ለተወደዳችሁ የዘ-ሐበሻ ድረ-ገፅ ታዳሚያን እና የዝግጅት ክፍሉ ባልደረቦች! በሀገር ውስጥና በውጪ ላላችሁ ውድ ኢትዮጵያውያን በሙሉ! ለ2014 አዲስ ዓመት እንኳን አደረሳችሁ!! ዛሬ ዘመን መለወጫ እንደመሆኑ፤ የአውደ-ዓመት ሙዳችንን በጠበቀ መንገድ ሆዳችንን ሳያስጨንቅ፤ አዕምሮአችንን ሳይጎረብጥ፤ በሆዳችን የያዝነውን! በአዕምሮአችን የምናብሰለስለውን ጉዳይ! ቀለል ባለ መልኩ በጥቂቱ እየተጨዋወትን ብናንሸራሽረው፤ ለዚህ ዓመት የሀሳብ ስንቅነትና ዝግጁነት ጠቀሜታ ይኖረዋል ብዬ አስባለሁ፡፡ እነሆ፤
ቴዎድሮስ ጌታቸው /ደራሲና የፖለቲካ ተመልካች/
እንቁጤን በትዝታ ስንቃኝ!
መቼም መስከረም አንድ ከመጥባቱ በፊት የእንቁጣጣሽ ዋዜማ ድረስ፤ አውደ-ዓመት የሚያስመስሉ ብዙ የሚያውዱ ነገሮች አሉ፤ ልጅ እያለሁ ‹‹በአመት በዓል መዳረሻ›› ልቤን ከሚያውዱኝ ነገሮች ውስጥ፤ አባቶችና እናቶች የበግ፣ የዶሮ፣ የቅቤ፣ የሽንኩርት፣ ሎሚና እና የማጣፈጫ ቅመሞች ሸመታ አንዱ ነው፤ የጥላሁን ገሰሰ ‹‹በፀሐይ ብርሃን ደምቃ ክረምትና በጋ፤ የትውልድ ሀገር ያላት ያሥራ-ሶስት ወር ፀጋ…››፤ የማን አልሞሽ ዲቦ ‹‹ጤና ለሰጠው ሰው እድሜውን ላደለው፤ አውደዓመት ደስታ ነው አውደዓመት ፀጋ ነው…››፤ የታደሰ አለሙ ‹‹መጣሽ እንምነሽነሽ ቀረሽ እንምነሽነሽ…አውደ-ዓመት ዓለም ነሽ…›› የሚሉ የዓውደ-ዓመት ጥዑም ዜማዎች፤ በሬዲዮና ቴሌቪዥን የንግድ ማስታወቂያዎች መሀል ቁርጥ…ቁርጥ እያሉ ሲቀርቡ፤ በቤት ውስጥ ከሚገኙት የአሪቲ፣ የሎሚና የቅመማ-ቅመም ሽታዎች ጋር ተደባልቀው፤ ልብን በደስታና ተስፋ ፀዳል ያሞቃሉ፡፡ ይህ እንግዴ ዋዜማ ላይ ነው!!
