*ሊባኖስ 96 በመቶ፣ ሱዳን 92 በመቶና ግብጽ 80 በመቶ የስንዴ ፍላጎታቸውን የሚያሟሉት ከሩሲያና ዩክሬን ነው:: ውድ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ-ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች እንደ ምን ሰነበታችሁ? በዛሬው ትንታኔዬ የዐረብ አገሮች ከውጭ አገሮች የሚያስገቡት ስንዴ ምን ያህል በሩሲያና ዩክሬን ላይ ጥገኛ እንደሆነ በዝርዝር አስቃኛችኋለሁ። ከዐረብ አገሮችም ሱዳን፣ የመንና ሊባኖስን ጨምሮ በርካቶቹ በሩሲያና ዩክሬን ጦርነት መዘዝ በገጠማቸው የስንዴ እጥረት የተነሳ የዜጎቻቸው ኑሮ እንዴት እንደተፈተነና የወሰዷቸውን መፍትሄ መንገዶች ሰፋ አድርጌ አቀርብላችኋለሁና በጥሞና ትከታተሉ ዘንድ በማክበር እጠይቃለሁ።
ውድ ወገኖቼ:- የዓለማችንን 17 በመቶ የተረጋገጠ ነዳጅ የያዘችው የምድራችን ቀዳሚ ነዳጅ አምራች አገር፤ ለመጠጥ የሚውል አንድ ሊትር ውሃ ከአንድ ሊትር ነዳጅ በሽያጭ ዋጋ የሚወደድባት በሰፊ ግዛቷ አንድም ወንዝ የሌላት የዓለማችን የበረሃ ምድር፤ የአውሮፓ አገሮቹ፦ ፈረንሳይ፣ ቤልጀየምና ኔዘርላንድስ እንደ አገር በቆዳ ስፋታቸው ቢደመሩ በትልቅነቱ የማይደርሱበትን “ረብ-አል ኬሃሊ” በረሃ በእቅፋቷ የያዘችው ሳዑዲ ዐረቢያ በዋናነት ስንዴ ከየት እንደምትሸምት ታውቃላችሁ የሚል እምነት አለኝ።
ይኸውም የዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት በምኅጻረ-ቃል “ፋኦ” የጎርጎሮሳዊያኑ ቀመር በ2021፤ “ለዐረብ ባህረ- ሰላጤና ለኦማን ባህረ-ሰላጤ የቀረበችው፤ በሰሜን፣ ምሥራቅና ደቡብ በረዥም የውሃ አካል በመከበቧ “የባህረ-ገብ መሬት አገር” የምትሰኘው የታወቀችው መርከብ ሠሪ የሰላምና የጸጥታ አገር “ኦማን” እና ሳዑዲ ዐረቢያ የፍላጎታቸውን ግማሽ ያህል ስንዴ የሚያስመጡት ከሩሲያና ዩክሬን ነው!” ሲል አረጋግጧልና።
ለነገሩ የሳዑዲ ዐረቢያ የምግብ ዋስትና ማረጋገጫ እጆች እስከ ኢትዮጵያና ሱዳን ለም መሬት ድረስ ዘልቀው ገብተው እንደሚያውቁ እናንተ ወገኖቼ ጠንቅቃችሁ እንደምትረዱ እገምታለሁ።
ይህ ብቻ አይደለም። ከዐረቡ ዓለም ከአስር ሰዎች ስምንቱ ከድህነት ወለል በታች ከሚኖሩባት፤ ከ18 ሚሊየን የሚልጡ ዜጎቿ ወደ ረሃብ ጎዳና እየተጓዙ ካሉባት፤ 15 ሚሊዮን የሚበልጥ ሕዝቧ ውሃና የንጽሕና መጠበቂያ በሚጠይቅባት፤ ከአራት ሚሊዮን የሚበልጡ ንጹሐን በእርስ በርስ ጦርነት በተፈናቀሉባት፤ ከአንድ መቶ ሺ የሚበልጡ ዜጎቿ በጦርነት ያለቁባት፤ ሁለት ሚሊዮን ሕጻናት ከትምህርት ገበታ የራቁባት፤ ሕጻናት መከላከል በሚቻል በሽታ እየተጠቁ በጥቂት ደቂቃዎች ወደ ሞት መንደር የሚቀላቀሉባት ጥንታዊቷ ዐረባዊቷ አገር የመንም ብትሆን እጅግ ከፍተኛ መጠን ያለው ስንዴ የምትገዛው ከሩሲያና ዩክሬን ነው።
