ሕወሃትና “ሕዳር ኮበለለች፣ትብትቧን አዘለች” (ከይመር ሙሄ)

December 1, 2020

ከይመር ሙሄ
ኅዳር 22, 2013

ከአገር ቤት ከወጣሁ እረዘም ያለ ዓመታት ስላስቆጠርኩ፣ ዛሬ ላይ “ኅዳር ኮበለለች ትብትቧን አዘለች” እንደባህል የሚተገበር ይሁን አይሁን አላውቅም። እኔ በአደግኩበት አካባቢ ኅዳር ውስጥ በየዓመቱ ሁሉንም ባሳተፈ መልክ ሰፈር ይፀዳና የመንደር ቆሻሻ የሚጣልበት ጎድጎድ ያለ ቦታ ላይ ይጠራቀማል፣ ይከመራላ። የንጨት ስንጣሪው፣ ቅጠሉ፣ ሳሩ ከላይ ከበድ ያለው ቆሻሻ ከሥር ይሆንና በሳት ይለኮሳል። ይጓፈጥና መጨስ ሲጀምር የየሰፈሩ ጭስ ተገናኝቶ ወደላይ ሲወጣና እንደጉም ሲያስገመግም አካባቢው ከዳር እስከዳር የተቃጠለ ይመስላል። መንደርተኛው፣ ልጅ አዋቂው፣ ሴቱ፣ ወንዱ በየመንደሩ በተጓፈጠው እሳት ዙሪያ ቆሞ ጭሱን እያየ ከፍ ባለ በተቀናጀ ድምፅ “ኅዳር ኮበለለች፣ ትብትቧን አዘለች” በማለት በሽታው ሁሉ ንቅል ብሎ ካካባቢው እንዲወጣለት ምኞቱን ይገልጣል።

የሃገራችን መከላከያ እንዲሁም የአማራ ክልል ልዩ ሃይልና ሚሊሽያ ትግራይ ላይ የተጎናፀፉት ድል በኅዳር ወር ውስጥ ስለተፈፀመ፣ ቆሻሻውና ተውሳኩ ሕወሃት ከዳር ወደመሃል እየተጠረገ መቀሌ ላይ እንደጢስ የተነነበት ሁኔታ “ኅዳር ኮበለለች፣ ትብትቧን አዘለች” የሚያሰኝ ክስተት ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ሕወሃት ላለፉት ሰላሳ ዓመታት በወገናችን ላይ የፈጸመው ግፍ፣ ግድያ፣ ዝርፊያ፣ ድብደባ፣ አካል ማጉደል፣ ካገር ማሰደድ፣ የማህበረሰባችንን እሴቶች የሆኑትን መከባበርን፣ መተሳሰብን፣ መተማመንን፣ አዜኒታን እንዳልነበሩ ማድረጉ ሌሎች አስከፊ ስሞቹ እንደተጠበቁ ሆነው ከቆሻሻ ያለፈ ሌላ ምን ማዕረግ ሊያስገኝነት ኖሯል?

ለመሆኑ የማይካድራን የወገኖቻችንን ጭፍጨፋ፣ በሰሜን እዝ ላይ የተፈጸመው ክህደትና ደባን የሚበልጥ ቆሻሻ ሥራ ማሰብ ይቻላል? ለውይይትና ለእርቅ የተጠሩ ወገኖችን አብልቶ አጠጥቶ በማዘናጋት በተኙበት ማረድ፣ ለዘመናት የትግራይ ወገናችን በድርቅና በቸነፈር ሲመታ ያለውን አካፍሎ የሚያበላውን ጎረቤቱን የአማራን ሕዝብ ዘሩን ለማጥፋት መግደልና ከመሬቱ ማፈናቀል፣ በቋንቋው እንዳይናገርና በቋቋው እንዳያለቅስና ዘፈን እንዳይሰማ ማስገደድ የቆሻሻነት ጥግ እንጂ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል? ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ እንድትሆን በታሪክ ከፍተኛ ሚና የተጫወተውን አማራን በጠላትነት የፈረጀ ሕገመንግሥት በማውጣት በማንነቱ የጥቃት ዒላማ እንዲሆን ያደረገ የጥራጊ ጭንቅላት ባለቤት ቆሻሻ እንጂ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል?

የትግራይ ሕዝብን ብሶት እቀርፋለሁ ብሎ በመነሳት በመንደር ልጅነት ዙሪያ ተኮፍሶ በትግራይ ሕዝብ ስም የነገደ የሞራል ኮምፓሱ የተሰበረበት ስብዕና አልባ ስብስብ፣ ሴት መድፈርንና ሽንት በእስረኛ ላይ መሽናትን ብቻ ሳይሆን ግብረሰዶም በመፈፀምና በማስፈፀም የግለሰብን ክብር ያዋረደ፣ ለብዙ ዓመታት ወገኑን በጉድጓድ በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ሰውነቱ እስኪተላ ያሠርና በረሃብ የቀጣ፣ ሲፈልግም ደብዛውን ያጠፋ በተለምዶ ቆሻሻ የምንለው ሊገልጸው የማይችል ሕወሃት የቆሻሻ ቆሻሻ ነው። የመንግሥትነትን ስልጣን ይዞ፣ ያውም ለአፍሪካ ነፃነት ተምሳሌት በሆነች አገር ላይ፣ ዋና ከተማዋ የአፍሪካ መዲና በሆነች አገር ላይ፣ ባንኩን ታንኩን በቁጥጥሩ ሥር አድርጎ፣ እንደገና በኮንትሮባንድ ንግድና በአደገኛ እፅ ዝውውር ሥራ የሚሰማራ ስብስብ የቆሻሻ ቆሻሻ እንጂ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል?