መስከረም 1 ጨለማውን ገፍፎ ወፍ ጭጭ….ጭ ሲል! በቤት ውስጥ የሚከናወነው ነገር ሁሌ ግርም ይለኛል፤ አይ ልጅነት! መቼም አይረሳኝም! እናታችን ከተኛንበት ትቀሰቅሰንና እዚያው በአልጋችን ላይ እያለን፤ የሆነ ፍትፍት ነገር በአፍ-በአፋችን ታጎርሰናለች፤ ፌጦና ሎሚ የተቀላቀለበት የእንጀራ ፍትፍት ነው! ጉምዝዝ ቢለንም የእናት ጉርሻ ነውና አላምጠን መዋጣችን አይቀርም፤ ‹‹እ…ም በቃኝ!›› እያልን በሞልቃቃ ድምፃችን ብናጉረመርምም ማን ሰምቶን ‹‹ዝም ብለህ ጉረስ! ለራስህ ነው! በሽታ ውስጥ እንዳትወድቅ ነው!›› የሚል ማስጠንቀቂያ እየተሰጠህ፤ ከእህቶችህና ወንድሞችህ ጋር ወይም ብቻህን! በጎርጓዳ ሳህን ውስጥ ያለውን ጎምዛዛውን የእንጀራ ፍትፍት እስኪያልቅ ድረስ! የመጉረስ ግዴታህን ትወጣለህ፡፡
ፍትፍት የመጉረስ ግዴታህን እንደተወጣህ አንድ ማስጠንቀቂያ ይታከልልሀል፤ ‹‹በየደጁና በየበራ-በሩ ሎሚ ይጣላል! ሟርት ስለሆነ እሱን እንዳትረግጡ! ዃላ በሽታ ውስጥ ነው የምትወድቁት!››፤ እንዲህ ያሉ የማስጠንቀቂያ ምክሮች እያገባደድክ ባለህበት ሰዓት፤ ከየት መጣ የማይባል! የቀለጠ የሴቶች ‹‹የአበባይሆሽ ድምፅ›› ድንገት ከተፍ ይላል!! በሩን ስትከፍትላቸው! እንዲህ ባለ በቀለጠና በተስረቀረቀ ድምፅ! የአበባይሆሽ ዜማ የሚያወርዱት! የጎረቤት ልጃገረዶች መሆናቸውን ትረዳለህ፤ በዚያች የእንቁጤ ቀን ግን! ልጃገረዶች ሳይሆኑ! አምላክ የላካቸው መላዕክቶች መስለው ይታዩሀል!! አንተም በድርሻህ! ገላህን ተጣጥበህ! የተገዛልህን አዲሱን ልብስ ለብሰህ! ያዘጋጀኸውን የእንቁጤ ስዕል ይዘህ! ወደወዳጅ፣ ዘመድና ጎረቤት ትፈተለካለህ!!
የ2014 ክስተቶችን ስንቃኝ!
አሁን በአካል አድገናል! በአዕምሮም በስለናል! ምን-አልባት ልጆች ወልደናል ወይም በሀገራችን አባባል ‹‹ዓይናችንን በዓይናችን›› አይተናል!! ስለዚህ ብዙዎቻችንን እንቁጣጣሽ ‹‹እንቁጤን›› ብቻ ሳይሆን! ‹‹አዲሱ ዓመት እንዴት ያልፍ ይሆን?›› እያልን አሻግረን እንድንመለከት! አንዳች የኃላፊነት መንፈስ ያስገድደናል!! በመሆኑም ይህ ‹‹የኃላፊነት መንፈስ›› ዛሬ ላይ ቆመን 2014ን ሙሉውን ዓመት እንድንቃኝ ይመራናል፡፡ በኃላፊነት መንፈስ የተመራው ቅኝታችን ደግሞ አንድ ተጠባቂ ክስተት እና ሁለት መጤ ክስተቶችን እንድናገኝ ያስችለናል፡፡ እነሆ፤
‹‹እጅን በአፍ የሚያስጭነው›› ተጠባቂ ክስተት!
ለዚህ ሀሳብ መነሻ የሆኑኝ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ጠቀላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ናቸው፤ ጠቅላዩ እነዚህን ቃላቶች ‹‹እንደውም ይግረማችሁ›› ያሉ በሚመስል መልኩ፤ አንዴ ብቻ ሳይሆን ሁለት ጊዜ ደጋግመው ተናግረውታል፡፡ በአጋጣሚ ካገኘሁት አንድ ጎልማሳ ጋር ‹‹ይህ የጠቅላዩ መልዕክት እንዴት ሊፈፀም ይችላል?›› በሚለው ዙሪያ ተወያይተን ነበር፤ ጎልማሳው ‹‹ጠቅላዩ ቀንደኛ የህ.ወ.ሓ.ት. አሸባሪ ቡድን አመራሮችን ለመያዝ፤ የስፔሻል ሚሊታሪ ኮንትራክተሮችን ሊጠቀም ይችላል›› ሲል ግምቱን አስቀመጠ፤ ‹‹ምን ማለት ነው?›› አልኩት፤ ጎልማሳውም ‹‹ጠቅላዩ በአሜሪካን ከሚገኙ ፕራይቬት ፎርሶች ጋር የቅጥር ውል በማድረግ፤ የአሸባሪዎቹን ቀንደኞች በቁጥጥር ስር ሊያውላቸው ይችላል›› በማለት የግል እይታውን አስቀመጠ፡፡ እኔም ‹‹ይህ ስልት አያስኬድም›› አልኩት፤ ለዚህ ምክንያት አድርጌ ያቀረብኩት ደግሞ፡-
