የኢትዮጵያ መንግስት በአሸባሪነት የፈረጀው የኦነግ ሽበርተኛ ቡድን ከትግራይ ሽበርተኛ ቡድን ጋር ወታደራዊ ጥምረት መፍጠሩን አስታወቀ

August 11, 2021
mero

የኢትዮጵያ መንግስት በአሸባሪነት የፈረጀው ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር በማለት ራሱን የሚጠራው እና በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሰው የታጠቀ ኃይል ከትግራይ ኃይሎች ጋር ወታደራዊ ጥምረት መፍጠሩን አስታወቀ። በሀገሪቱ አሁን ያለው ብቸኛ መፍትሔ « ይህንን መንግስት ማስወገድ ነው» ለዚህም ከትግራይ ኃይሎች ጋር ጥምረት ፈጥረናል ሲሉ የኦሮሞ ነጻነት ጦር አዛዥ ኩምሳ ዲሪባ ለአሶሽየትድ ፕረስ ነግረዋል።

ጥምረቱ በትግራይ ኃይሎች ሃሳብ አመንጪነት ከጥቂት ሳምንታት በፊት መፈጸሙንም ጨምረው ገልጸዋል። «ጥምረቱ የጋራ ጠላትን በጋራ መፋለም » በሚል መርህ በተለይ ወታደራዊ ትብብር ለማድረግ ከስምምነት መደረሱንም አመልክተዋል። በወታደራዊ ስምምነቱ መሰረት ወታደራዊ መረጃዎችን መቀባበል መጀመራቸውን የገለጹት የታጣቂ ቡድኑ መሪ ለጊዜው ጎን ለጎን ሆነው መዋጋት አለመጀመራቸውን እና ምናልባትም «ያንን የምናደርግበት ጊዜ ሊመጣ ይችላል» ብለዋል።
ከወታደራዊ ጥምረቱ ጎን ለጎን ከሌሎች የፖለቲካ አጋሮች ጋር ንግግር መጀመራቸውንም ለአሶሽየትድ ፕረስ የነገሩት ኩምሳ ዲሪባ የጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድን መንግስት የሚቀናቀኑ እና አጋር መሆን የሚሹ ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች በሀገሪቱ እንዳሉም ጠቁመዋል።
በጉዳዩ ላይ የትግራይ ኃይሎች አዛዥ ጄኔራል ጻድቃን ገብረትንሳይ እና ከጠቅላይ ሚንስትር ጽ/ቤት የተሰጠ ምላሽ እንደሌለ የዜና ምንጩ አክሎ ጠቅሷል። ይሁንና ህወሓት፣ቡድኑን ጨምሮ በኢትዮጵያ እጣ ፈንታ ላይ ለመወሰን አቅም አላቸው ካላቸው ቡድኖች ጋር ጋር እየተወያየ መሆኑን ቃል አቀባዩ አቶ ጌታቸው ረዳ ለዶቼቬለ በሰጡት ቃለ ምልልስ ተናግረዋል።
«ኢትዮጵያን አሁን ካለበት ቀውስ ለማዳን አቅም ካላቸው ኃይሎች ጋር መተባበር እንዳለብን እናምናለን። ከዛ ጋር የተያያዙ የጀመርናቸው ውይይቶች አሉ። የዛ አካል OLF ሠራዊትም በኢትዮጵያ ውስጥ ስራ እየሰራ ያለ በኢትዮጵያ እጣ ፈንታ ላይ ለመወሰን አቅም ካላቸው ወገኖች አንዱ ስለሆነ ከኛጋም የጀመርነው ውይይት አለ ከዛ በላይ ብዙ መናገር አልችልም።» ብለዋል። ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ቡድኑ በኢትዮጵያ በህዝብ ብዛት ትልቁን ቁጥር የሚወስደውን ኦሮሚያ ክልል ሕዝብ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት ለማጎናጸፍ እንደሚታገል ሲገልጽ ቆይቷል።
ፎቶ ፤ ከማሕበራዊ ትስስር ዘዴዎች የተወሰደ /DW

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

gizachew
Previous Story

የትግሉ ዓላማ አሸባሪውን ሙሉ በሙሉ መደምሰስና ተላላኪዎቹንም የኢትዮጵያ ስጋት እንዳይሆኑ ማድረግ መሆኑ ተገለጸ

Next Story

ጠቢቡ ሰለሞን የፈተናት ሴትና ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚፎክሩት እርጉሞች! – በበላይነህ አባተ

Go toTop