የትግራይ ሕዝብን ጨምሮ የሁላችንም ጥያቄ “…ከወርቅ ሕዝቢ ተወሊድና…” እየተባለ እንደምን በዚህ ስፋትና ጥልቀት መቆሸሽ ተቻለ የሚለው ቢሆንም፣ መልሱ ግን ሕወሃት ሲወጠን ከጧቱ ይዞት የተነሳው ቆሻሻ አስተሳሰብ እንደሆነ ማንም የሚያጣው አይመስለኝም። በሱዳን በስደት ላይ የሚኖሩ የትግራይ እህቶቻቻን በሴትኛ አዳሪነት ሰውነታቸውን ሽጠው የሚያገኙትን ገንዘብ ለተለያየ በሽታ የተጋለጠ ሰውነታቸውን እንዳያሳክሙበት በካድሬዎቹ አማካይነት እጅ እየጠመዘዘ በማስገደድ በቋሚነት እየነጠቅ በመውሰድና እንዲሁም በረሃብ የተጎዱ ወገኖቻችንን ለመርዳት ከውጭ የመጣን እህል ከጉሮሯቸው በመንጠቅ አዙሮ በመሸጥ  የተቋቋመና ያደገ ድርጅት ቆሻሻ እንጂ ሌላ ምን መገለጫ ሊኖረው ይችላል?

ትግራይ ውስጥ በሰፈሩ ኤርትራውያን ስደተኞች ስም የሚወጣውን ዲቪ ለቤተሰቦቹና እንዲሁም ለሰላዮቹ መጠቀሚያ እያዋለ ወደአሜሪካ እንዲመጡና ዜግነት እንዲያገኙ ያደረገ፣ በኤርትራውያን ስደተኞች ስቆቃ የነገደ የማፊያ ድርጅት ቆሻሻነቱ መቸም በሂሳብ አይደረስበትም። በአግአዚ ጥይት በተገደለ ልጇ እሬሳ ላይ ተቀምጣ እንድታለቅስ ወላጅ እናትን ያስገደደ ስብስብ ከአውሬ እንጂ እንደምን ከሰው ልጅ ማህፀን ወጥቷል ለማለት ያስደፍራል? የሲኦል እሳት አቃጥሎ የማይፈጀው ቆሻሻነት ማሰብ ከተቻለ የሕወሃት ቆሻሻነት ነው። ስለሕወሃት “ሰይጣን በዕድሜ እንጂ በተንኮልና በክፋት አይበልጣቸውም” ተብሎ የተወራውን ለቀልድና ወሬ ለማሳመር ብቻ ነው የተባለው ደፍሮ የሚል ካለ እንስማ!

“ኢትዮጵያውያን ደሃ ብቻ ሳይሆኑ ለካስ ባለጌም ናቸው!” ያስባለን የነማን አስጸያፊ ሥራ ነው? ከሰላሳ ዓመታት በፊት የነበሩት የአገራችን መንግሥታት በመልካም አስተዳደር ጉድለት ለብዙ ችግሮች ቢዳርጉንም ድህነታችን ሳያሸማቅቀን በታሪካችን ኮርተን የምንኖር ሕዝቦች ነበርን። ዛሬ ሕወሃት በሕገመንግሥት አዋቅሮ እንዲከሰት ባደረገብን ዘር ተኮር ግድያ ምክንያት በዓለም አካባቢ በሃፍረት አንገታችንን እንድንሰብር ተገደናል። ወደድንም ጠላንም እኛም ሆንን መጪው ትውልድ ሊያመልጠው የማይችልው የታሪክ ሃፍረት ማቅ በቆሻሻው ሕወሃት እንድንከናነብ ተደርገናል። ሕወሃት ቆሽሾ አቆሽሾናል!

የዋልድባ ገዳምንና የታላቁ አንዋር መስጊድን በመሳሰሉ የእምነት ተቋማት ውስጥ ሰላዮች በመሰግሰግ በምእመናን መካከል አለመተማመን ከመፍጠር የበለጠ ምን ቆሻሻነት አለ? ምን በሕወሃት ያልቆሸሸ የሕብረተሰባችን ክፍል አለ? ሁለት ወንድማማች ሕዝቦች  “እሳትና ጭድ እንዲሆኑ”ና እርስበርስ እንዲጨራረሱ የሆነኝ ብሎ በታሪክ ያልተደገፈን ትርክት በመመርኮዝ የአኖሌን የተቆረጠ ጡት ያያዘውን የእጅ ሃውልት ያቆመው የሕወሃት ስብስብ መገለጫው ቆሻሻ ነው ስል ሌላውን በተለምዶ ቆሻሻ የምንለውን መስደብ እንዳይሆንብኝ እሰጋለሁ። “ሰኔና ሰኞ ሲገጣጠም” እንዲሉ ከፍተኛ መስዋዕትነት ከተከፈለ በኋላ በዚህ በያዝነው ኅዳር ወር የሃገራችንና የሕዝቦቿ ያደገደገ እድፍ ሆኖ የቆየው ቆሻሻው ሕወሃት ከመቀሌ፣ ከወልቃይትና ጠገዴ እንዲሁም ከራያ ተጠራርጎና ተጥረግርጎ እንደ ኅዳር የቆሻሻ ጪስ ተኖ በመበተኑ “ኅዳር ኮበለለች፣ ትብትቧን አዘለች” ማለት በእርግጥም እጅግ ወቅታዊ ነው!

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Previous Story

ኡንም  “ሳይቃጠል በቅጠል  ”- ለሁሉም ይበጃል – ማላጂ

Next Story

አድናቆትም ንቀትም አያወላዳም !   – “ማላጅ ”

Go toTop