መጥፎው ታሪካችን እንዳይደመር ፤ ጥያቄዎቼ በአግባቡ ና በአፋጣኝ ይመለሱ – ሲና  ዘ ሙሴ

ኢትዮጵያ  ከምኒልክ ሞት በኋላ የሥልጣን ሹክቻ እና የሤራ ፖለቲካ  እንደጀመራት በታሪክ ተመዝግቧል ። ኢያሱ ና ዘውዲቲ በአንድ በኩል ተፈሪ መኮንን በሌላ ጎራ በሤራ ፖለቲካ  ተጠምደው  እንደነበር  ታሪክን አንብቦ መረዳት ይቻላል።  ከዛም ለጥቂት ወራት ዘውዲቱ ለጥቂት ወራቶች ኢያሱ ነግሠው ኢትዮጵያን አሥተዳድረዋል ። ለረዥም ዓመታት ደግሞ ፣ ተፈሪ መኮንን “ ቀዳማዊ ኃይለሥላሤ ፤ “ ተብለው ፈላጭ ቆራጭ ንጉሥ ሆነዋል ።

ቀዳማዊ ኃ ሥላሤን ፣ የሥልጣን ጥም  በዘግናኝ ና በአሣፋሪ ሁኔታ እንዲሞቱ አደረጋቸው ። ባይንገዛገዙና ለወታደሩ የተለየ ጥቅምና ጉርሻ በመሥጠት ፣ ቀልቡን ወደእሣቸው በመመለሥ የመለዮ ለባሹን እንቅሥቃሤ ቀልብሰው ጦሩን ወደ ከምፑ ቢመልሱት ኖሮ ወደ ወታደራዊ ጁንታነት ጦር ሠራዊቱ  አይቀየርም ነበር ። ከዛም እንደ እንግሊዝ ዓይነት ሞናርኪ በመፍጠር ፣ ከኢምፔሪያሊዝም ጉያ ተሸጉጠው  በሥርዓት ተከብረው የንግሥናውን ሥርዓት በአገር ሞገሥነት ማሥቀጠል  ይችሉ ነበር ። ኢትዮጵያም እንዲህ በእርሥ ፣ በእርሥ ጦርነት አትታወክም ነበር ።  ያውም የአማራ፣ የትግሬ፣ የኦሮሞ ፣  የደቡብ  እየተባለች ፤  የሌሎች 80 ቋንቋ ተናጋሪ ፈጣሪ ወይም እግዚአብሔር ለነብቻቸው ያለ ይመሥል ፤ ሰውነታቸውን በመርሳት ለመጠፋፋት ፣ በየፊናቸው በአሥጠሊ መልኩ ለሠለጠነው ዓለም በመታየት እና መሣቂያና መሣለቂያ በመሆን ።

በኢትዮጵያም ሆነ በአፍሪካ ያለው ታላቅ ድንቁርና  ሰው ፍጡር ና ዛሬ ወይ ነገ ሟች መሆኑን መዘንጋት ነው ። ሰውነትን ያለማወቅና ለመብል ብቻ ብሎ ሰው ሥጋ ለባሽነቱን የመዘንጋት አባዜ በአፍሪካ  መንግሥት ሹማምንት  ላይ በሥፋት ተሠራፍቷል ።   በአፍሪካ ውሥጥ ሰዎች የመንግሥት ቁንጮ ኃላፊ ሢሆኑ በእውነቱ ራሣቸውን እንደ እግዜር ወይም እንደ ዓለም ፈጣሪ ይቆጥራሉ ።  በዚህ የተነሣም ሥልጣኑንን በይሁንታ ና በዝምታ የሰጣቸውን ህዝብ ና ህዝቡን የፈጠረ እግዚአብሔርን ይዘነጋሉ ።  (በበኩሌ ከሞት በኋላ የሚያጋጥማቸውን ቅጣት የማይፈሩ ብቻ ሣይሆኑ በፈጣሪ መኖር ፤ ሥለገነት እና ገሃነም እምነት ያላቸው አይመሥሉኝም ። )

መንግሥት ተቋም እንጂ ግለሰብ አይደለም ። መንግሥት መንግሥትነቱ የሚወደውም ሆነ የሚጠላው ተቋማቱ ለህዝቡ በሚሠጡት አገልግሎት ነው ። አሁን ጥያቄ የሀገሬን መንግሥት  ልጠይቅ ። ማለትም ተቋሙን ።  በእርግጠኝነት ተቋም እንጂ ግለሰብና ጠመንጃ በዚች አገር እንዳሻቸው ፣ አይፎልሉባትም ከተባለ ዘንዳ … ጥያቄ አንድ ፣ መናገር ተፈጥሯዊ አይደለም ወይ ?ጥያቄ ሁለት ፣ አንድ ሰው ያሰበውን ውሸትም ሆነ እውነት የመፃፍ መብት የለውም ወይ ?

