ከኢትዮጲያውያን አውስትራሊያውያን የሰላምና ትብብር አድቮኬሲ ግሩፕ የተሰጠ መግለጫ

July 14, 2020
የኢትዮጵያውያን አውስትራሊያውያን የሰላምና የትብብር አድቮካሲ ግሩፕ ፤ ኢትዮጵያ  ላይ የደረሰው የሰሞኑ ሰቆቃ በእጅጉ ያሳሰበን በመሆኑ ይህንን መግለጫ ለማውጣት ተገደናል።
በአገራችን በተለይም በኦሮሞ ክልል የተከሰተውን ሁለገብ አስቃቂ ጥፋት በእጅጉ እንዳሳዘነን እየገለጽን ጽንፈኞች ባስነሱት በዚህ ሁከት ሕይወታቸውን ላጡ ኢትዮጵያውያን ቤተሰቦች ሁሉ መጽናናትን እንመኛለን።
የ ህዝባችን እምባ መድረቅ አለበት። ውስጣችን ተሸጉጠው የሚቦረቡሩን ባንዳዎች ሌላ ጥፋት ከመሰነቃቸው በፊት ሊመነጠሩ ይገባል።  የውጭ ጠላቶቻችንን መግቢያ ቀዳደዎች ሁሉ መድፈን መቻል አለብን።
እርግጥ ነው መንግሥት የተለያዩ ግዙፍና አቻ ትኩረት የሚሹ  ጉዳዮችና ተግዳሮቶች እንደገጠሙት በሚገባ እንረዳለን። ይሁን እንጂ የተለያዩ የፍትህና የጸጥታ አካላት ይህንን እኩይ ተግባር  ቀድመው ማክሸፍ ይጠበቅባቸው ነበር።  «ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ እንዲሉ» በቅድመ መከላከል ላይ ትኩረት ተሰጥቶ በብቃት ባለመሰራቱ ሕዝባችንና አገራችንን ከፍተኛ ዋጋ አስከፍሏል።
ከዚህ በፊት ከተከሰቱ ተመሳሳይ ችግሮችም ጋር በተያያዘ ትኩረት መሻት የሚገባቸው ቀጠናዎች ተለይተው ስለሚታወቁ  በእነዚህ አካባቢዎች ልዩ ትኩረት ማድረግ ቀዳሚ ሥራ መሆን እንደነበረበት ይታመናል። ይህ አሳዛኝ ክስተት ለመንግሥት የመጨረሻው የማንቂያ ደወል ሆኖ ዳግም መሰል ሁኔታ እንዳይከሰት  መሰረታዊ ሥራ መስራት የሚጠበቅበት ጊዜ እንደሚሆን እንተማመናለን። የኢትዮጵያ ሕልውና የሁሉም ቁልፍ ጉዳይ በመሆኑ ጽንፈኞችን፤ዘረኞችን በማይመቻመች መንገድ ሥርአት የማስያዙ ጉዳይ የመንግሥት መሆኑ ላፍታም ሊዘነጋ አይገባም።
በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ሕዝብን የጨፈጨፉ ግለሰቦች፤ የተባበሩ የጸጥታ አካላት ተባባሪ ባለስልጣኖች ጥፋታቸው ትንሽ ትልቅ ሳይባል ባስቸኳይ ለፍርድ እንዲቀርቡ እያሳሰብን፦ከሁሉም በላይ የዚህ ሁሉ ጥፋት መሰረቱ  የዘር ፓለቲካና በወጣቱ ላይ የተነዛው የዘር ጥላቻ  በመሆኑ በሕዝቦች መካከል እየተቆፈረ ያለው የልዩነት ሸለቆ ከፍተኛ ነው። ስለሆነም ይህንን አመለካከት የሚቀለብስና ብሎም የሚያከስም በሥልት የታገዘ የአመለካከት ለውጥ ስራ በወጣቱ ዘንድ በመንግሥት በኩል ትኩረት እንዲሰጠው  ሳናሳስብ አናልፍም። በተለያየ መገናኛ ብዙሃን በማህበራዊ ሚዲያና በመሳሰሉት ጥላቻና ክፍፍል በሕዝባችን መካከል የሚነዙትን በጥብቅ እያወገዝን ከዚህ እኩይ ተግባራቸው እንዲታቀቡ በጽኑ እናሳስባለን።
ለኢትዮጵያ ህልውና ሲባል መንግሥት በሚያደርገው አገር አድን እንቅስቃሴ ላይ በቁርጠኝነት ተባባሪ እንደምንሆንም በዚህ አጋጣሚ  እንገልጻለን።
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!
የኢትዮጵያውያን አውስትራሊያውያን የሰላምና የትብብር አድቮካሲ ግሩፕ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Previous Story

ከብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ

Next Story

ፖለቲካ እውነትም ሸር…ጣ  ነው! – ዳግማዊ ጉዱ ካሣ

Go toTop