በኮንትራክተር የሚታወቁት የአሜሪካን ስፔሻል ፎርሶች፤ በአሜሪካን አስተዳደር (በጆ. ባይደን) ፍቃድ ሥር የሚንቀሳቀሱ ናቸው፤
በአሜሪካን ስፔሻል ፎርስ መጠቀም! ጣልቃ-ገብነትን በግልፅ የሚያውጅ እና የሀገራችንን መከላከያ ሠራዊት ብሄራዊ አለኝታነትን የሚሸረሽር ነው፤
ሀገራችን ኢትዮጵያ! ድንገተኛ ኦፕሬሽን ለማካሄድ የሚችል፤ በሚገባ የሠለጠነ ‹‹በቂ ስፔሻል ፎርስ›› አላት፡፡ የሚል ነው፡፡
ተወያዬ ‹‹ታዲያ ጠቅላዮ የአሸባሪ ቡድኑ ቀንደኞችን እንዴት በቁጥጥር ስር ሊያውላቸው ይችላል?›› የሚል ጥያቄ አነሳልኝ፤ እኔም! ‹‹የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በየደረጃው ያሉ የሲቪልና የጦር አመራሮቹ፤ የአሸባሪ ቡድኑ ቀንደኛ አመራሮች ላይ የሚወስዱት እርምጃ፤ በምን መልኩ እንደሆነ ቀድሞ ሊገመት የማይቻል ነው›› በማለት፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተገማች ሥራ እንደማይሠሩ ገለፅኩለት፡፡ ይህ ተገማች ያልሆነው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ‹‹እጅን በአፍ ለሚያስጭን ዜና ተዘጋጁ›› የሚለው መልዕክት! ፍፃሜውን በአዲሱ ዓመት 2014 በጉጉት የምንጠብቀው ክስተት ነው!!
‹‹ድል አድራጊነት›› እና መጤ ክስተቶች!
እንደአንድ የፖለቲካ ተመልካች፤ የ2014 ሙሉን ዓመት በፖለቲካ መነፅር ስቃኝ፤ የድል-አድራጊነት ጉዳይ አያሳስበኝም! ምክንያቱም 2014 ሁለንተናዊ ድል የምንጎናፀፈበት ዓመት በመሆኑ ነው!! አሁን ላይ ሆኜ እኔን በእጅጉ የሚያሳስበኝ፤ ከሁንተናዊ ድል አድራጊነታችን በዃላ፤ በሀገራችን አፍጥጦና አግጦ የሚመጣውን፤ ለመምጣቱም አይቀሬ የሆነውን! ግብዝነታችንን ወይም ተመፃዳቂነታችንን /Hypocrisy/ እንዴት አድርገን እናስተናግደዋለን የሚለው ነው፡፡ ምን ማለት ነው!!
ይህን ብርቱ ጉዳይ ግልፅ ለማድረግ፤ ግንባር ቀደም የሕይወት መስዋዕትነት እየከፈሉና ሀገራዊ ግዴታቸውን እየተወጡ ከሚገኙት፤ የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የፌዴራል ፖሊስ ሠራዊት፣ መደበኛ የክልል ልዩ ኃይሎች፣ የክልልና ከተማ ፖሊስ ሠራዊት፤ እንዲሁም ሚሊሻና ‹‹ሀገር ወዳድ ታጣቂዎች›› ባሻገር ያለውን ተጨባጭ እውነታ መቃኘት ጠቃሚ ይሆናል፡፡