ከዚሁ መረጃ ጋር በተያያዘ አምስት ሚሊዮን ያህል ሕዝብ ያላት ፍልስጤምን ብንመለከት፤ በጎርጎሮሳዊያኑ ቀመር 2020 ላይ በ3 ነጥብ 57 ሚሊዮን ዶላር በቀጥታ ከሩሲያ ስንዴ መግዛቷን እንረዳለን። ፍልስጤም በተመሳሳይ አመት በ5 ነጥብ 61 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ደግሞ ከዩክሬንና ሩሲያ የተገዛ ስንዴ በእስራኤል በኩል ወደ ግዛቷ እንዲገባ ማድረጓን በኢትዮጵያ አቆጣጠር የካቲት 25 ቀን 2014 ዓመተ-ምህረት ማለትም ማርች 04 ቀን 2022 የተነበበው የኢንቨስትመንት ሞኒተር ዘገባ ማመልከቱ የዐረብ አገሮች የስንዴ ፍለጋ የሩሲያና ዩክሬን ደጃፍን እንዴት እንደሚያንኳኳ ያሳያል።
ከሩሲያ ስንዴ ከገዙት መካከል ነጥለን ለማሳያነት ለመቃኘት ያክል፤ የእርስ በርስ ጦርነት ከመቀሰቀሱ ከጎርጎሮሳዊያኑ ቀመር 2011 በፊት በአገሯ ውስጥ ስንዴ በማምረት ዜጎቿን ትመግብ የነበረችው ሶሪያ፤ ጦርነት ባስከተለባት መዘዝ የተነሳ ወደ ውጭ አገሮች ለመማተር ተገድዳ፤ በተጠናቀቀው የጎርጎሮሳዊያኑ አመት 2021፤ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ቶን ስንዴ ከሩሲያ መግዛቷን በምጣኔ ሀብት ላይ አተኩሩ በየካቲት 2014 (ፌብሩዋሪ 2022) ለንባብ የበቃ የኅትመት ሰነድ ማመልከቱን የፈረንሳይ ዜና ማሠራጫ አዣንስ ፍራንስ ፕረስ የካቲት 18 ቀን 2014 ዓመተ-ምህረት ከካይሮ ባሠራጨው ዘገባ ላይ ተጠቅሷል።
በዓለምአቀፉ የንግድ ማዕከል መረጃ መሠረት ደግሞ፦ በጎርጎሮሳዊያኑ አመት 2020 ግብጽ በ2 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር ወጪ ከሩሲያና ዩክሬን ስንዴ በመግዛት ከዓለማችን ግንባር ቀደምትነቷን አረጋግጣለች።
እንዲሁም የመን 318 ነጥብ 7 ሚሊየን፣ ሞሮኮ 286 ነጥብ 7 ሚሊዮን እና ሱዳን 282 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዶላር አውጥተው ከዩክሬንና ሩሲያ ስንዴ መግዛታቸውን የዓለምአቀፉ የንግድ ማዕከል መረጃ ማመላከቱ፤ የዐረብ አገሮች የስንዴ ማግኘት ሕልውና በሩሲያና ዩክሬን የስንዴ አቅርቦት ክር ላይ ተንጠልጥሎ እንደሚገኝ አመላካች ነው።
ምን ይሄ ብቻ?! ከዐረብ አገሮች፦ ዓባይን፣ የዓባይ ገባሮችንና ዝናብን ተጠቅማ ለእርሻ ምቹ የሆነ ብዙ ሚሊዮን ሔክታር ለም መሬት ብታለማ “የዳቦ ቅርጫት ትሆናለች!” የሚል ትንበያና እምነት ተይዞላት ግና ያልተሳካላት፤ በተገላቢጦሹ