ጥያቄ ሦሥት ፣ አንድ ተናጋሪ ወይም ፀሐፊ ጠቅለል ያለ ፣ ራሱ ሥርዓተ መንግሥቱ በሚከተለው የመላውን ኢትዮጵያ መብት የጣሰ ቋንቋዊ የፌደራል ሥርዓት ላይ የራሱን እና የሌሎችን ሃሣብ ደምሮ ፣ ቢፅፍና ቢናገር ምንድነው ነውሩ ??

ጥያቄ አራት ፣  የአገሬ መንግሥት በለውጡ ማግሥት የገባውን ቃል ችላ በማለት ፣  ዛሬ በሰው ዘር በሙሉ ውጉዝ የሆነውን ሰውን እንደ ቀበሮና  ጅብ የሚከፋፍለውን  የከረረ የጎሣ ሥርዓት በበለጠ አጠና ሮ ለመቀጠል ለምን ተነሣ ?

ጥያቄ አምሥት ፣ የአማራ ክልል ና ህዝብ የበለጠ ወደ ጎሠኝነት የገባው በዚህ አራት አመት ውሥጥ አይደለም እንዴ ?

ኦሮሞ ፣ አማራ ፣ ትግሬ ፣ ተብሎ ሰው በጎሣው የሚጮኽለት ብቻ ነው እንዴ ኢትዮጵያዊ ? ካልሆነ ይህ የጎሣና ቋንቋን ያማከለ ሥርዓተ መንግሥት ቢቀር ምን እንጎዳለን ? (በእርግጥ በቋንቋ የሚነግዱ ፣ ከሞታቸው በፊት ያለዘሩትን በማጨድ በመንቀባረር የሚኖሩ ይኽ የቋንቋ አገዛዝ እንዲቀር አይፈልጉም ። ሆኖም ለአንድ ምሥኪን አርሶ አደር ፣ ላብአደር ፣ የከተማ ነዋሪ ፣ የመንግሥት ና የግል ተቀጣሪ ልዩ ልዩ ሙያ ያለው ሠራተኛ ፣ ወዘተ የአንድ አማራ ፣ የአንድ ትግሬ ፣ የአንድ ኦሮሞ ንግሥና ህይወቱን ከቶም እንደማይቀይርለት ያውቃል ። በግለሠብ ደረጀ የሚመጣ የመለ ህዝብ ዕደገት የለምና ። አንድ አማራ ቢነግሥ ለመላ አሜርኛ ተናጋሪ ጠብ የሚልለት ነገር የለም ።  እርግጥ ነው ዛሬ በቅንጥብጣቢ የሚደሠቱና ጮማ ለሚቆርጠው ጥብቅና የሚቆሙ ሰው መሆናቸውን የዘነጉ “ ጎሣው ነን “ ባዮች መኖራቸው ይታወቃል ። እነዚህ ሰዎች በእርግጠኝነት ልንገራችሁ አብይን በማጅራቱ ያሣሩዱታል ። የጃዋር ጫዎታ ይኽቺናት ። ፊኒሺንግን ማሣመር ይሉሃል ። ተመሥገንም ሆኑ ሌሎች ጋዜጠኞች መንግሥትን አንቂ ፣ ከሥህተት አራሚ ፣ መጪውን ጥፋት  አመላካች ናቸው ። የከረረ እና የመጠፋፋት በደም መንገድ ና አቅጣጫ የሌላ ጎሣ የበላይነት ለመሥፈን ግፋ በለው የሚሉት ባሃር ማዶ ያሉ ማህበራዊ አንቂዎችን በበኩሌ  እውነታችሁን ባውቅም ሰከን ብላችሁ አሥቡ እላለሁ ። በረከት ሥምዖንም እኮ ኢህአዴግ ከመሞቱ በፊት ፣ የመጣው አደጋ ሁላችንንም ከመብላቱ በፊት ከእኛ መሐል ዘራፊዎችን መንጥረን በማውጣት ከህዝብ ጋር እንታረቅ ። ብሎ ነበር ። ዛሬም ዘራፊዎችን የመደበቅ ፣ ወንጀላቸውን የመካድ አዝማሚያ እየታየ ነው  ። የዚህ ሁሉ ምሥኪን ህዝብ እልቂት በአልጠግብ ባዮቹ  ና በህሊና ቢሦቹ ፖለቲከኞቻችንየተከሰተ ነው ። ( አንዳንድ  መሣፍንት  የግዜው ባለሥልጣናት እኮ የሚፀዳዱ እንኳን እንዳይመሥለን ይፈልጋሉ ። ያው አዳርጋቸው ቀዳማዊ ኃ/ሥላሤን እንደ ዓምላክ እንደሣላቸው መሆኑ ነው ። እናም ከፕሬሥ ነፃነት አንፃር የኃብታሙንም ሆነ የኤርሚያሥን ንግግር አልቃወምም ። የጋዜጠኞች መብት ተሞጋች የሩሲያ ቴሌቪዢንን መዘጋት ተቃውሞ ጉዳዩን ወደፍርድ ቤት የወሰደው ከዚህ በተፈጥሮ ከታደለ  ሰብዓዊ  መብት አንፃር ነው ።  መንግሥት  ሁልጊዜም እንደ መንግሥት በተቋም ደረጃ ሥለ ተፈጥሯዋ ሰብዓዊ ሠብቶች ካላሠበ እና በግለሰብ እልህ እና ” ቆይ አሣየዋለሁ ፣ ደሞ እኔ ለዚህ አብቅቸው እንዴት ጠገበ ? ” በሚል ፊውዳላዊ ትምክህት የሚጋልብ ከሆነ ፤  በዝሆኖች መጣላት የሚጎዳው ሣሩ ነው ። እናም ህዝብ  በምሬት ተነሳስቶ ፣ አጥፊ የሆነ አካሄድ እንዲከተል ያደርገዋል ።ደሞም እሣት ላይ ቤንዚል  መርጨት እጅግ ጥፋት እንጂ የሚያመጣው ጥቅም ከቶም የለም  ። )

