በአሮማያ ዩኒቨርሲቲ በፈነዳ ፈንጂ ሰባ ሰዎች ተጎዱ

May 1, 2014

በሃረር አሮማያ ዪኒቨርሲቲ ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች በፈነዳ ፈንጂ እግር ኳስ በማየት ላይ በነበሩ ሰባ ተማሪዎች ላይ ጉዳት መድረሱንና አንድ ሰው መሞቱን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ አስታወቀ።

የመንግስታዊው ራድዮ ፋና ዘገባ እንደወረደ ለግንዛቤዎ ይኸው፦

ጽህፈት ቤቱ ማምሻውን እንደገለፀው በአዲስ አበባና በዙሪያው የሚገኘውን የኦሮሚያ ልዩ ዞንን በልማት ለማስተሳሰር የተነደፈውን የተቀናጀ የልማት ማስተር ፕላን አስመልክቶ ከፕላኑ ፋይዳና አላማ ጋር የሚቃረን መሰረተ ቢስ አሉባልታ በአንዳንድ ወገኖች በስፋት ሲሰራጭ ቆይቷል፡፡

ይህን መነሻ በማድረግም በበርካታ የክልሉ ነዋሪዎች ዘንድ ትክክለኛውን መረጃ የማወቅ ፍላጎት መኖሩን ከግምት በማስገባት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የተለያዩ መድረኮችን በማዘጋጀት በእቅዱ ልማታዊ ዓላማና በሚያስገኛቸው ጥቅሞች ዙሪያ ማብራሪያ ሲሰጡ መቆየታቸውንና አሁንም በመስጠትም ላይእንደሚገኙም ነው ያመለከተው፡፡

በምክክር መድረኮቹ የተጀመረው ህዝባዊ ውይይት እየተካሄደ ባለበት በአሁኑ ወቅት ትክክለኛው መረጃ እንዲሰጣቸው ጥያቄ ላቀረቡ የኦሮሚያ ክልል ተወላጅ የሆኑ የከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎችንም በውይይቶቹ ውስጥ የማሳተፍ እንቅስቃሴ መጀመሩን አስታውቋል ፡፡

ይሁንና በሁሉም ክልሎች ከሚገኙ ባለ ድርሻ አካላት ጋር የሚደረገው ይህ ህዝባዊ ምክክር ከመዳረሱ በፊት አስቀድሞ ጥርጣሬዎችን ለመንዛት ሆነ ተብለው በተሰራጩ አሳሳች አሉባልታዎችና ሃሜታዎች የተደናገሩ የተወሰኑ ተማሪዎች በፈጠሩት ሁከት በክልሉ በሚገኙ የተወሰኑ ዩንቨርስቲዎች በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል ብሏል፡፡

በዚህ በሃይል በታጀበ ግርግር ሳቢያ በመደ ወላቡ የሶስት ተማሪዎች ህይወት ማለፉ ተረጋግጧል፡፡

በተለይም በአምቦ ዩኒቨርስቲ የተቀሰቀሰው ሁከት ወደ ከተማ በመዝለቁ እስካሁን ባለው መረጃ መሰረት በአምቦ ከተማ ቢዝነስና ኮንስትራክሽን ባንክ ላይ በተደረገው የዘረፋ ሙከራና ሌሎችም ህገ ወጥ የነውጥ እነቅስቃሴዎች በአምቦና ቶኬኩታዮ ከተሞች የሰባት ሰዎች ህይወት እንዳለፈና ባንኩን ጨምሮ በበርካታ የመንግስትና የሀዝብ ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱ ተመልክቷል፡፡

በተያያዘም በሃረማያ ዩንቨርሲቲ ለጊዜው ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች በሰላም የእግር ኳስ ጨዋታ በቴሌቪዥን በመከታተል ላይ በነበሩ ተማሪዎች ላይ በተወረወረ ፈንጂ ወደ 70 ያህል ተማሪዎች የመቁሰል አደጋ የደረሰባቸው ሲሆን፥ የአንድ ተማሪ ህይወት ማለፉ ተረጋግጧል፡፡

በፌዴራልና በክልል የፀጥታ ሃይሎች ትብብር ሁከቱ በተፈጠረባቸው ዩንቨርስቲዎች ውስጥ ያለውን ሁኔታ ለማረጋጋት ተችሏል፡፡

እስካሁን በተደረገው ማጣራት ከበስተጀርባ በመሆን ሁከቱን በማነሳሳትና በማቀነባበር ተግባር ላይ የተሰማሩት ጥቂት ፀረ ሰላም ሃይሎች መሆናቸውን ለማወቅ መቻሉን ነው መግለጫው ያመለከተው ፡፡

ፅህፈት ቤቱ እንዳለው ከዚሁ ግርግር በስተጀርባ የቆሙትና ከዚህ ቀደም በነበሩ ግጭቶች እጃቸውን ሲያስገቡ የነበሩ የአገር ውስጥና ከአገር ውጭ ያሉ ሃይሎች በሚቆጧጠሯቸው ሚዲያዎች እየታገዙ ይህንን የተማሪዎችን ጥያቄ ለጥፋት አላማቸው መጠቀሚያ ለማድረግ መንቀሳቀሳቸው ታውቋል፡፡

እነዚሁ አካላት ህገ ወጥ እንቅስቃሴያቸውን ሰላማዊ ዜጎችን ሰለባ በማድረግ ጭምር ከማራመድ የሚቦዝኑ አልሆኑም ያለው መግለጫው በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ የሚሹ ተማሪዎችን ተገቢ ጥያቄ በአግባቡ እንዳይስተናገድ የሚፈልጉት የነውጥ አቀንቃኞች ከአንድ ጥግ ሆነው ብዙሃኑን ሰለባ በማድረግ ርካሽ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት በመራወጥ ላይ ይገኛሉ ብሏል፡፡

የአገሪቱ ዴሞክራሲያዊው ስርዓት ማንኛውንም አይነት ጥያቄ ለማስተናገድ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን በማጤን ብዙሃኑ ወጣት ተማሪዎች ከጉዳዩ በስተጀርባ በሚንቀሳቀሱ ጥቂት የጥፋት ሃይሎች በሚነዙት የተዛባ ዘመቻና አሉባልታ ሳይደናገሩ ትምህርታቸውን በሰላም እንዲከታተሉ መንግስት አሳስቧል፡፡

በዚህ አጋጣሚ በተፈጠረው ሁከት ሳቢያ ጉዳት ለደረሰባቸውና ወገኖችና ቤተሰቦቻቸው መንግስት የተሰማውን ሃዘን እየገለፀ የጥፋቱ ዋነኛ አንቀሳቃሽ የነበሩትን ተከታትሎ ለፍርድ ለማቅረብ የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጧል ፡፡

ዝርዝሩን ይዘን እንመለሳለን

Previous Story

ጭፍጨፋውና አፈናው ይቁም፤ ወያኔ ይወገድ !!!

Next Story

በአንድነት ፓርቲ ቅስቀሳ – ቪዲዮ ይዘናል

Go toTop