አፍሪካን በመፈንቅለ-መንግሥት በመምራት በአምባገነን መሪዎቿ የሌቦች አገዛዝ “ክሌፕቶክራሲ” ተገዝግዛ በስንዴ እጥረትና ዳቦ እጦት የዳቦ አመጽ የበረታባት፤ አገረ ሱዳን አንስቶ- ከሕዝቧ 45 በመቶ የሚሆነው ኀይል፤ እርሻን ጨምሮ በዓሳ እርባታና ደን ልማት የሚሳተፍባት በረሃማዋ የዐረብ አገር ሞሮኮ ስንዴን በስፋት የሚሸምቱት ከሩሲያና ዩክሬን እንደሆነ ልብ በሉልኝ።
በአሜሪካ ኢሊኖይስ ግዛት የሚሠራጨው “ፋርም ፖሊሲ ኒውስ” ማርች 30 ቀን 2022 ባቀረበው ትንታኔ ደግሞ በተለምዶ በዐረቢኛ “የማግሪብ” ማለትም “የፀሓይ መጥለቂያ” አሊያ ከሰሐራ በረሃ ሰሜን ወይም ከዓባይ (ናይል) ምዕራብ አቅጣጫ የሚገኙ ከሚባሉት አገሮች መካከል፦ ሞሮኮ፣ አልጀሪያና ቱኒዚያ፤ ከሩሲያና ዩክሬን ሁነኛ ስንዴ አስመጭዎች ናቸው በማለት ገልጿል።
ለምሳሌ በዐረቡ ዓለም በስንዴ እጥረት እየተፈተኑት ካሉት አገሮች መካከል፦ ዓለም በጎርጎሮሳዊያኑ ቀመር ኦውገስት 4 ቀን 2020 ወይም በኢትዮጵያ አቆጣጠር ሐምሌ 27 ቀን 2012 ዓመተ-ምህረት በጥንታዊቷ መናገሻ ከተማዋ “ቤይሩት”፤ በገጠመ የአሞኒየም ናይትሬት ፍንዳታ፤ ለአራት ወራት ለመጠባበቂያ ያስቀመጠችውን እህል ሙሉ በሙሉ የወደመባትን፤ ለአብነት ያህል በጎርጎሮሳውያኑ አመት 2020፤ በ119 ነጥብ 1 ሚሊዮን ዶላር ከዩክሬን፤ በ22 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዶላር ደግሞ ከሩሲያ ስንዴ የገዛችውን ሊባኖስን ዓለም ጠንቅቆ ያውቃታል።
በመካከለኛው ምሥራቅና አብዛኛው የእስያ አገሮች በገጠመ የስንዴና ሌሎች የምግብ እህል አቅርቦት የተነሳ በከፍተኛ ሁኔታ ለአደጋ ተጋልጣ የምግብ ዋጋ ንረት አንድ ሺ በመቶ (1,000 በመቶ) የጨመረባት የዓለማችን የኑሮ ፈተና አገር ሊባኖስ፤ 96 በመቶ የሚሆነውን ከውጭ አገሮች የሚመጣ ስንዴ የምትሸምተው ከሩሲያና ዩክሬን እንደሆነ
ሪስፖንስቢሊቲ ስቴት ክራፍት መካነ- ድር በመጋቢት 21 ቀን 2014 ዓመተ-ምህረት (ማርች 30 ቀን 2022) ዘገባው አመልክቷል። ሊባኖስ የሕዝቦቿ የስንዴ ዳቦ የማግኘት የረዥም አመታት ሕልውና የተመሠረተው በሩሲያና ዩክሬን ላይ ጥገኛ በመሆኑ የተነሳ በሁለቱ አገሮች መካከል በመካሄድ ላይ ያለው ጦርነት ሊባኖስ የዳቦ ስንዴ አጥታ እርጥባን እስከመለመን አድርሷታል ብሏል፤ የሪስፖንሲብል ስቴት ክራፍት ዘገባ።
የዐረብ አገሮች ከውጭ አገር ከሚያስመጡት ስንዴ ከግማሽ የሚበልጠውን ወደ አገር ቤት የሚያስገቡት ወደለየለት ጦርነት ውስጥ ገብተው እየተቆራቆሱ ካሉት ሩሲያና ዩክሬን መሆኑን ሪስፖንስቢሊቲ ስቴት ክራፍት ዘገባ አመልክቶ፤ ሊባኖስ 96 በመቶ፣ ሱዳን 92 በመቶና ግብጽ 80 በመቶ የሚሆነውን የስንዴ ፍላጎታቸውን የሚያሟሉት ከሩሲያና ዩክሬን ነው ሲል ጠቅሷል። እንደሚታወቀው በጎርጎሮሳዊያኑ ቀመር ከ2007 እስከ 2008 በገጠመ ድርቅ የተነሳ የስንዴ፣ ሩዝና ነዳጅ ዋጋ እጅጉን መጨመርን ተከትሎ በዐረቡ ዓለም የዳቦ አመጽ ወይም የፀደይ አብዮት በመቀስቀሱ በበርካታ የዐረብ አገሮች ብዙ ሰዎች ለሞት፣ ለመቁሰልና መፈናቀል ሲዳረጉ ቱኒዚያና ግብጽን ጨምሮ በአንዳንድ የዐረብ አገሮች መንግሥታዊ ለውጥ ተስተውሏል። በወቅቱም በነበረ የኑሮ ውድነት መዘዝ በዓለማችን ከአርባ (40) በላይ አገሮች አመጽ መካሄዱ ይታወሳል።
