በሤጣን ፈረሥ እየጋለቡ ግፍ መሥራትን የተዋህዶ ልጆች ይቃወማሉ

February 8, 2023

 በሤጣን ፈረሥ እየጋለቡ ግፍ መሥራትን የተዋህዶ ልጆች ይቃወማሉ ። ያውም እንደ አቡነ ጴጥሮስ በመሰዋትነት ።

 ጮራ እንዲሆነን ይኽንን ግጥም ከባለቅኔው ተዋስኩ ።

( ወልደ  ትንሣኤ ፤ የክርስትና ሥሜ ነው ። ሃሌሉያ )

       እንደሰዶም

ሞኝ አንግስ ተግቶ እንደሰከረ ፤ ፍቶት አናቱ ላይ ወጥቶ

የሚያደርገውን አሳጥቶ

ያለአባት አዳሩ ሲያወራጨው

መለኮት መቅሰፍት አውርዶ ፣ የሰው ልጅ በንፍር ውሃ

ሟምቶ ሲቀልጥ እንደ ጨው

የነገሩ ምላሽ የጥፋቱ ቁርሿ ፣ የቅጣቱ ውርጅብኝ …

ሂድበት ነው ሂጂብኝ

በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ምኑም ምናምኑም እየተወተፈ

ንውር እንደጓሮ አይደርቄ ጎመን ፣ ባዋጅ እየተከተፈ

አለም በቃኝ በራሱ ፈርዶ

ከፈንኳ ሳይበቃ ፤ መቀመቅ ገባ ተዋርዶ

ምን ግድ አለው ፣ ዲበ ኩሉ ፣ የፍትህ አምላክ እንጂ እሱ

ለሰውማ ራሱ ነው ዋሱ …ልቡ ያመለከተውነው ፣ ምሱ

ለአብነት አነሳሁት እንጂ ሰዶምና ጎሞራን

ጉዳዬ ከሰሜን ተራራ ልጆች ነው

እንድርጭት በስለው ፣ እንደባጩት ተሰደው

ያስከበሩት ደን አሞራን

ከጀምበር  መፍለቂያ ከፅዮን

ከቅኔ ቤት መሪጌታ …ኤዶንን እንደመቀነት

እሰከአቀፋት ግቢ አግዶ ጊዮን …

አለት እንደ በቆሎ እሸት ፈልፍለው

ቤተ መቅደሳቸውን ንሰው

በፍቅርና በትህትና ተጋርተው

ሞኝ ባያፍር ዘመዱ ያፍር ብለው

ቁልቁል እንደ ጅራተፍየል ፣ ይጠበቃል ማዕረጉ …

ነገርን በወግ መርምሮ

ቢሆን ሎሚ ለሁለት አስታርቆ

እንደ እራስ ፈርዶ…በቃ ጠብ በቃ ብሎ

በሃሌ በማሳረጉ እንጂ…

ዳኛ ፊት ማን ያደርገው ነበር ባለሟል

ለሱእንጂ ሰግሮ ሰማ  ችሎት  ፣ ለሱእንጂ ለማ ተሰይሟል

ከሳሽና ተከሳሽማ ግራና ቀኝ ነው መቆሚያቸው

ምሶሰው … ቢሻው ከጭንቅ ሊያወጣ

ቢሻው ሊያዳፍን …ምሶ ነው ።

ብቻ በቃን ፤

ኢትዮጵያ እጆቿን የዘረጋችው ዛሬ ነው

ሌላም ጊዜ ከአምላኳ ጎን አትለይም

የአሁኑ ግን ቁርጥ ነው

የትውልድ ጥንድ ምጥ ነው ።

ሞት አንገት ላይ ደረሰ …ማህተምን ሊፈታተን

እኛው ቤት እምቦሳ ብለን ያደምነው

እልፍኛችንን ከፍተን

……………………..

