ውድ ወገኖቼ ኢትዮጵያ ብሄራዊ መግባባት ያስፈልጋታል የሚለው ጥሪ የሁላችን ነው። ብሄራዊ መግባባት ሲባል ምን ማለት ነው? የሚለው ጉዳይ ላይ ግልፅነት እንደሌለ የገባኝ የምክክር ኮሚሽነሩ ሲናገሩ አድምጬ ነው። እያዘንኩ በትህትና ይህንን ልበል……….።
ዋናው የምክክር ኮሚሽነር ሲናገሩ የምክክር አጀንዳ ከታች ከህዝቡ ነው የምናመጣው ስለዚህ ህዝቡን እያወያየን አጀንዳ እንሰበስባለን ወደ ሃያ ሺህ ስብሰባ እናደርጋለን ይላሉ። ገበሬውን ስናወያይ ችግሬ የማዳበሪያ ነው ሊል ይችላል ይህ ችግሩ ይመዘገባል ይላሉ ኮሚሽነሩ። ወጣቱ ችግሬ ስራ ማጣት ነው ሊል ይችላል ይህ ችግር ይመዘገባል ይላሉ ኮሚሽነር………።
እንደማየው የብሄራዊ ምክክር ፅንሰ ሃሳብ በምርጫ ከሚመጣ የመንግስትና የህዝብ ስራዎች ጋር ተምታቶባቸዋል። ይህ ኮሚሽን የህዝብን ችግር ሁሉ መዝግቦ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን እናድርግ? ለማለት የተቋቋመ መሆን የለበትም። የማህበረሰብ ችግር እኮ ሁል ጊዜም አለ። ገበሬው የራሱ ከግብርና ጋር የተያያዙ ችግሮች አሉበት፣ ሃኪሙ ከስራው ጋር የተያያዙ ችግሮች አሉበት፣ አስተማሪው ከትምህርት ጋር የተያያዙ ችግሮች አሉበት፣ ወጣቱ የስራ ችግር አለበት፣ ህዝቡ በኑሮ ውድነት እየተጠበሰ ነው፣ ኢንፍሌሽኑ ልጓም አጥቶ ይጋልባል ወዘተ. ይሁን እንጂ ይህ ኮሚሽን እነዚህን ችግሮች አዳምጦ ፓሊሲ ለመቅረፅ የተነሳ አይደለም። እነዚህ ሁሉ የህዝብ ችግሮች የመድብለ ፓርቲ ስርዓት ከተዘረጋ በሁዋላ ፓርቲዎች የህዝቡን ችግሮች እያጠኑ አማራጭ ፓሊሲ እየቀረፁ በምርጫ ስልጣን እየያዙ ሲሄዱ በሚያድግ ዴሞክራሲና ልማት የሚቀረፉ ናቸው። ገበሬው ዛሬ ማዳበሪያ ተቸግሮ ቢሆን የተሻለ መንግስት ሲመጣ ለዚህ ችግሩ መላ ይሰጠዋል፣ በታሪካ አጋጣሚ ዋልጌ መንግስት ሲመጣ ደግሞ የማዳበሪያ ችግሩ እንደገና ሊመጣ ይችላል። ይህንን ችግር የምንቀርፈው በመድብለ ፓርቲ ስርዐት ነው እንጂ የብሄራዊ ምክክር ኮሚሽን በማቋቋም አይደለም። ከቶውንም የዚህ ኮሚሽን ስራ እንደዚህ አይደለም።
በአንድ ሃገር ብሄራዊ መግባባት የሚያስፈልገው በፓርቲዎች መካከል የሃሳብ ልዩነት ስለታየ አይደለም። በተለይ እኛ ብሄራዊ መግባባት የሚያስፈልገን በዋና ዋና መተሳሰሪያ መርሆዎች ላይ ጽንፈኛ ልዩነት ስላለ፣ ምርጫ በማይፈታቸው ልዩነቶች ላይ ስለወደቅን፣ ወይም ችግሮቹን ለምርጫ ብናቀርብ በውጤቱ ለሃገር ህልውና እምቅ አደጋ ደቅኖ ስለመጣብን፣ በለሂቅ ክፍፍል በሃይል ህብረታችን ስለተመታና ስርዐቱ እገጭ እጓ ስለሚል ነው ብዬ አምናለሁ። በኔሽን ግንባታ ላይ መሰረታዊ ችግሮች ስላለ ነው ብየ አምናለሁ።