ከየካቲት 16 ቀን 2014 ዓመተ-ምህረት ጀምሮ በሩሲያና ዩክሬን መካከል በመካሄድ ላይ ያለው ጦርነት ደግሞ በዓለምአቀፍ ገበያ የእህል አቅርቦት እጥረት እንዲገጥምና የምግብ ዋጋ እንዲጨምር በማድረግ በበርካታ የዐረብ አገሮች ላይ የረሃብ አደጋ መደቀኑንና ድህነትን እያባባሰ እንደሚገኝ በተባበሩት መንግሥታት የዓለምአቀፉ የእርሻ ልማት ፈንድ ፕሬዚዳንት የሆኑትን ጊልበርት ሆውንግቦ ጠቅሶ ፋይናንሻል ታይምስ በኢትዮጵያ አቆጣጠር መጋቢት 12 ቀን 2014 ዓመተ-ምህረት (ማርች 21 ቀን 2022) ከሎንዶን ባሠራጨው ዘገባ አመልክቷል።
እነሆም ምዕራባውያን ቢጢዎቻቸውን አስተባብረው በሩሲያ ባንኮች፣ የመርከብ ጭነት አመላላሾችና የአውሮፕላን በረራዎች ላይ ማዕቀብ ከመጣላቸውን በተጨማሪ ጦርነቱን ተከትሎ ሩሲያና ዩክሬን ስንዴና ዘይትን ጨምሮ ሌሎች መሠረታዊ የፍጆታ እቃዎች ወደ ውጭ መላክን በማቋረጣቸው በዓለም ገበያ የምግብ ሸቀጦች አቅርቦት እጥረት እንዲገጥምና የዋጋ ግሽበት እንዲባባስ መንስኤ በመሆን ዓለምአቀፍ ንግድ (global trade) እንዲዛባ አድርጓል።
በአሁኑ ወቅት በዐረብ አገሮች ያለው ትልቁ ጥያቄ ዓለም ከጧት እስከ ማታ ስሙን ጠርቶት የማያጠግበውን፣ ከማለዳ እስከ ምሽትና ከምሽት እስከ ንጋት በናፍቆት የሚመለከተውን፤ ስሙንና ጥቅሙን በመልካምነት ጎን- ደጋግሞ የሚያነሳውን፤ “በየትኛውም የዓለም ክፍል ያለ የኅብረተሰብ ክፍል ወዶና ፈቅዶ የሚመገበው!” ተብሎ፤ ስሙና ግብሩ ገዝፎ፤ እንደ ትልቅ አደራ ከዘመን ዘመን ተላልፎ፤ በየዕለቱ ለምግብነት እየዋለ የሚገኘውን ተወዳጁን የምግብ ዓይነት “የስንዴ ዳቦ” ለብዙ መቶ ሚሊየኖች እንዴት እናቅርብ? ከሆነ ውሎ አድሯል።
በመሆኑም በጊዜያዊ መፍትሄነት አንዳንዶቹ አገሮች “የሆድ ነገር ሆድ ይቆርጣል! የዳቦ ነገር ጊዜ አይሰጥም! የሕዝብ አመጽን አባብሶ ወደ መንግሥት ግልበጣና ቅያሬ ሊያመራ ይችላል?” ብለው በመስጋት የሩሲያና ዩክሬን ጦርነትን መቋጫ ቀን እየናፈቁ ለተጨማሪ ስንዴ ግዢ ወደ ሕንድ፣ ዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ፣ ፈረንሳይ፣ ሩማኒያ፣ ካዛክስታን፣ ሞልዶቫ፣ አውስትራሊያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ አርጀንቲና ሌሎች አገሮች በመሯሯጥ ላይ ይገኛሉ። ለአብነትም ግብጽንና ሊባኖስን መጥቀስ ይቻላል።