እንደሚታወቀው አሁን እያከናወን የምንገኘበት ዘመቻ! በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. መንግስት ውስጥ የአመራርነት ሚና ያለውን የብልፅግና ፓርቲን ጨምሮ፤ በተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ በጋዜጠኞች፣ በፖለቲካ ተንታኞች፣ በአርቲስቶች፣ በሲቪል የመንግስት ሠራተኞች፣ በነጋዴዎች፣ ልዩ ልዩ የሞያ ተሰጥኦ ባላቸው እና በመላው ሕዝብ የጋራ ርብርብ የሚከናወን፤ ‹‹ሀገራችንን እና አፍሪካ ቀንድን የመታደግ የህልውና ዘመቻ›› ነው፡፡ ከነዚህ ከተጠቀሱት ‹‹የህለውና ዘመቻ ተዋናዮች››፤ በሁለት አካላት ውስጥ ከድል በዃላ በ Hypocrisy የመጠለፍ አደጋ ሊያጋጥም እንደሚችል ይታመናል፤ እነዚህም በፖለቲካ ተንታኞች እና በፖለቲካ ድርጅቶች ውስጥ፤ ሊያጋጥሙ የሚችሉ የመጠለፍ አደጋዎች ናቸው፡፡
የከሣቴ ብርሃን ተሰማ የአማርኛ መዝገበ ቃላት፤ ‹ግብዝ› የሚለውን ቃል ‹ቁም ነገርና ጥኅክርና የሌለው› በሚል ሲገልፀው፤ ተመፃደቀ (መመፃደቅ) የሚለውን ደግሞ ‹ራሱን ፃድቅን አደረገ›፤ ‹ተመጻዳቂ› የሚለውን ደግሞ ‹በውስጡ ተንኮለኛ ኾኖ በላይ ለሰው ዐይን ጻድቅን መሳይ ተመፃዳቂ ይባላል፡፡› የሚል ትንታኔ ይሰጠናል፡፡ ይህን እንደያዝን በ Hypocrisy የመጠለፍ አደጋ ያጋጥማቸዋል ያልናቸውን አካላት እስኪ በጥቂቱ እንመልከታቸው!!
የፖለቲካ ተንታኞች Hypocrisy!
በፖለቲካ ተንታኞች በተናጥል የሚከሰተው ‹‹በሂፖክራሲ የመጠለፍ አደጋ›› መንስኤ የሚሆነው፤ ከድል በዃላ ‹‹በመንግስት ተገቢው ቦታ አልተሰጠኝም›› የሚለው ቅሬታ ሲሆን፤ ፖለቲካ ተንታኙን ድሉን ‹‹ከጋራ ድምር ውጤት›› አንፃር እንዳይገመግመው በማድረግ፤ ለራስ ከሚሰጥ ልዩና ገደብ የለሽ ግምት የሚመነጭ ነው፡፡ በፖለቲካ ተንታኞቹ/ተንታኙ ዘንድ የሚንፀባረቀው፤ ይህን መሰሉ ‹‹ልዩና ገደብ የለሽ ግምት›› ወደፍቅረ-ንዋይ አምርቶ ኩርፊያን ማስከተሉ የማይቀር ያደርገዋል፡፡ ምን ማለት ነው!!
ከዚህ በፊት እንዳየናቸው የፖለቲካ ተንታኞች! ማለትም ከሀገራዊ የፖለቲካ ለውጡ በፊት የለውጥ ሀዋርያ በመምሰል፤ ከፖለቲካ ለውጡ በዃላ ያሰቡትና በምናባቸው ያሰላሰሉት ጥቅም ሲቀርባቸው፤ የሀገራዊ ለውጡ ፍፁም ተቃራኒና ጠላት ሆነው፤ ጊዜያቸውንና አቅማቸውን ‹‹ሀገራዊ ለውጡንና የለውጥ አመራሩን ማጥቂያ›› አድርገው እየተጠቀሙ እንደሚገኙት የፖለቲካ ተንታኞች፤ በህልውና ዘመቻ ላይ ጠቃሚ አስተዋፅኦ ያበረከቱት እነዚህ ተንታኞችም! በድሉ ማግስት በ Hypocrisy ተጠልፈው! ወደዃላ መንሸራተታቸው የማይቀር ይሆናል፡፡ ይህም ማለት ከሌሎች በ Hypocrisy አደጋ ከተጠለፉ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር! ሀገራዊ አዋጭነት ወደሌላቸው የፖለቲካ መደጋገፍ ሊያመራቸው ይችላል፡፡
የፖለቲካ ድርጅቶች Hypocrisy!
በዚህ ‹‹ሀገራችንን እና አፍሪካ ቀንድን የመታደግ የህልውና ዘመቻ››፤ የፖለቲካ ድርጅቶች ያበረከቱት አስተዋፅኦ ከፍተኛ ዋጋ የሚሰጠው ነው፤ ይህን ከፍተኛ ዋጋና ክብር የሚሰጠውን አስተዋፅኦ፤ ጠቃሚ ዋጋ እንዳለው የከበረ ማዕድን ተከብሮ እንዲቀመጥ መድረግ የሚቻለው፤ ከድል በዃላም ላለው ሀገራዊ ሠላምና መረጋጋት አስተዋፅኦውን ማስቀጠል ሲቻል ብቻ ነው፡፡ ከድል በዃላ በፖለቲካ ድርጅቶች ውስጥ በ Hypocrisy የመጠለፍ አደጋ ካጋጠመ! ያለፈውን የከበረ አስተዋፅኦ መና ሊያስቀረው ይችላል!!
