የ’ኤች አር 6600’ ረቂቅ ሕግን የሚቃወም ሰልፍ በሳን ፍራንሲስኮ ከተማ ተካሄደ

March 26, 2022

ኢትዮጵያዊያንና ኤርትራዊያን የተሳተፉበት ’ኤች አር 6600’ ረቂቅ ሕግን የሚቃወም ሰልፍ በካሊፎርኒያ ግዛት ሳን ፍራንሲስኮ ከተማ ተካሄደ።

ኢትዮጵያዊያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን እና ኤርትራዊያን የተሳተፉበት ሰልፍ የተካሄደው በሳን ፍራንሲስኮ የሕዝብ ቤተ-መጽሐፍት አካባቢ ነው።

እ.አ.አ በ2014 ሕይወቷ ያለፈው የአሜሪካ ገጣሚ ማያ አንጀሎ የመታሰቢያ ሥነ ሥርዓት በቤተ-መጽሐፍቱ የተካሄደ ሲሆን በዝግጅቱ ላይ የአሜሪካ ኮንግረስ አፈ-ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲና የአሜሪካ ኮንግረስ አባል ባርባራ ሊ(ካሊፎርኒያ) ተገኝተዋል።

ዳያስፖራው ይሄን አጋጣሚ በመጠቀም ’ኤች አር 6600’ ረቂቅ እንደሚቃወሙትና ባለስልጣናቱ ኢትዮጵያን እንዲሁም በኢትዮጵያና አሜሪካ መካከል ያለውን ግንኙነት የሚጎዳውን ሕግ ውድቅ እንዲያደርጉት መልዕክታቸውን ማስተላለፋቸውን ኢዜአ በሰሜን ካሊፎርኒያ የኢትዮጵያዊያን ስብስብ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

ረቂቅ ሕጉ በአሁኑ ሰአት በኮንግረስ አፈ-ጉባኤዋ ናንሲ ፔሎሲ እጅ ላይ የሚገኝ በመሆኑ አፈ-ጉባኤዋ ሕጉን ለኮንግረሱ እንዳታቀርብ ጥሪ ቀርቧል።

ሕጉ ኢትዮጵያንና በኢትዮጵያና አሜሪካ ያለውን የረጅም ጊዜ ግንኙነት የሚጎዳ መሆኑን ልትረዱት ይገባል ብለዋል ሰልፈኞቹ።

በአሜሪካ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማኅበረሰብ መጋቢት 1 ቀን 2014 ዓ.ም ‘ኤችአር 6600’ ረቂቅ ሕግን የሚቃወም ሰላማዊ ሰልፍ በኒው ጀርዚ ሕጉን ባረቀቁት ቶም ማሊኖውስኪ ቢሮ ማድረጋቸው የሚታወስ ነው።

‘ኤች አር 6600’ እና ‘ኤስ.3199’ ረቂቅ ሕጎችን የሚቃወም ሰላማዊ ሰልፍ መጋቢት 19 ቀን 2014 ዓ.ም በዋሺንግተን ዲሲ በአሜሪካ መንግሥት መቀመጫ ‘ካፒቶል ሂል’ ፊት ለፊት ይካሄዳል።

በአሜሪካ የኮንግረስ አባል ቶም ማሊኖውስኪ (ኒውጀርሲ) ዋና አርቃቂነት፣ በያንግ ኪም (ካሊፎርኒያ)፣ ግሪጎሪ ሚክስ (ኒው ዮርክ)፣ ዴቪድ ሲሲሊን (ሮድ አይላንድስ)፣ ብራድ ሼርማን(ካሊፎርኒያ) እና ማይክል ማካውል (ቴክሳስ) ደጋፊነት የተዘጋጀው ‘ኢትዮጵያ ስታብላይዜሽን ፒስ ኤንድ ዴሞክራሲ አክት’ ወይም ኤችአር 6600 ረቂቅ ሕግ በኮንግረሱ የውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ ውይይት እንደተደረገበት የሚታወስ ነው።(ዋልታ)

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Previous Story

የፓትርያርኩ HR 6600 ላይ ያነጣጠረው ሴራና የጋዜጠኛ አርአያ ያልተሰሙ አዳዲስ መረጃዎች በስለ ሀገር

Next Story

እስክታልቁ ድረስ ስከኑ ይሉናል የአማራ ክልል ፕሬዘዳንት – መስከረም አበራ

Go toTop