የሃይማኖት መሪዎች የፀሎትና የሰላም ጥሪ 

February 7, 2025

የኢትዮጵያ የሃይማኖት መሪዎች ለመንግሥት እና ታጣቂዎች የሰላም ጥሪ አደረጉ። የሃይማኖት መሪዎቹ ይህንን የሰላም እና የጸሎት ጥሪ ያደረጉት የኢትዮጵያ ሲቪል እና የሙያ ማህበራት ኮንግረስ ባዘጋጀው መድረክ ላይ ነው። ትናንት ጥር 29 ቀን 2017 ዓ.ም አዲስ አበባ ውስጥ በተደረገው የሰላም ጥሪ “ጦርነትም፣ ደም መፋሰስም ይብቃ” የሚሉ መልዕክቶች ተላልፈዋል።  መንግሥት ስለ ድርድር እና ውይይት በተደጋጋሚ የሚያቀርበውን ጥሪ ወደ ተግባር እንዲለውጥ እና የትጥቅ ትግል ውስጥ ያሉ ተዋጊዎችም ወደዚህ ዓላማ እንዲገቡ ተጠይቀዋል።

ይህንን የሃይማኖት መሪዎችን የፀሎት እና የሰላም ጥሪ ጉባኤ

ያዘጋጀውየሃይማኖት ተቋማትን ጨምሮ 51.3 ሚሊዮን አባላት እንዳሉት የገለፀው የኢትዮጵያ ሲቪል እና የሙያ ማህበራት ኮንግረስ ነው። በዚሁ ሥነ ሥርዓት የክርስትና እና እስልምና ሃይማኖቶች መሪዎች ኢትዮጵያውያን ወደሰላም እንዲያማትሩ፣ ይህንንም እንደየ ዕምነታቸው በፀሎት ጭምር እንዲያጠናክሩ ተማፅነዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፈጣሪ “በምድራችን ላይ በምናደርሰው የተዛባ ተግባር በጐርፍ፣ በድርቅ፣ በመሬት መንቀጥቀጥና በዓየር መዛባት እየገሠጸን እንደሆነ ማስተዋል አለብን” ሲሉ ተናግረዋል። ምዕመኑ በጾመ ነነዌ ከየካቲት 3 ጀምሮ ለሦስት ቀናት በንስሃ፣ በጸሎትና ምህላ የእግዚአብሔርን ምህረት እንዲለምን ሲሉም ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼህ ሐጂ ኢብራሒም ቱፋ “በየመድረኩ በየቀኑ ሰላምን ሳንሰብክበት ያለፍንበት መድረክ አልነበረም” በማለት  የጎደለን ነገር ተግባር ነው ብለዋል። “መንግሥት ለሰላም፣ ለድርድርና ለንግግር በሩ ክፍት እንደሆነ እንሰማለን፣ እናያለን። ይህንን ወደ ተግባር እንዲያገባ” ሲሉ የጠየቁት ቬህ ሐጂ ኢብራሒም ለታጣቂዎችም ቢሆን “ዜጎቻችን ተበድለዋ፣ እየተበደሉም ነውና ኑ እንታረቅ” የሚል ጥሪ አድርገዋል።

 

የሃይማኖት መሪዎች የፀሎትና የሰላም ጥሪምስል Solomon Muche/DW

ብፁዕ ካርዲናል ብርሃን ኢየሱስ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስትያን ሊቀ ጳጳስ በበኩላቸው “ጦርነት ይብቃን። ደም መፋሰሱ ይብቃን። ወንድም በወንድሙ ላይ መጨከኑ ይብቃ።” በማለት ተማጽነዋል። በዚሁ ትናንት በተከናወነ የሰላም ጥሪ መድረክ ላይ ቄስ ደረጄ ጀምበሩ የኢትዮጵያ ወንጌላዊ አማኞች ቤተ ክርስትያን ዋና ጸሐፊ “ደም ሊፈስ በፍፁም አይገባም። ሊታሰብም አይገባም። ምክንያቱም አንዳንችን ላንዳችን እናስፈልጋለ። ገዳይ ሟች የእኛው ነው” ብለዋ።

ሰለሞን ሙጬ

አዜብ ታደሰ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Previous Story

በአቃቢ ህግ በክስነት የቀረቡ አንዳንድ ጉዳዮች ላይ ለተከበረው ችሎት ማብራሪያ መስጠት አስፈላጊ ሆኖ ስላገኘሁት ክቡራን ዳኞች እንዳቀርብ ትፈቅዱልኝ ዘንድ በአክብሮት እጠይቃለሁ።

Next Story

 የአማራ ህዝብና ምሁራኑ በአብይ አህመድ ታጣቂ መታረድ  እናወግዛለን

Go toTop