ገፅ ( 58  _59 )

ይኽንን የባለቅኔውን የሙሉጌታ ተስፋዬን ( ኢትዮጵያዊ ሊቅ ) ግጥም  ለአንባቢ ሳቀርብ ፣ የዘመኑ ፖለቲኮኞቻችን ፣ ይልቁኑም አንዳንድ ፣ የአበልፃጊው መንግስት  ፣ በተዋረድ ያሉ ህግ አስፈፃሚዎች ፣ በሤጣን ፈረስ የሚጋልቡ በመሆናቸው  ፤ ይህ ድርጊት የሶዶምና የጎሞራ ሰዎች ድርጊት መሆኑንን ለማሳሰብ ነው ። እነዚህን ሐጢያተኛ እና ወንጀለኛ   ግለሰቦች ገዢው ፖርቲ በጊዜ   ገለል   እስካላደረጋቸው ድረስ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ጨምሮ ፣ ዜጎች በአጠቃላይ  ፣ ሽንት ቤት ውስጥ ከተሰቃዩት አባት የባሰ ውርደት እንደሚያጋጥመን ፤ እየተቀጣጠለ ያለውን እሣት አሥተውለን በቀላሉ መረዳት አያዳግተንም ።

መንግስት ውስጥ ያሉ ፣ ፈሪሃ እግዛብሔር ያላቸው ባለሥልጣናት ( በሲቪሉም በወታደሩም )   በተረጋጋ አእምሮ  እዛም ቤት እሣት እንዳለ ተረድተው ግን ፣ ዛሬ መላውን ኦሮሚያን የወረሯት ሤጣናት  እጃቸውን ከጥፋት  በአፋጣኝ እንዲሰበስብ ካለደረጉ እነሱም የሎጥን ሚስት እጣ ፈንታ ያገኛሉ ። የሐጢያቱ ተባባሪነታቸውን በተግባር አስመስክረዋልና !..

የህዝቡን አንድነት በኃይል እየናዱ “ አንድነት ፖርክ “ በማለት አራት ኪሎ ላይ ታላቅ የቱሪስት መሥህብ የሆነ ሥፍራ መገንባት ፤ “ የወዳጅነት አደባባይ “ በማለት ሰው የሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ በመፈቃቀር እንዲኖር እንፈልጋለን ማለት ፣ በተግባር ግን አባቶቻችን በደምና በአጥንታቸው የገነቧትን መናድ ፤  “ እዛም ቤት ያለው እሣት በሌሎች ላይ ጉዳት እንዲያደርስ መገፋፋት ነው ። ይኽ ደግሞ የሞኝ ድርጊት ነው ። በእሣት የሚጫወት ብልህ የለምና ! ደግሞም ፣  በአጋጣሚ በኮስ አበደች  ፖለቲካ ፣ ሥልጣን እንዳገኛችሁ ና በመልካም አንደበታችሁ ፣ በቃላችሁ የዜጎችን ይሁንታ እንዳገኛችሁ አትዘንጉ ።  በህዝቡ ውስጥ እልፍ ባለአእምሮዎች እንዳሉም ተረዱ ። በማሰበ ፣ በዕውቀት ፣ በችሎታ ፣ በሥርዓት ፣ በጨዋነት ሺ ጊዜ የሚያስከነዷችሁ በህዝብ ውስጥ አሉ ። ውሸት ይብቃችሁ ።  አገር መውደድ ፣ ዜጎችን በማክበር በተግባር  የሚገለጥ እንጂ ቋንቋን በማምለክ በቃላት የሚታይ እውነት አይሆንም ።  እምነትም ቁርኝቱ ከሁሉን ቻዩ አምላክ ጋራ እንጂ ከቋንቋ  ጋር አይደለም ።  እግዚአብሔር ለቋንቋ ና ለነገድ አይገደውም ። እግዛብሔር  የሚገደው በአምሳያው ለፈጠረው ሰው ሁሉ ነው ። ቀይ ፣ ጥቁር ፣ ነጭ ፣ ቢጫ  ፣ጥይም መልክ ይኑረው ፤ ኦሮሞ ፣ አማራ ፣ ትግሬ ፣ ሱማሌ  ወዘተ ።  ” ነኝ  ፤ ብሎ ቢገበዝም ፣ ቅጣቱ የናቡከደናፆር አይነት እንደሚሆን ከወዲሁ እወቁ ። በእናንተ ባይደርስ በልጆቻችሁና በልጅ ልጆቻችሁ እንደሚደርስ እወቁ ። ሁላችንም የእግዚአብሔር የእጁ ሥራ ነን ። በእግዛብሔር ፊትም ሁላችንም እኩል እንደሆንን ኢየሱስ ክርስቶስ በወጉ አስተምሮናል ።