ለምሳሌ በፌደራል ስርዓቱ፣ በፖለቲካው ሰልፍ፣ በባንዲራና በሌሎች ከፍተኛ መዋቅራዊና ስርአታዊ ትክሎች ላይ መግባባት የለም። ይሄ አለመግባባት በመድብለ ፓርቲ ስርዓት ውስጥ ጤነኛ ልዩነት አይባልም። ስርዓቶች ቋሚ መሆን አለባቸው። ለስርዓት ተከላና ነቀላ ምርጫ ካደረግን አንዱ ሲያፈርስ አንዱ ሲተክል ሃገር መንግስት ሳይረጋጋ ይቀርና ችግር ውስጥ እንገባለን። ስለዚህ ከባድ የለሂቅ ክፍፍል በስርዓተ መንግስት ላይ ሲኖር የብሄራዊ ምክክር አሳብ ይነሳል። ይህ የምክክር ኮሚሽን ግን የህብረተሰብን ችግር ሁሉ ልመዘግብ ነው ብሎ ከተነሳ በራሱ ተወሳስቦ የማይመለከተውን ሲያቦካ ከርሞ ይፈርሳል። ይህ ኮሚሽን ይህንን በማድረጉ የሚጠቅመው ነገር መንግስት ስልጣን ላይ ውሎ ያድር ዘንድ አስታማሚ መሆን ብቻ ነው። የአሁን አያያዙም ይህንን ያሳያል። ሃገሪቱ ሃቀኛ መዋቅራዊ ጉዳዮችን አንስታ በወቅቱ እንዳትወያይ ምክክሩን ቡርቅቅ አድርጎ ዋናውን አጀንዳ ማዘናጋት ሃይ የሚባል ተግባር ነው። የማንነት ኮሚሽንና የብሄራዊ እርቅ ኮሚሽን በመንግስት ተጠልፈው ምንም ፍሬ ሳያሳዩ እንደፈረሱት አይነት ነው።
ስለዚህ በኢትዮጵያ ሁኔታ የምክክር ኮሚሽን ስራ በሚገባ ካልተበየነ ወደፊትም ወደ ምክክር ገብተን ችግሮችን ልንፈታ አንችልም። በዚህ ሰዓት ሃገሪቱ በስርዓታዊ ሽብር ውስጥ ባለችበት ሰዓት አጀንዳዎችን ሰብሰብ አድርጎ በመዋቅራዊ ጉዳዮች ላይ ለሂቁ፣ የፓለቲካ ፓርቲ መሪዎች፣ የሃይማኖትና የሲቪክ መሪዎች በፍጥነት ወደ ውይይት መግባት ነበር የሚያስፈልጋቸው። ኢትዮጵያ ውስጥ ህዝብና ህዝብ ተጋጭቶ አያውቅም። በብሄሮች መካከል በባህል ግጭት የለም። አንዱ ብሄር የኔ ምግብ ይጣፍጣል ያንተ አይጣፍጥም ብሎ ጦርነት አያደርግም። ሌላው ብሄር የአንተ ልብስ አያምርም የኔ ያምራል ብሎ ጦርነት አይገባም። ቡድኖች የሚጋጩት ኢንስትሩመንታሊስት ወይም ብሄርን መሳሪያ አድርገው የሚያጋጩ ፓለቲከኞች ሲበጠብጡት ብቻ ነው። ህዝቡ ፓርቲዎቹን ወይ ተባበሩ ወይ ተሰባበሩ እያለ ተግባብተው እማራጭ ፖሊሲ እያመጡ እንዲመርጣቸው ነው የሚፈልገው።
እውነቱን ለመናገር በዚህ ሰዐት በኢትዮጵያ ውስጥ የብሄራዊ ምክክር አጀንዳዎች ግልፅ ናቸው። አጀንዳዎቹ አይደሉም የጠፉት። የምክክር ኮሚሽኑ አጀንዳ ፍለጋ ሃያ ሺ ስብሰባ ማድረግ የለበትም። የተቸገርነው አጀንዳ ሳይሆን በነዚህ አጀንዳዎች ላይ ሁሉን አቀፍ የሆነ ምክክር በጊዜው ማድረግ ነበር። ኮሚሽኑም ስራው ይሄ ሆኖ ሳለ የሃገሪቱን ምክክር ስራ ቡርቅቅ አድርጎ እያሰፋ ማወሳሰብ በእውነት ያሳዝናል። ይህ አካሄድ ለስልጣን ጥመኞች ጊዜ እየሰጡ እያስታመሙ ማኖር ነው አላማውና መቃወም ያስፈልጋል። የምክክር ኮሚሽን የሚቋቋመው ሃገራዊ ቀኖናዊ ችግሮችን ለመፍታት አይደለም። ቀኖናዊ ችግሮች በምርጫ በመድብለ ፓርቲ ስርዐት ይፈታሉ። የምክክር ኮሚሽን የሚያስፈልገው በሃገራዊ አይነኬ ዶግማዊ ጉዳዮች ላይ ለመግባባት ሃገርን በቋሚ ስርዐት ለማርጋት ነው።
