እስክንድር ከበደ
አትሌት ሀይሌ ገብረሰላሴ በዓለም አቀፍ የሩጫ መድረክ ደጋግሞ በማሸነፍ የኢትዮጵያ ህዝብ መዝሙር ያዘፍናል፡፡ አንድ ቀን የኬኒያው አትሌት ፖል ቴርጋት አንደኛ ወጣ፡፡ ፖል ቴርጋት የኢትዮጵያን ህዝብ መዝሙር ይዘምር ጀመር፡፡ ( ይህ የተጋነነ ቀልድ ሊሆን ይችላል) አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ የኢትዮጵያ የማሸነፍ ምልክት ነው፡፡ አንድ ሀገር ሄዳችሁ ከየት እንደመጣችሁ ቢጠይቋችሁ፤ ከኃይሌ ገብረስላሴ ሀገር እንደመጣችሁ ከተናገራችሁ ወዲያው የሚረዷችሁ ብዙ ናቸው፡፡ ኃይሌ ገብረስላሴ በዓለም አቀፍ መድረክ ኢትዮጵያን ወክሎ ብዙ ሜዳሊያዎች ወስዷል፡፡ የወርቅ ሜዳሊያዎቹ ተራ አሸብራቂ ጌጦች አይደሉም ፡፡ ስለኢትዮጵያ ያገኛቸው ውድ ክብሮች ናቸው፡፡ ከፊት ቆሞ የበርካታ ሀገራት አትሌቶች ከኋላው አስከትሎ የኢትዮጵያን ህዝብ መዝሙርና ባንዲራን አስጠንቷል።
https://fb.watch/9zpG6AREPP/
በተስፋዬ ገብረአብ አንድ ድርሰት ውስጥ ስለአንድ የሶቭየት ህብረት ዜጋ ወግ ጽፎ ማንበቤን አስታውሳለሁ፡፡ ስደተኞች ተራ በተራ እየተመዘገቡ መዝጋቢዋ የሞስኮቡን ሰው የየት ሀገር ዜጋ እንደሆነ ትጠይቀዋለች፡፡
”ሀገሬን ከስራ ስመለስ አጣኋት ” ይላል ስደተኛው
” ሀገርህ የት ነው ?” አለችው መዝጋቢዋ በመገረም ፡፡
” የቀድሞዋ ሶቭየት ህብረት ናት፡፡ ከስራ ስመለስ ፈራርሳ ጠበቀችኝ ”
” ስራህ ምን ነበር ?” አለች ስደተኛውን በመገረም እያየችው፡፡
”ጠፈርተኛ ” አላት ያ ስደተኛ ፡፡ ወደ ህዋ ከሄደ በኋላ ሶቭየት ህብረት 15 ትናንሽ ሀገራት ሆና ጠበቀችው፡፡ ይህ ጠፈርተኛ የሶቭየት ህብረት ዜጋ ሆኖ ወደ ህዋ ሄዶ መሬት ሲወርድ አጣት ፡፡ በዚህ ሰው የሚፈጠረውን የሀዘን፣የመከፋትና የመሰበር እንዲሁም ብዙ ውል አልባ ጉድለቶች የትኛውም ነገር አይሞላውም፡፡ የአትሌት ኃይሌ ገብረስላሴም ሆነ የአዛውንት ጀኔራሎች የግንባር ዘመቻ የላቀ ግብ ያጠለቁት ኒሻኖች ምትሀትና ህያውነት ሀገራቸው ናት፡፡