የቀጠለው ድርድር

June 2, 2022

መቀሌ ላይ ከህወሃት ሊቀመንበር ዶክተር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል ጋር የተነጋገሩት የአፍሪቃ ሕብረት ልዩ መልዕክተኛ የቀድሞው የናይጀሪያ ፕሬዝደንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ የጀመሩት የሰላም ጥረት «በጣም ዝግ ብሎ ሆኖም ሳይዛባ» ለውጥ እያሳየ መሆኑን ተናግረዋል። አሁን ያለው ሁኔታ ከስድስት ወር በፊት ከነበረው የተሻለ ነው ያሉት ኦባሳንጆ የሚያደርጉት እና ማድረግ አለብን ብለው የሚያምኑት መተማመንን የሚፈጥሩ ርምጃዎች መቀጠል እንደሚኖርባቸው መሆኑንም ለቢቢሲ አፍሪቃ በሰጡት ቃለመጠይቅ ገልጸዋል። በውይይታቸውም ያልተገደበ ነጻ የሆነ የሰብዓዊ ርዳታ አቅርቦት እንቅስቃሴ እንዲኖር፤ እንዲህ ያለው አቅርቦትም በሚፈለግበት በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል መድረስ እንዲችል፤ በሂደትም ቀደም ሲል የተወሰነውን ጥቃት የማቆም ውሳኔ ተከትሎም በድርድር የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ እንደሚፈልጉ መነሳቱን አመልክተዋል። የአፍሪቃ ሕብረት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ግጭት ከምር ወስዶታል ወይ በሚል የተጠየቁት ኦባሳንጆ፤ «ሰላም፣ ጸጥታ እና መረጋጋት በአፍሪቃው ቀንድ እንዲሰፍን እኔን በልዩ መልዕክተኛነት ስለሰየመኝ የአፍሪቃ ሕብረት ችግሩን ከምር እንደወሰደው ማሳያ ነው።» ነው ያሉት።

ለዚህም ሕብረቱን ማመስገን እንደሚገባም አመልክተዋል። የእሳቸው ሚና በተቀናቃኝ ኃይሎች ላይ ጫና ማድረግ ሳይሆን ያለውን ጫና ተመልክተው በየራሳቸው ወደ ጦርነት ሳይሆን ያንን የማቅለል ርምጃ እንዲወስዱ ማበረታታት መሆኑን የተናገሩት ኦባሳንጆ በህወሃት እና በፌደራል መንግሥት መካከል የሰላም ስምምነት ሊፈረም የሚችልበትን ጊዜ አሁን ለመግለጽ እንደሚቸገሩ ገልጸዋል። እንዲያም ሆኖ በሂደቱ ስኬቶችን እያስመዘገቡ በመቀጠል አሁን ያለው የሰብዓዊ ተኩስ አቁም ውሳኔ በድርድር ወደ ሚደረሰው የተኩስ አቁም እንዲሄዱ እንደሚፈልጉም ተናግረዋል።

ይኽ ስምምነት ደግሞ በይፋ ጸብን አስቁሞ በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች ትግራይ ክልልን ጨምሮ አገልግሎቶችን ወደ ነበሩበት የመመለስ እንዲያደርስ እንደሚጠበቅም አመልክተዋል። ይኽ በእንዲህ እንዳለም የአፍሪቃ ሕብረት ልዩ መልዕክተኛው ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ በዛሬው ዕለት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከሚመራ የባለሥልጣናት ቡድን ጋር በመሆን ባሌ ሮቤ መግባታቸውን ኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የኮምዩንኬሽን ቢሮ አስታውቋል። በዚህ ጉዞ ከኦባሳንጆ ሌላ በኢትዮጵያ የዓለም ባንክ ዳይሬክተር ኡስማን ዲዮን፣ የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ እና የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝደንት ሽመልስ አብዲሳ ከተካተቱት ባለሥልጣናት እንደሚገኙ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Previous Story

ተቃዋሚው የአፋር ህዝብ ፓርቲ በብሔራዊ ምክክር ላይ ለመሳተፍ እንደሚቸገር አስታወቀ።

Next Story

“… አላውቅም ! የወንድሜ ጠባቂው እኔ ነኝን … ? ” ባዮቹ ፤ ቃየንአዊያን እና ባቢሎናዊያን አኛ  አይደለንምን? – መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ

Go toTop