ውይይት ወይም ምክክር ሲደረግ በውጤቱ ሮድማፕ ለማዘጋጀትና ለህገ መንግስት ማሻሻያ የሚሆኑ ሃሳቦችን ማምረት ነበር። በዚህ ሂደት ላይ ህዝቡ በአጀንዳዎቹ ላይ፣ በውይይቱ ሂደት ላይ ቀጥተኛ አስተያየት የሚሰጥበትን መድረክ ማዘጋጀት በርግጥ ተገቢ ነው። መጨረሻ ሮድማፑን የሚያጸድቀው ግን ህዝብ ነው። ይሁን እንጂ አጀንዳዎችን በማወሳሰብና በማንዘላዘል የምክክር ሂደትን ማጓተት ተገቢ አይደለም::
ለማናቸውም ዛሬም፣ ከዚህ በፊት እንደ ዜጋ ያጠናሁዋቸውን ብሄራዊ የምክክር አጀንዳዎች አካፍላለሁ።
ዋናው ጉዳይ ሃገራችን መቼም ቢሆን የምክክር ምእራፍን ወደ ጎን ትታ የረጋ መንግስት መስርታ ልትኖር አትችልም። ስለዚህ ሃቀኛ የምክክር ሂደት ውስጥ ስንገባ አጀንዳዎች እነዚህ ቢሆኑ ብሄራዊ ችግሮቻችን ይፈቱና ከዚያ በመለስ ያሉ የህዝብ ችግሮች በፖሊሲ እየታረቁ ይፈታሉ ብየ አምናለሁ። አጀንዳዎቹ የሚከተሉት ነበሩ።
- በህብረታችንወይምበአብሮነታችን ፍፁምነት ላይ ውይይት ያስፈልጋል ። ህብረታችንና የጋራው ቤታችን በምን ያህል አቅም ወይም በምን ያህል የአብሮነትና የወዳጅነት የቃልኪዳን ልክ ይታተ? የሚለው ዋና የምክክር አጀንዳ ነው። አሁን ያለው መተሳሰሪያ መርሆ የህብረታችንን ልክ በመገንጠል የወሰነው ሲሆን አሁን ይህንን የህብረት ልክ እንዴት እናሳድገው የሚለውን ቁልፍ ጉዳይ ነው :: ለዚህ ነው Toward a More perfect Union እያልኩ የፃፍኩት:: ውይይታችን የጋራውን ቤት ፍፁም ወደ ማድረግ እንዲሆን መወያየት ያስፈልጋል ::
- በቅርፀመንግስትላይ (Government Structure ) ምክክር ያስፈልጋል ። ቅርፀ መንግስት በምርጫ መንግስት ሲመጣና ሲሄድ የሚቀየር አይሆንም። በዚህ አንድ ኢትዮጵያን የመሰለ ቅርፀ መንግስት መስፋት አለብን። ይህ ጉዳይ ሀገሪቱ ፓርላመንታሪ ትሁን ወይስ ፕሬዝደንሺያል? የፌደራል ሥርዓቱ ምን መልክ ይያዝ? የመንግስት ቅርፁ ምን ይጨምር ምን ይቀንስ? ለምሳሌ የህገመንግስት ዳኛ ይኑር ወይስ እንዴት እንቀጥል ወዘተን ይመለከታል ::
- ብሄራዊማንነትንናየብሄር ማንነትን እንዴት እንንከባከብ። በምን አይነት ምህዋር ይዙሩ? እንዴት ሳይጠላለፉ ይኑሩ በሚለው ላይ ምክክር ያስፈልጋል። በማንነት ፖለቲካ ላይ ውይይት ያስፈልጋል:: Identity politics and Identity vote on the scale of democracy and justice መቀመጥ መመዘን አለበት::
