በቅርቡ ከትጥቅ ትግል ወደ ሰለማዊ ትግል የተመለሱ 38 የኦሮሞ ነፃነት ግንባር /ኦነግ / አባላት ወደ ማሰልጠኛ ማዕከል መላካቸውን በኦሮሚያ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ።
https://youtu.be/J8BZqY2t65c
የመምሪያው አዛዥ ኮማንደር መኳንንት ምትኩ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳስታወቁት አባላቱ መንግስትና ህዝብ ያደረገላቸውን ሰላማዊ ጥሪ ተቀብለው ወደ ሰላማዊ ኑሮና ትግል ለመመለስ የወሰኑ በመሆናቸው ለተጨማሪ ስልጠና ወደ ማስልጠኛ ማዕከል ተልከዋል፡፡
በትጥቅ ትግል ከስድስት ወር እስከ 20 አመታት የቆዩት የግንባሩ አባላት በዞኑ ኩዩ፣ ደገም፣ ወረ ጃርሶና ያያ ጉለሌ ወረዳዎች በሚገኙ ሸለቆማና ተራራማ ስፍራዎችን ጨምሮ በከተማው ውስጥ በትጥቅ ትግል መንግስትን ለመጣል ሲታገሉ የቆዩ እንደነበር አዛዡ አስረድተዋል፡፡
ታጣቂዎቹ በትግል ወቅት ሲጠቀሙበት የነበሩትን የጦርና የመገናኛ መሳሪያ ለዞኑ ፀጥታ ኃይሎች ማስረከባቸውን ኮማንደር መኳንንት ተናግረዋል ።
ወደ ማሰልጠኛ ማዕከል እንዲገቡ የተደረጉ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር አባላት ወደ ህብረተሰቡ ሲመለሱ የተገኘውን ለውጥ መደገፍና የለውጡም ተጠቃሚ መሆን እንዲችሉ የተሃድሶና የስነልቦና ትምህርት የሚሰጣቸው መሆኑ ተመላክቷል፡፡