንስ የሚችልበት ዕድል ሊኖር ይችላል፡፡ በመሆኑም ሁልጊዜ ተጫዋቾችን በጣም ተጠግቼ አለመቆሜን አረጋግጣለሁ፡፡
ጥያቄ፡- ያጠኑት ስነ ልቦና ነው?
መልስ፡- አይደለም፡፡ እኔ የተማርኩት ኢኮኖሚክስ ነው፡፡ ነገር ግን የተወሰኑ የስነ ልቦና መፅሐፍትን አንብቤያለሁ፡፡
ጥያቄ፡- ዳኛ ስሜታዊ መሆን ይፈቀድለታል?
መልስ፡- ዳኛ የተለየ ነው እስካልተባለ ድረስ አዎን፡፡ ስሜታዊ ስንል ለስራው ያለውን ፍቅር ተንተርሰን ከሆነ አዎን፡፡ ስሜታዊ መሆን ይገባዋል፡፡
ጥያቄ፡- እነዚህን ሁሉ ብቃቶች ያለው የትኛውም ሰው መጠነኛ ክፍያ የሚያስገኝለትን እና በዘላቂነት በጫና ውስጥ እንዲሆን የሚያስገድደውን ስራ ለመስራት ፈቃደኛ እንዲሆን የሚያደርገው ምን እንደሆነ ሊያብራሩልን ይችላሉ?
መልስ፡- ይህን ለማብራራት የስራውን ጠቃሚ ጎኖች መጥቀስ ሳያስፈልግ አይቀርም፡፡ የእግርኳስ ዳኛ በመሆኔ ከታላላቅ ተጨዋቾች ጎን በሜዳ ውስጥ የመገኘት ዕድል ይኖረኛል፡፡ ከፍተኛ ግምት የሚሰጣቸውን ጨዋታዎችም እመራለሁ፡፡ በ2002 ብራዚል እና ጀርመን ያደረጉትን ጨዋታ ከመራ በኋላ በፊፋው ፕሬዝዳንት ጆሴፍ ብላተር ሜዳልያ ተበርክቶልኛል፡፡ ለአንድ ዳኛ የሚሰጠው ስሜት አንድ ተጨዋች የዓለም ዋጫን ማሸነፉ ከሚፈጥርበት ስሜት ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡
ጥያቄ፡- ዳኝነትን እንዴት ጀመሩ?
መልስ፡- እስከ 17 ዓመቴ እኔ እራሴ እግርኳስ ተጫዋች ነበር፡፡ በርካቶች ግን የዳኝነት ተሰጥኦው እንዳለኝ ይነግሩን ነበር፡፡ በሽርፍራፊ ሰከንዶች ውስጥ ውሳኔ ማስተላለፍ እንደምችል እና ይህንንም ለትልለቆቹ ተጫዋች ምክንያታዊ ሆኜ ማስረዳት እንደምችል ያስቡ ነበር፡፡ ዛሬ ላይ ሆኜ ያንን ምክር ለለገሱኝ ሰዎች ከፍተኛ ምስጋና አቀርባለሁ፡፡
ጥያቄ፡- ቃለ መጠይቁን በትዕግስት ስላከናወኑ አመሰግናለሁ፡፡ ይህም ይመስለኛል የዓለማችን እጅግ ዝነኛው የእግርኳስ ዳኛ ያደረጎት…
መልስ፡- ሀቁን እንድናገር ይፈቀድልኛል?
ጥያቄ፡- በትክክል፡፡
መልስ፡- ቃለ መጠይቁ ቀላል አልነበረም፡፡

Previous Story

ድምፃዊ ጃኪ ጎሲ ሚኒሶታ ገባ፡ “የተወራብኝ ሁሉ ውሸት ነው፤ ቅዳሜ እስከምዘፍን ቸኩያለሁ”

Next Story

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ምትሃታዊ ማጭበርበር ተፈጽሞብናል ያሉ ደንበኞች ቅሬታ አሰሙ

Go toTop