በተለይ ሊባኖስ የሚላስና የሚቀመስ አጥታ፤ በሕዝቦቿ ተደጋጋሚ የዳቦ ጥያቄ መከራዋን አይታ፤ “ወይ ስንዴ ሽጡልኝ አሊያ እርዳታ ስጡኝ!?” በማለት አፍ አውጥታ እርጥባን እስከ መጠየቅ ደርሳለች።
የአገራቸው የስንዴ ምርት ወደ ሌሎች አገሮች እንዳይሸጥ የከለከሉና ለአገር ውስጥ ፍጆታ እንዲውል የወሰኑ፤ ለዳቦ ስንዴ ዱቄት ድጎማ በጀት የመደቡ፤ የግልና የማኅበራት ስንዴና የስንዴ ዱቄት አስመጪና አከፋፋዮች፣ የስንዴ ዱቄትና ዳቦ ነጋዴዎች፣ የስንዴ ውጤት ተጠቃሚ የምግብ አምራች ድርጅቶች ወዘተ ኢ-ፍትሀዊ የዋጋ ጭማሪ እንዳያደርጉ መመሪያና ትዕዛዝ እስከ ማስተላለፍ የደረሱ አገሮችም አሉ።
ለምሳሌ የሞሮኮ በጀት ሚኒስትር ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ መንግሥት በአገሪቱ የገጠመውን የስንዴ እጥረት ከግምት ውስጥ በማስገባት ለዳቦ ስንዴ ዱቄት ድጎማ አራት መቶ ሚሊዮን ዶላር መመደቡን መናገራቸውን ፍራንስ 24 በየካቲት 18 ቀን 2014 ዓመተ-ምህረት ካሠራጨው ዘገባ ለመረዳት ተችሏል።
የዐረቡ ዓለም የፀደይ አብዮት ጥሩ ትምህርት ስለሆናቸው ከዩክሬንና ሩሲያ ጦርነት በፊት ቀደመው በገዙት ተቀማጭ ስንዴ ተማምነው ለጊዜው ለገጠማቸውን የከበደ
የዳቦ ጥያቄ ምላሽ የሰጡ የዐረብ አገሮችም ይገኙበታል። በዚህ ረገድ ከሚጠቀሱት መካከል ቱኒዚያ ትገኝበታለች።
ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆነው የቱኒዚያ ግብርና ሚኒሰቴር ባለሙያ የሆኑት አብድልሀሊም ጋስሚ ለአዣንስ ፍራንስ ፕረስ በሰጡት መግለጫ፤ ቱኒዚያ ከውጭ ከምታስገባው ስንዴ 60 በመቶ ያህሉ ከዩክሬንና ሩሲያ እንደሚመጣና በሁለቱ አገሮች መካከል ጦርነት ቢቀሰቀስም ቱኒዚያ እስከ ሰኔ ድረስ መጠቀም የሚያስችላት ተቀማጭ ስንዴ አላት ሲሉ መናገራቸው ነው።
በጥቅሉ በነዳጅ አምራችና ላኪነት ስማቸው የሚጠራው ባለሃብቶቹ ሳዑዲ ዐረቢያና የተባበሩት ዐረብ ኢሜሬቶችን ጨምሮ ሊቢያና ሌሎች በርካታ የዐረብ አገሮች እጅግ ጥገኛ ባደረጋቸው ሁኔታ አብዛኛውን መጠን ስንዴ ከዩክሬንና ሩሲያ እንደሚገዙና በዩክሬንና ሩሲያ መካከል የሚካሄደው ጦርነት ምን ያህል የዐረቡን ዓለም የዳቦ ማግኘት እጣ ፈንታ እንደ ወሰነው ከላይ ከቀረበው ሰፊ ዘገባ ለመረዳት ችላችኋል የሚል እምነት በመያዝ ለዛሬ ያዘጋጀሁትን ሰፊ ዘገባ እዚህ ላይ እቋጫለሁ።
በመጨረሻም ቸሩ እግዚአብሔር አገራችንን ይጠበቅልን!
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!
የኢትዮጵያ አምላክ አገረ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይባርክ!
(ጌታቸው ወልዩ)