በቀጣዩ የኢትዮጵያ ምርጫ ዙሪያ ለመወያየት ዶ/ር አብይ አህመድ ሁሉንም የተፎካካሪ ፓርቲ አባላት ጽህፈት ቤታቸው መጥራታቸው ተሰማ:: የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት ሌሊት ላይ በለቀቀው መረጃ መሰረት ዶ/ር አብይ ከተፎካካሪዎቻቸው ጋር የሚነጋገሩት የፊታችን ማክሰኞ ህዳር 18 ቀን 2011 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አዳራሽ ነው::
“የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችን አሁን ላይ በሀገሪቱ ስለተጀመረው የዴሞክራሲ ለውጥ እና በሚቀጥለው ዓመት የሚደረገውን ሀገራዊ ምርጫ ነፃ እና ፍትሃዊ ለማድረግ ሊወሰዱ በሚገባቸው አስፈላጊ ለውጦች ዙሪያ እንወያያለን” የሚለው የጥሪው ወረቀት በውይይቱ ላይ የሁሉም የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች እንዲሳተፉ ጥሪ ቀርቧል።
በሀገር ውስጥ የተመዘገቡ ተፎካካሪ ፓርቲዎች እና በመንግስት ጥሪ ተደርጎላቸው ከውጭ ሀገር የተመለሱ ፓርቲወች በውይይቱ ይሳተፋሉ የጽህፈት ቤቱ መግለጫ ከዛሬ ጀምሮ እስከሚቀጥለው ሰኞ ህዳር 17 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስም የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ድረ ገጽ እንዲመዘገቡ ጥሪ አቅርቧል::
ዶ/ር አብይ “በእኛና በ ህዝብ መካከል ያለው መሀበራዊ ዉል በ ነፃ ፍቃድ ሊመሰረት የሚችለዉ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ መሆኑን በሁሉም ባለድርሻ ኣካላት ሲታመን ነው።” ማለታቸው ይታወሳል::
ከውጭ ሃገር የገቡት የፖለቲካ ፓርቲዎች በአብዛኛው የውጭ ሃገር ዜግነት ያላቸው በመሆኑ እስካሁን ድረስ በምርጫ ቦርድ ሳይመዘገቡ መቅረታቸውን ከተመዘገቡት ድርጅቶች ውስጥ ብቸኛውም የአፋር ፓርቲ ብቻ መሆኑን ዘ-ሐበሻ ከዚህ ቀደም ዘግቧል:: የፊታችን ማክሰኞ በሚደረገው ስብሰባ ላይም ከውጭ የገቡ የፖለቲካ ድርጅቶች ጥያቄያቸው ከዚህ ጋር እንደሚያያዝ ይጠበቃል::
በዚህ ዙሪያ አስተያየቱን የሰጠው አክቲቭስት ሙሉነህ ዮሐንስ ” ይህን በአንክሮ ስንጠብቀው ነበር። ምነው ዘገየም ብለናል። መንግስትም ሆነ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የሃገርን እና የህዝብን ጥቅም ባስቀደመ፣ በቀናነት፣ ከትናንሽ ልዩነቶች ማትኮር ይልቅ መሰረታዊ በሆኑ የጋራ አበይት ሃገራዊ ፋይዳ ባላቸው ጉዳዮች ላይ አትኩረው ሊወያዩ ይገባል። ለዘመናት ዲሞክራሲያዊ ስርአት መሰረት ለመጣል የተከፈለው ከባድ መስዋእትነት ፍሬ እንዲያፈራ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች በተጨማሪ የማህበረሰብ ድርጅቶች የሃገር ሽማግሌዎችና የሚዲያ አካላት በቀጣይነት ሚና እንዲጫወቱ መደረግ አለበት።” ያለው ሙሉነህ አክሎም “ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ እና የምርጫ ቦርድ በወ/ሮ መአዛ አሸናፊና በወሪ/ት ብርቱካን አመራር ውስጥ መሆን ቀጣዩ ምርጫ ተስፋ እንድናደርግበት አስችሏል። የዶ/ር አብይ እርምጃዎች ሊበረታቱና ሊደገፉ ይገባል። ይህ ሂደት ተፋጥኖ እኔን የናፈቀኝ ፓርቲዎች ምን አይነት የፖሊሲ አማራጭ ይዘው ይመጣሉ የሚለውና ስልጡን የሞቀ የሃሳብ ክርክር ነው” ብሏል::
https://www.youtube.com/watch?v=wcjYZaYCiUM&t=245s