ይኽንን የኃይማኖት አውነት የኃይማኖት ትምህርት ማስተማሪያ ኮሌጅ ውስጥ  ገብቶ ያልተማረ ህኖም ግን ከህፃንነቱ ጀምሮ  በክርስቶስ  ሥቅለት ፣ ሞት እና ትንሣኤ … በብሉይ ኪዳን እና  በሐዲስ ኪዳን ትምህርት ቤተ ክርስቲያን በመመላለስ፣ አእምሮውን ያበለፀገና ቀፈጣሪው ፍቅር የበለፀገ አእምሮ ያለው  ሁሉ  ጠንቅቆ ያውቃል ።

እንሆ ዛሬ ይኽንን ጠንካራ እምነታችንን ለማስካድ ፣ ሤጣን  አንገታችን ለማነቅ እየተገዳደረን ነው ።  …ማህተባችንን ለማስወለቅ እየተናነቀን ነው ። ሰዶምን እንዳንሆን  ግን የሰዶማውያንን  ፀያፍ እምነት በብርቱ ልንዋጋ ና ልጆቻችንን ከጥቃቱ ልንከላከል ይገባናል ። ይኽ ግጥም የዛሬውን ዱብ ዕዳ ፣ ከትላንቱ የመቅሰፍት ዱብዳ ጋር ያመሳሰለ ነው ።

 

ሙሉጌታ ተስፋዬ  ” የባለቅኔ ምህላ ” በተሰኘ የግጥም መፀሐፉ ፣ ለዛሬና ለነገው ትውልድ የሚበጅ ዕውቀት ፣ ትቷልን አልፏል ። በንፁህ ልቡም በገነት ይኖራል።  ሙሉጌታ ተስፋዬ ፣ ለኢትዮጵያዊያን የኢትዮጵያዊነትን ሥሜት በልባቸው ለማበልፀግ የሚበቃ ጥበብን የተጎናፀፈ ባለቅኔ ነው ። …

ሙሉጌታ ተስፋዬ ( ጀግና ባለቅኔያችን ) ለኢትዮጵያዊያን ፣ ቅኔያዊ መልዕክቱ ፣  ዛሬ በእጅጉ ያስፈልገናል ።  አዎ ፣ እምነታችን በመናፍቃን የተደፈረበት ፣ አብያተ ክርስቲያናችን ቅጥር ውስጥ መፀሐፍ ቅዱስ የያዙ ክርስቲያኖች በሴጣን ደማቸው እንደጎርፍ የፈሰሰበት  እጅግ አሳዛኝና አሳፋሪ ጊዜ ላይ ደርሰናል  ። ይኽ የሚጠቁመን ምድራችን በከፊል እንደሰዶምና ገሞራ አይነት ሰዎች መሞላቷን ነው ። ለስጋቸው እንጂ ለነፍሳቸው ደንታ በሌላቸው ።

ዓለምን የፈጠራት መድሃኒዓለምን የካዱ ፣ ምንም አያመጣም ያሉ ፣  በመሳሪያ ( በሴጣን ኃይል ) ታጅበው የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን ሊያፈርሱ ብቻ ሳይሆን ክርስትናንን ዓለማዊ ለማድረግ ተነስተዋል ክርስትና የመጣው ከፈጣሪያችን ነው ።   ለክርስትናችን ለክራችን ለማተማችን ደስ እያለን እንሞታለን ። ትላንት አቡነ ጴጥሮስ ደስ እያላቸው ሞተዋል  ። ከሳቸው በኋላም በመላው ኢትዮጵያ ሥለ ክርስቶስ ፍቅር በፋሺሽስቶች የተገደሉ  መሰዋት የሆኑ በሺ የሚቆጠሩ ናቸው ።

ለመሆኑ ለአምሥት አመቱ ተጋድሎ እና ለነፃነታችን ፋና ወጊ የሆኑት ፣ ዋና ተዋንያን  ፣ በዛን ዘመን ፣ ህዘበ ክርስቲያኑ ለፋሺስቱ የኢጣሊያን መንግስት እንዳይገዛ ገዝተው ፣ በኢጣሊያን  መትረየስ የተሰው ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ፓትርያርክ  አቡነ ጴጥሮስ አይደሉምን ? ( የታላቁን ደራሲ ና በለቅኔ የሎሬት  የፀጋዬ ገ/ መድህንን “ ጴጥሮስ ያቺን ሰዓት ግጥም ያነቧል ። )