ጥያቄ ሥድሥት ፣ እውን ጠ/ሚኒሥተራችን አማካሪ አላቸው ወይ ? በበኩሌ ጠጋ ብሎ ጠረናቸውን አሽቶ “አፍንጫዎት ይገማል ።” የሚል አማካሪ ያላቸው አይመሥለኝም ። ዝርዝር ታሪኩን ትቼ ፣ በአጭሩ ተረቱን እንሆ ።

በእሩቅ ምሥራቅ  ተረት አንድ ንጉሥ ፣ አንድ ተራ እና የታወቀ ፈላሥፋ ሰውን ጠጋ ብለው ሲያጫውቱት የንጉሡ አፍንጫ ሸተተው ።  ያ ፈላሥፋም ወዲያውኑ “ንጉሥ ሆይ የአፍንጫዎት ግማት ሠነፈጠኝ ።” አላቸው ።  ንጉሡም በጣም ተገርመው ይኽንን እውነት ባለቤቴ እንኳን አልነገረቺኝም ። ይኽንን እውነት በመናገርህ በጊዜ ካለብኝ ህመም ታክሜ ለመዳን እችላለሁና አመሠግንሃለሁ ። ከዛሬ ጀምሮ በዚህ ቤተመንግሥት የቅርብ እረዳቴና አማካሪዬ አደርጌ ሾሜሃለሁ ። አሉት ። ከዚህ ተረት አንፃር አማካሪዎቻቸውን ቢገመግሙ መልካም ነው ።  እንደ መንግሥቱም ሆነ እንደ መለሥ በሃሰተኛ ሪፖርትም ሆነ በምላሥ ሽንገላ መታለል ይለባቸውም ። ( ማን ነበር ከመንግሥቱ ኃ/ማርያም ጋር ወደ ጋምቤላ ጉብኝት ሄዶ ” ይህ መሬት ለሥንዴ ይሆናል ወይ ” ብለው በሚሥገመገመው ድምፃቸው  ሲጠይቁ አፈሩን በጣቱ ዛቅ አድርጎ በመቅመሥ ” አዎ ይሆናል ። ጎድ ሊቀመንበር ። ” ያለው … በቀልድ ውሥደነዋል ።)

ጥያቄ  ሥድሥት ፣ እውነትን እሥከዘለዓለም መቅበር ይቻላል ወይ ? እንደው ረዘመ ብንል ፣   የዚህ መንግሥት  ከፍተኛ የሲቪልና ወታደራዊ ባለሥልጣናት ከሞቱ በኋለ የተደበቀው እውነት ሊወጣ እንደሚችል ዛሬ ላይ ሆነው መገንዘብ የዛሬዎቹ ባለሥልጣናት እንዴት ተሣናቸው ?

ጥያቄ ሠባት ፣ ቀላል  ና የመጨረሻ ጥያቄ። ከፍተኛና መካከለኛ የፌደራልና የክልል ባለሥልጣናት እንዲሁም ፣  የሰውን ላብ በመዝረፍ የከበራችሁ በሙሉ ፣  ዘወትር  የተሞላቀ ኑሮ  ሥለምትኖሪ ፣  በራቫ 4 ሥለምትምነሸነሹ ።  ወዘተ ።  ከተራው ህዝብ ፣ ከበረንዳ አዳሪው በሰውነት የምትበልጡ ይመሥላችኋልን ?

በመጨረሻም ለታሪክ ከጦቢያ መፅሔት ከየካቲት 1992  7ኛ ዓመት ቁ 7  ላይ ያንን ዘመን የማያሥታውሥ ፅሑፍ ጀባ ብያችሁ ፅሑፊን እቋጫለሁ ። ከሲና ተራራ አይደለም አንዴ ሙሴ አሥርቱን ትዕዛዛት ያወረደው ? እኔም ይህን ህግ ደጋግሜ ወደ ኢትዮጵያ መንግሥት እወረውረዋለሁ ። ጣዖታቱን ይበላቸው ዘንድ ።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Previous Story

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝን በተመለከተ

Next Story

በዘረኝነት የሚናጠው የመጅሊስ ቢሮን ለመቆጣጠር የኦሮሚያ መጅሊስ ሃጂ ሙፍቲን ከስልጣን አባረርኩ አለ

Go toTop