የሀገራችንን የፖለቲካ ድርጅቶችን ድርጊት ብዙ ጊዜ እንደታዘብነው፤ በማንኛውም ሁኔታ ላይ ሆነው ድርጅታቸውን ሲመሠርቱ፤ እንወክለዋለን የሚሉትን ማህበረሰብ፤ የፖለቲካ ድርጅታቸውን በመሠረቱበት ቅፅበት ‹‹ዘርተው ያበቀሉት›› መስሎ የሚታያቸው ጥቂቶች አይደሉም፡፡ በዚህ አስተሳሰብ ውስጥ ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶች፤ እንወክለዋለን ከሚሉት ማሕበረሰብ ውስጥ የበቀሉ መሆናቸውን! ያም ማሕበረሰብ ከሌሎች የሀገራችን ማህበረሰቦች ጋር ለዘመናት እጣ-ፈንታውን በጋራ እየወሰነ የመጣ መሆኑን ሲዘነጉ ይስተዋላል፡፡
የፖለቲካ ድርጅቶቹ በዚህ የተሳሳተ ስሌት በመመራት፤ ውስን የማሕበረሰቡን ክፍል ለተናጥል ዓላመቸው ከማንቀሳቀስ አልፈው፤ ማሕበረሰቡ የሰጣቸው በቂ ውክልና ሳይኖራቸው ‹‹እጣ-ፈንታህን እኛ እንወስንልህ›› ይሉታል፤ እንዲህ ያለው የፖለቲካ ድርጅቶች እንቅስቃሴ፤ ሕዝብ ለመምራት በቂ ውክልና ከተሰጠው መንግስት ጋር ወዳልተገባ እንዲሁም ግልፅ የሆነ ቅራኔና ግጭት ውስጥ እንደሚከት አያጠያይቅም፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል!
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፤ ለተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፤ ተገቢ ሹመት (ሥልጣን) እንደሚሰጡ (እንደሚያከፍሉ) ቃል ገብተዋል፤ ‹‹ለተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች›› እንዳልተባለ ልብ እንበል!! ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል! በፖለቲካ ድርጅቶች ውስጥ የሌሉ ነገር ግን በቂ ሞያና ክህሎት ያላቸውን እንደሚያካትት ይታመናል፡፡
ቃል በተግባር እንዲፈፀም የሚጠበቅ ቢሆንም፤ ነገር ግን ከዚህ አልፎ የተገባው ቃል ‹‹ሳይሸራረፍ የሚተገበርና የአስገዳጅነት መርህና ማዕቀፍ ያለው›› አድርጎ መደምደም! ያልተገባ ስህተት ውስጥ ጥሎን! ሌላ የህልውና ዘመቻን ሊወልድ ይችላል!! ስለዚህ ከድል በዃላ ስለሚፈጠረው ‹‹መጤ ክስተት›› ግንዛቤ መጨበጥ፤ ችግር ከመከሰቱ በፊት በሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች እና የፖለቲካ ተንታኞች ውስጥ፤ አስቀድሞ የአዕምሮ ልምምድ ማድረግን የሚጠይቅ! ተገቢ የዝግጅት አካል መሆኑን! ሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶችና የፖለቲካ ተንታኞች ሊያውቁት ይገባል፡፡
ማንሸራሸሪያ!
በዚሁ አዲስ ዓመት፤ በዚሁ የመስከረም ወር፤ በ6ኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ አሸናፊ የሆነው ፓርቲ /ብልፅግና/፤ መንግስት የሚያዋቅርበት ሂደት፤ ዋናውና ተጠባቂ ክስተት ይሆናል፡፡ ሁለንተናዊና ቋሚ ድል የምንጎናፀፍበት አዲስ ዓመት ይሁንልን፡፡
ሠላም ለኢትዮጵያ ሠላም ለአፍሪካ
ቴዎድሮስ ጌታቸው
/ደራሲና የፖለቲካ ተመልካች/