የፓለቲካ እስረኞች እንዲፈቱና በክልሉ ያለው ግጭት እንዲቆም ኮሚሽኑ ጥያቄ አቅርቧል
በዋና ኮሚሽነር መስፍን ዓርዓያ (ፕሮፌሰር) የተመራ የኮሚሽኑ ልዑክ ትላንት መጋቢት 4/2017 ዓ.ም ወደ አማራ ክልል ባህርዳር ከተማ አቅንቶ ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድርና ሌሎች ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ጋር ውይይት አድርጓል።
\
የኮሚሽኑ ልዑክ ወደ አማራ ክልል ያቀናው የአማራ ክልል የአጃንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ በሚካሄድበት አስቸኳይ ሁኔታ ላይ ከክልሉ መንግስት ጋር ለመነጋገር ነው።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ በተገኙበት በዚህ ውይይት የኮሚሽኑ የእስካሁን ስራዎች በዋና ኮሚሽነር መስፍን ዓርዓያ(ፕሮፌሰር) ቀርቦ የክልሉ አመራሮች ስለ ኮሚሽኑ የስራ እንቅስቃሴ ግንዛቤ መሰጠቱ ተነግሯል።
በክልሉ ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ሃይላት ወደ ሰላም ንግግር እንዲመጡ የክልሉ መንግስት እያደረገ ያለውን የሰላም ጥሪ ጥረት ያደነቀው የኮሚሽኑ ልዑካን ቡድን ሆኖም አሁንም መሰራት አለባቸው ያላቸውን ስራዎች ጠቁሟል፡፡
ኮሚሽኑ ምክክሩን አካታች በሆነ ሁኔታ ማከናወን እንዲችል በማንኛውም አካባቢ በፖለቲካ ጉዳዮች ምክንያት የታሰሩ እስረኞች እንዲፈቱ የክልሉ መንግስት በራሱ በኩል እርምጃ እንዲወስድ እንዲሁም በሌሎች ላይም ግፊት እንዲያደርግ ልዑኩ ጠይቋል፡፡
በክልሉ ያለው ግጭት ቆሞ አስቻይ የምክክር ሁኔታ እንዲኖር ራሱ የክልሉ መንግስት ተኩስ አቁሜአለሁ ብሎ በማወጅ የመጀመሪያውን እርምጃ እንዲወስድም ነው የኮሚሽኑ ልዑክ አፅንኦት ሰጥቶ የጠየቀው፡፡
(ኢትዮ ኤፍኤም)