የክልሉ መንግስት ትናንት አመሻሽ ላይ ባወጣው መግለጫ የትግራይ ህዝብ ለፍትህ ሲል ከፍተኛ መስዋእትነት መክፈሉን አስታውሶ አሁንም በሚሰሩ ሴራዎችና ችግሮች ሳይንበረከክ በአንድነት ትግሉን እንዲቀጥልበት ያሳስባል።
“አሁን እየተወሰደ ያለው እርምጃም በማናቸውም ብሔር ላይ የተለየ ጥቃት የሚፈፀምበት እንዳይሆን፣ መስመር እንዲይዝና ህግን የተከተለ እንዲሆን የትግራይ ህዝብ በከፍተኛ ኃላፊነትና ጥንቃቄ እንዲታገለው” በማለት ጥሪ አድርጓል። ከሌሎች የአገሪቱ ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች ጋር በአንድነት እንዲሰራም ይጠይቃል።
“የትግራይ ህዝብ ማንኛውም ዓይነት ጭቆናና ባርነት እንደማይቀበል ሁሉ ይህ ሌላው ላይም እንዲሆን አይፈልግም፤ ይሁን እንጂ ሊያጠቃን ለሚመጣ ማናቸውም ኃይል እንደማንምበረከክ የትናንት፣ የዛሬና የነገ ቃልኪዳናችን ነው” ይላል መግለጫው።
በሰብዓዊ መብት ጥሰትና በሙስና የተጠረጠሩ በርከት ያሉት የመከላከያ ብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን ሜቴክና የደህንነት አገልግሎት የቀድሞ ኃላፊዎች በቁጥጥር ስር ላይ እየዋሉ እንደሆነ የፌደራል ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ አስታውቋል። ትናንትም የሜቴክ ዋና ዳይሬክተር የነበሩት ሜጀር ጄነራል ክንፈ ዳኘው በቁጥጥር ውለዋል።
ቀደም ሲል በተካሄዱት የኢህአዴግ መድረኮች ላይ እንዲህ ዓይነት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና የሙስና ተግባራት ማስተማሪያ ይሆኑ ዘንድ ህግንና ስርዓትን በተከተለ ፤ ብሄርን መሰረት ሳያደርግ እርምጃ እንዲወሰድ መግባባት ላይ መደረሱንም መግለጫው አክሎ ያትታል።
እንዲሁም እርምጃው እርቅንና ይቅርታን መሰረት ተደርጎ የተጀመረውን ጥረት ወደኋላ የሚመልስ እንዳይሆን ፤ የህግ የበላይነትን ሳይሸራረፍ እንዲፈፀም መግለጫው ያሳስባል።
ህዝቡንም አካባቢውን ነቅቶ እንዲጠብቅና ሊመጣ የሚችለውን ማናቸውንም ጥቃት ከመንግስት ጋር በመሆን ለመመከት እንዲዘጋጅ ይጠይቃል።
እየተወሰደ ባለው እርምጃ የማጣራት ሂደቱ በግልፅነትና ከማንኛውም ኃይል ተፅእኖና ጣልቃ ገብነት ውጪ እንዲሆንም የክልሉ መንግስት ይታገላል ብሏል።
በሌላ በኩል የኦሮሚያ ክልል መንግስት የህግ የበላይነት እንዲከበር እየወሰደ ያለውን እርምጃ እንደሚያደንቅና ለዚህም አስፈላጊውን ትብብር እንደሚያደርግ ትናንት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
https://www.youtube.com/watch?v=DWNBg4WLnI0&t=540s