- ብሄራዊምልክቶችንበተመለከተ መመካከር ያስፈልጋል። ባንዲራን መዝሙርን ወዘተ ይመለከታል።
- የመሬትላራሹጥያቄ ምክክር ውስጥ መግባት አለበት። የፓሊስ ቀጭን ጉዳይ አይደለም ይህ አጀንዳ።
- ያለፈመጥፎትውስታዎች እንዴት ይታዩ? (Past bad memories) የሚለውን ማንሳት ተገቢ ነው።
- ቋንቋናተግባቦትንበሚመለከት ውይይት ያስፈልጋል። ይህ ጉዳይ የአንድ ፓርቲ ፓሊሲ ሳይሆን የቋንቋ አያያዛችን ላይ የጋራ አቋም መያዝ ይቻላል።
ይህንን ካልኩ በሁዋላ ግን ሁላችንም እንደምናየው ሃገራችን ሁለንተናዊ ደህንነቷ ዛሬስ ከመቼውም ጊዜ ይልቅ አደጋ ላይ ወድቋል። አድሮ የተሻለ ነገር የለም። መንግስት ይህ ሁሉ ችግር እየተፈጠረ ጣቱን ሌላው ላይ እየጠቆመ ከመኖር ባሻገር የፖለቲካ ለውጥ ለማድረግ አልፈለገም። የኢትዮጵያ ህዝብ ደርግ እንዲወድቅ የታገለው፣ ህወሃት እንዲወድቅ የታገለው እነዚህ መሪዎች ህዝቡን ከአንድ መከራ ወደ ሌላ መከራ እየዘፈቁ ስለሄዱ ነው። ዶክተር አብይ ህዝቡን በኑሮ ውድነትና በሰላም እጦት፣ በመፈናቀልና በመከራ ብዛት ከደርጉና ከመለስ በልጠዋል። ስለዚህ ይበቃል። መንግስት ለሚከሰቱ ችግሮች ሁሉ ጣት መቀሰር አያዋጣውም። ይልቁን አሁን ዶክተር አብይም በክብር ስልጣን ያስረክቡና የተውጣጣ የሽግግር መንግስት ይቋቋም። ከዚያም ሃገሪቱ ወደ ብሄራዊ መግባባት ታዘንብል። ከፍ ሲል እንዳልኩት በምንም መልኩ ልንዘለው የማንችለው ምዕራፍ የብሄራዊ ምክክር ምዕራፍ ነው። ነገር ግን ዶክተር አብይ ብዙ ተቋማትን እንዳበላሹት ይህንን ተቋምም አበላሽተዋል። በዚህ ሁሉ ግን ሃገራችን ተስፋ መቁረጥ የለባትም። እንደ ሃገር የሽግግር መንግስት መስርቶ የጠዳ ብሄራዊ ምክክር ወደ ማድረግና ህብረትን ፍጹም ወደ ማድረግ ማሻገር የዚህ ትውልድ ትልቅ የቤት ስራ ሆኖ ይታያል። እንደሚታየው በዚህ ወቅት በሃገራችን የውስጥ ጉዳዮች ላይ የውጪ ጣልቃ ገብነት አይሏል። ስለዚህ ኢትዮጵያውያን ችግሮቻቸውን በረጋ መንፈስ ያለ ውጪ ጣልቃ ገብነት ማስተካከል አለባቸው። ከአለም አቀፉ ኮሚኒቲ ጋር ያለን ግንኙነት ጨለምተኛ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም ጠብቀን መራመድ ያስፈልጋል። በመሆኑም ነጻ የሆነ የሽግግር መንግስት መስርተን የፖለቲካ ለውጥ በማምጣት መረጋጋት ፈጥረን መተሳሰሪያ መርሆዎቻችንን ለማሻሻል ምክክር ውስጥ እንግባ። ለምክክር ሰላም ወሳኝ ነው። ጦርነቱ የሚያቆመውና ጊዚያዊ መረጋጋት የሚመጣው ሁሉን አቀፍ የሽግግር መንግስት ሲቋቋም ነው።
እግዚአብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ
http://amharic-zehabesha.com/archives/125663