አይዞን ወሎ (አሁንገና ዓለማየሁ)

October 31, 2021

አይዞን ወሎ
በውበትም በባሕርይ
ከማርም ማር ወለላ
ጣፋጭ የወይን ዘለላ
የሥልጣኔው እምብርት
የእውቀት ጭማቂው ጠለላ
የአለት ቅኔሽ ላሊበላ
የቃላት ቅኔሽ ሳይንት ዋድላ
የአክሱም ነገሥታት መሸሻ
የዛጔ ጻድቃን መንገሻ
የበሬንቱ ጦር መድረሻ
የሙእሚን አገር የኡለማ
የወዳጃ የመንዙማ
የአምባሰል ባቲ ዜማ
ባጥሽን ዘልቆ የሚሰማ
የትዝታችን መዲና
ያንቺወዬአችን ቃና
ኧረ ምኑ፣ የቱ ጎድሎ?
የደም ኅብር ነበርሽ ወሎ
የፈጠረሽ ተቀላቅሎ
አማራ አገው አርጎባ
ከትግሬ ኦሮሞ ሲጋባ
እና ግን
የእንክርዳዱ ሊጥ ሲጋገር
ባምናው ምጣድ አክንባሎ
የአድዋችን ጦስ ጭዳ ሲሻ
እሳት ላይሽ ተከንብሎ
የትህነጉ የእሮብ ሴራ
አሳልፎሽ ለመከራ
የአቢይ አህመድ ረጅሙ ቀን አርብ ሆኖብሽ የጎልጎታ
ችንካር በራ/ስጌ በግርጌሽ/ በቀኝ በግ/ራሽ ሲመታ
በጎንሽ ጦር ተሽጦ
ለጥም የሰጡሽ ሆምጥጦ
በእሾህ አክሊልሽ ስቀው
በኤሎሄሽም ተሳልቀው
የቂም እሳት ሲንቀለቀል
ለአይሁድ ሮማዊው በቀል
ደጀኔ ብሎ ስሞሽ
አሳልፎ ሰጭ ይሁዳ
ጴጥሮስሽም ክዶሽ ማልዳ
መከራ አይተሽ እንደጌታ
በጊሸን ትከሻ መርከብሽ
ግማደ መስቀል አርፎብሽ
የሃጂ አገር የመነኩሴ
የአዛና ምድር የቅዳሴ
የነካሌብ የነሙሄ
ምልእት ነበርሽ በኩለሄ
ዛሬ ታጭተሽ ለኤሎሄ
የጭንቅሽ ሬቱ ቢመርም
እንዲህ ሆኖ ግን አይቀርም
አይዞሽ ሲሞላ ሱባኤ
የሕዝብሽ ዱአ ጉባኤ
ሞታለች ቢሉሽ ቅዳሜ

ቀጣዩ እሁድ ነው — ትንሣኤ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Previous Story

የሕወሃት ኃይሎች ስልታዊቷን የደሴ ከተማን መቆጣጠራቸውን ትናንት ቅዳሜ ካስታወቁ በኋላ የመንግስት ኃይሎች በከተማዋ ዛሬ እሁድ አዲስ ውግያ መክፈታቸው ተሰማ

Next Story

ኢትዮጵያን በአንድነት ከጥቃት እንድንከላከላት ጥሪዬን አቀርባለሁ – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ

Go toTop