ሰሞኑን አዲስ አጀንዳ ሁኖ ያለዉ መንግስት ከአሸባሪዉ የትግራይ ወራሪ ሀይል ሊደራደር ወሰኗል፤ማሳያዉም በየአካባቢዉ ዉይይት እያካሄደ ነዉ የሚል ነዉ።
እንደ አጋጣሚ ሁኖ ከ5/6 አመት በሁዋላ ድርጅቱ በጠራዉ እንዲህ አይነት ወሳኝ መድረክ እኔም ተገኝቸ ዉይይቱን ተከታትየዋለሁ። በዚህ ዉይይት እንደተረዳሁት ከሆነ ከማናቸዉም ወገን ጋር የሚካሄድ ድርድር በተባለዉ ልክ የሚተገበር ከሆነ ለኢትዮጵያም ሆነ ለአማራ ጥቅም እንጅ ጉዳት አያመጣም። እኔም በተገኘዉ ድል ተደስቸ ” ነገሮችን በአርምሞ እየተከታተልኳቸዉ ነዉ ” ያልኩት፣ ድርድር እዉነትም የሚካሄድ ከሆነ በተነገረዉ ልክ ይፈፀም ይሆን ወይ የሚለዉን የምከታተለዉ መሆኑን ለመግለፅ ነዉ።
ለሁሉም ይህ ጦርነት አንድም በሀይል ሁለትም በድርድር መቋጨቱ አይቀሬ ነዉ። ሁለቱም አማራጮች ግን የኢትዮጵያን ሆነ የአማራን ጥቅም አሳልፈዉ የማይሰጡ እና ለጠላት ጉልበት የማይሰጡ መሆናቸዉ ላይ እርግጠኛ መሆን ያስፈልጋል።
ከዚያ ዉጭ ድርድር ስለተባለ ብቻ ጫፍ ይዞ መጮህና ቡራ ከረዩ ማለት ተገቢ አይደለም። ሰከን ብሎ ነገሮችን መመልከት ተገቢ ነዉ። ከሁሉ በፊት እየተባለ ስላለዉ ነገር የተሟላ መረጃ መያዝ ያስፈልጋል። በተሟላ እዉቀት ላይ ተመስርቶ የሚሰጥ አሰተያየት ምንጊዜም ገንቢ ነዉ።
ለሁሉም ወደ ድርድር የሚገባ ከሆነ(በእኔ እምነት በትህነግ ግትርነት የተነሳ የመሳካት እድሉ ጠባብ ነዉ)፣ ማንሳት ያለብን መሰረታዊ ጥያቄወች የሚከተሉት ሊሆኑ ይገባል፣
- ድርድሩ የሚካሄደዉ መንግስት እና ወራሪዉ ትህነግ በምን ቁመና ላይ ሁነዉ ነዉ? የዚህ ጥያቄ መልስ የድርድሩን ፍሬወች ከወዲሁ ይጠቁመናል።
- በድርድሩ ማዕቀፍ ዉስጥ የአማራ ጥያቄወች(በተለይም የማንነትና ወሰን ጉዳዮች) እንዴት ይስተናገዳሉ?
- ወራሪዉ ሀይል በአገሪቱ በአጠቃላይ በተለይም ደግሞ በአማራና አፋር ህዝቦች ላይ ላደረሰዉ ሁሉን አቀፍ ጥቃትና ዉድመት ምን አይነት ሀላፊነት ሊሸከም ይገባል?
የመሳሰሉትን አንኳር ጥያቄወች የሚመልስ ድርድር ከተካሄደ ሌላዉ ነገር እዳዉ ገብስ ነዉ።
በመጨረሻም ድርድር እንዴዉ ቢሆንስ ተባለ እንጅ ቁርጥ ያለ አቋምና ዉሳኔ የተደረሰ አይመስለኝም። ስለዚህ ዉሳኔ እስኪደረስ ድረስ በተጀመረዉ መንገድ ጠላትን መምታቱ የሚቀጥል መሆን አለበት። ድርድሩ ሁኔታወች ሲሟሉ ሊጀመር ይችላል፤እስኪጀመር ግን ከጉዟችን የሚገታን ነገር ሊኖር አይገባም። የመንግስት አያያዝም ይሄን የሚያሳይ ይመስለኛል።