የዛሬ ባለሥልጣን ሁሉ ሟች እና ኃላፊ ነው  ። ከሞት አያመልጥም ። ጥይት ባይገለው ፣ ባዮሎጂ ወይም ድንገተኛ አደጋ ይገለዋል ። እንደ ሁሉም ሰው   ባለሥልጣናትም ሆኑ ኃያለን ነን  ባዮች  በጊዜያቸው ከዚች ምድር ይሰናበታሉ ። ዛሬ በሥሜት ወይም በብሽቅ ፖለቲካ ጠላቴ ያልከውን ሥለገደልክ ሞት ለአንተ የሚቀርልህ እንዳይመስልህ ! ሞት   ሁሌም በህይወት ካለ ሰው ጋራ የሚጎዝ ነው ። … ፈጣሪ በቃ ሲለን እስትንፋሳችን ይቋረጣል ።

ይህ እውነት ቢሆንም እውነቱን ለመቀበል የታወሩ  ፣  የፈጣሪያችንን ኃያልነት የካዱ ፣  ፕለቲካውን ለማጦዝ እንደቻልነው ፣  ሰማያዊውን መንግሥት እናጦዘዋለን ብለው የሚያስቡ ( ልክ እንደሴጣን )   በዚች ቅድስት አገር ዛሬና አሁን ለፈጣሪዋ ለመድሃኒዓለም ባደረችው ቤተክርስቲያን ጉያ ውስጥ መፈጠራቸው  በእጅጉ ያሳዝናል ።  ሰው ዓለም በቃኝ ብሎ እንዴት የዓለም ና የሥጋ ፍቃዱን ለማሳካት ጦር ይሰብቃል ? ያውም ፀረ ክርስቶስ በሆነው ማርክሳዊ ህሳቤ ውስጥ ተወሽቆ ?!

በእውነቱ ፕለቲከኞቹ ሳይሆኑ የክርስቶስ ልጆች የሆኑ ፣ ሆኖም ግን በሥጋ ምኞት ተጠልፈው ፣ ሥጋ ና ክፉ መሻቱ አሸንፏቸው ፣ ከእዚህ ዓለም ገዢ ጋር ተባብረው ለመስራት የወሰኑ ከቤተክርስቲያኗ ያፈነገጡ አባቶች ናቸው ጥፈተኞች  ። እነዚህ ጥፋተኝች ላይ አንድ የሆነችሁ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ውግዘት ማስተላለፏ ይታወቃል ። ክህነታቸውን ገፋ አቶ እንዲሰኙ አውጃለች ። እነዚህ አቶዎች ዛሬም አባት ነን ብለው እየተንቀሳቀሱ ነው ።  ያውም  በዓለማዊ ፖለቲከኞች ታጅበው ። ይኽ  የሚያመለክተን በኢትዮጵያ ውስጥ የሚካሄደው ፖለታካ ማበዱን ነው ። ፖለቲካ የግለሰቦችን መብት ማስከበሪያ እንጃ   መጨቋኛ መሣሪያ ያለመሆኑ ይታወቃል ። መንግሥትም ሞራል ያለው እንዲሆን የፖለቲካ ሣይንቲስቶች ከጥንት ጀምረው መክረዋል ።  ፖለቲከኞቻችን ፣  በራሳቸው ላይ ሊደረግ የማይፈቅዱትን  ፣ “ ሥልጣን በእጃችን ነው ። “ በማለት ግፍ ባይሰሩና ጡር ለልጆቻቸው ባያቆዩ መልካም ነው ። ደግሞም በእሣት መጫወት ደጋፊ አያስገኝም ። እሣት ፣ እሣት ጫሪውን እንኳ አይምርምና ! በእሣት  መጫወት  አገርን ያፈርሳል  እንጂ አይገነባም ።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Previous Story

የሻሸመኔ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ የነበሩት ቄስ ሀረገወይን አርፈዋል፡

Next Story

በደም የጨቀዬው የሳሪዮስ መስቀል

Go toTop