ዕለቱ በታሪክ ውስጥ፡ ልክ ዛሬ ግንቦት 13 መንግስቱ ኃይለማርያም ሃገር ጥለው ወጡ፤ የሻለቃ ደመቀ ባንጃው ገድል

May 21, 2014

ከጌታቸው ሽፈራው

ልክ በዛሬው ቀን ግንቦት 13/1983 ዓ.ም መንግስቱ ኃይለማሪያም ብላቴና ማሰልጠኛን እጎበኛለሁ ብሎ ናይሮቢ ገብቷል፡፡ ከዚያም ወደ ዚምባብዌ ለመሄድ እየተሰናዳ ነው፡፡ በዚህ ወቅት መንግስቱ ሊሰደድ መሆኑን ሳያውቁ አጅበውት የሄዱት ኢትዮጵያውያን ሁለት አማራጮች ቀረበላቸው፡፡ ከመንግስቱ ጋር ወደ ዚምባብዌ ማቅናት አሊያም ወደፈለጉበት ሌላ ዓለም ለመሰደድ ‹‹መልካም አጋጣሚ›› እንዳላቸው፡፡ ያኔ ወታደሮቹ በኃይለስላሴ መንግስት ላይ ሲያሴሩ ለወታደሮቹ ሾፌር ሆኖ፣ ስልጣን ከጨበጡ በኋላ ደግሞ የመንግስቱ ጠባቂ የነበረውና ኬንያ ድርስም አጅቦ ያደረሰው ሻለቃ ደመቀ ባንጃው ግን እነዚህን አማራጮች አልቀበልም አለ፡፡ እሱ ሶስተኛ አማራጭ አለው፡፡ ወደ እናት አገሩ ተመልሶ በጠላት እጅ መሞት!

እሱ ለራሱ ‹‹እኔ ወደ አገሬ እመለሳለሁ!›› አለ፡፡ በእርግጥ በዛ ቃውጢ ወቅት መንግስቱም ሆነ ሌሎች ናይሮቢ የሚገኙት ይህን ለማመን አቅቷቸው ሊሆን ይችላል፡፡ ደመቀ ግን አደረገው፡፡ ‹‹በዚህ እድሜዬ አገሬን ጥዬ አልሰደድም፣ አገሬ ውስጥ አሞታለሁ፡፡›› ብሎ ተመለሰ፡፡ ለእኔ ጀግና ማለት አገሩ በጠላት ተይዛም ቢሆን ሞትን መርጦ የሚመለስ የቁርጥ ቀን ልጅ ነው፡፡

ደመቀ ይህን ውሳኔ ሲወስን አዲስ አበባ በገንጣዮቹ እንደምትያዝ፣ እነዛ ለኢትዮጵያ የማያስቡ ጠባቦች እንደሚያስሩት፣ እንደሚያሰቃዩትና እንደሚገሉት በደንብ ያውቀዋል፡፡ ይህም ሆኖ ‹‹ቆራጡን መሪ›› ትቶ ለሚወዳት አገሩ ነፍሱን ሸጦ ተመለሰ፡፡ እናም ታሰረ፡፡ እስር ቤት ውስጥም ሞተ፡፡ በዚህ እስር ቤት ውስጥ የደረሰበትን ስቃይና መከራ እሱ እግዚያብሄር ይወቀው፡፡ የህሊናውን እዳውን ግን ተወጥቷል፡፡

ደመቀ ባንጃው ሲጠብቀው የነበረው መንግስቱ ‹‹አንድ ጥይትና አንድ ሰው እስኪቀር እንዋጋለን›› ብሎ ነበር፡፡ ደመቀ ባንጃውና ሌሎች ጠባቂዎቹ ሳይኖሩ ራሱ መንግስቱና አንድ ጥይት እስኪቀር መሆኑ ነው፡፡ መንግስቱ ይህን አላደረገውም፡፡ ደመቀ ግን መሳሪያውያና ጥይቱንም አስረክቦ ባዶ እጁን ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰ፡፡ ለእኔ የአገር ፍቅር ማለት ይህ ነው፡፡ በዚህ ዘመን ስንቱ እምቦቀቅላ ልጆን ሳይቀር ጥሎ ይሰደዳል?

እርግጥ ነው ደመቀ አምባገነኑን መንግስቱ ኃይለማሪያምን ሲጠብቅ ኖሯል፡፡ እርግጥ ነው ደመቀ ደርግ ሲጨፈጭፍ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ አብሮ ጨፍጭፏል፡፡ ግን ግን ለእናት አገር ነፍስን ከመስጠት በላይ ምን ጀግንነት አለ?

አሁንም ድረስ መሪዎች፣ ፖለቲከኞችና ሌሎችም ትልቅ ተፅዕኖ ያላቸው ኢትዮጵያውያን ሲያወሩት የነበሩትን ረስተውት አገራቸውን ጥለው ይሰደዳሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ ልክ እንደ ደመቀ ባንጃው ናቸው፡፡ እዚህ ጋ ተመስገን ደሳለኝ ምሳሌ ሊሆን ይችላል፡፡ በአንድ ወቅት ‹‹ይህ አገር የማን ነው?›› ብሎ የጻፈ ጋዜጠኛ በነጋታው ሲሰደድ ማየት የተለመደ ሆኖ ነበር፡፡ ተሜ ‹‹ይህ አገር የማን ነው?›› ብሎ በጻፈበት ወቅት በርካቶች ‹‹በቃ ተሰደደ!›› ብለው አዝነው ነበር፡፡ እሱ ግን ‹‹አገሩማ የእኔ ነው፡፡ አልሰደድም!›› አለ፡፡

ደመቀ የአገር ፍቅር ተምሳሌነት ነው፡፡ ደመቀ ‹‹እኔ አገሬን ጥዬ አልሰደድም፣ አገሬ ሄጄ እሞታለሁ!›› ሲል ‹‹አንድ ጥይት፣ አንድ ሰው!››ን ሲፎክር የነበረው መንጌ እንዴት አፍሮ ይሆን? መሪ በመርህ የሚቆም፣ ያለውን የሚፈጽም ነውና ለእኔ ከመንጌ ይልቅ ደመቀ መሪ ነው፡፡ ጅግናዬም እሱው
ሻለቃ ደመቀ ባንጃው ነው!
ለአገራቸው ውድ ነፍሳቸውን የገበሩ ሁሉ ዘላለማዊ ክብር ይገባቸዋል!!!

Previous Story

ቴዲ አፍሮ፣ ጃኪ ጎሲ፣ ሸዋንዳኝ ኃይሉ እና ሚካኤል በላይነህ በኢትዮጵያውያኑ እግር ኳስ ጨዋታ ሳንሆዜ ላይ ሥራዎቻቸውን ያቀርባሉ

Next Story

ሱዳን ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያውይን ስደተኞችን በተመለከተ የተጠናቀረ 3 ኛ ጹሁፍ ነው ።

Go toTop