በአዲስ አበባና አካባቢው በስምሪት ላይ የሚገኙ የሀገር መከላከያ ሰራዊት አባላት ወደ ቤተመንግስት በመሄድ ከመብት እና ጥቅማጥቅም ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችን ማቅረባቸው መብታቸው ቢሆንም ነገር ግን ይህንን ለማድረግ በጅምላ የመጡበት ሁኔታ አግባብ እንዳልነበር ዶ/ር አብይ አህመድ እንዳስጠነቀቋቸው ተገለጸ::
ምንም እንኳ በቴሌቭዥን መስኮት ወታደሮቹ ከዶ/ር አብይ እና ደመቀ መኮንን ጋር ከስብሰባው በኋላ ታቃቅፈው ሰልፊ ፎቶ ሲነሱና ፑሽ አፕ ስፖርት ቢታይም ወታደሮቹ ከደንብ ውጭ ስልኮቻቸውን ይዘው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት መግባታቸው ህግን የጣሰ እንደሆነ ምንጮች ለዘ-ሐበሻ ገልጸዋል::
በመንግስት አሰራር አንድ ሰው ትጥቅ ፈትቶ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ገባ ሲባል ከጦር መሳሪያዎች በተጨማሪ ሴልፎኖችንም አስቀምጦ መግባት ይጨምራል የሚሉት እነዚሁ ምንጮች ሴልፎን ልክ እንደ ጦር መሳሪያ እየተቆጠረ ነገር ግን ትናንት ወታደሮቹ ከደንብ ውጭ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት ይዘው ገብተዋል::
ዶ/ር አብይ ለወታደሮቹ በቀጣይም በየደረጃው ከሚገኙ ከራሳቸው አመራሮች ጋር ዝርዝር ውይይት በማድረግ መግባባት እንደሚገባቸው እንዳስጠነቀቁ የተገለጸ ሲሆን ወታደሮቹ ወደ ቤተመንግስት ሲመጡ አራት ኪሎ አካባቢ ለጥበቃ የመጡ ወታደሮች በሰላማዊው ሕዝብ ላይ የወሰዱት እርምጃ ሕዝቡን ያደናገጠና ሌላ ነገር እንዲያስብ ያደረገ እንደሆነ ዘ-ሐበሻ ካነጋገራቸው ወገኖች ለመረዳት ተችሏል::
ወታደሮች አራት ኪሎ በመኪና የሚያልፉ ሰዎችን እያስወረዱ በእግራቸው እንዲሄዱ ማስገደዳቸውን የጠቆሙት እነዚሁ ወገኖች እነዚህ ወታደሮች ቤተመንግስት ገቡ ሲባል ሌሎች የፌዴራል ፖሊስ አባላት በአስቸኳይ ቴሌ ኮምዩኒክሼንን; ኢትዮጵያ ቴሌቭዥንን; ፋናን እና ዋልታ ህጻዎችን እንደተቆጣጠረ ነግረውናል::
ምሽት ላይ የአዲስ አበባ ሕዝብ በጊዜ ገብቶ ከተማዋ ጭር እንዲል ያደረገውም ቀን ላይ ወታደሮች ከመኪና እያስወረዱ በእግር እንዲሄዱ በማድረረጋቸው በፈጠሩት ሽብር ነው የሚሉት እነዚሁ ወገኖች ምሽቱን ከተማዋ ተረጋግታ በማደር ዛሬ ምንም የተፈጠረ ነገር እንደማይመስል ገልጸውልናል::
የዘ-ሐበሻ ዘጋቢዎች ማምሻውን ከተማውን ተዘዋውረው የተመለከቱ ሲሆን ንግድ ቤቶች ብዙም ሰው ባይኖርባቸውም የተለመደ አገልግሎት በመስጠት; መንገዶች ላይ የዶ/ር አብይ እና የጣሊያኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ፎቶዎች ተለጣጥፈው; የጣሊያን እና የኢትዮጵያ ባንዲራዎች በቦሌ መንገድ እስከቤተመንግስት ድረስ ተሰቅለው ተመልክተዋል::
https://www.youtube.com/watch?v=CzMvgTPy95U&t=353s