(ዘ-ሐበሻ) የዳላስ/ቴክሳስ ሚዲያዎች ትናንት ቅዳሜ በፌር ፓርክ አካባቢ የአንድ ሰው ሕይወት መኪና ከባቡር ጋር ተጋጭቶ መጥፋቱን ዘግበው ነበር። የዘ-ሐበሻ የዳላስ ምንጮች እንደጠቆሙት ከባቡሩ ጋር በመኪና ተጋጭታ ሕይወቷ ያለፈው ኢትዮጵያዊት ናት።
የዳላስ ፖሊስ ትናንት ማምሻውን በሰጠው መግለጫው ባቡሩ መንገዱን በሚያቋርጥበት ወቅት መብራቶች እና ደውሎች እየተሰሙ የነበሩ ቢሆንም መኪናው ውስጥ የነበረ ሹፌር ይህን ደውልና መብራት ባለማስተዋል በሚያቋርጥበት ወቅት አደጋው ደርሷል። ከዳላስ በደረሰን መረጃ መሠረት በዚህ አደጋ ሕይወቷ ያለፈው ኢትዮጵያዊት ስትሆን ስሟም ሜላት ማሞ እንደሚሰኝ ከፎቶ ግራፏ ጋር የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
በዳላስ ፖሊስ መረጃ መሠረት የተሳፋሪዋ ባቡሩና መኪናዋ በፈጠሩት ግጭት የተሳፋሪዋ ሕይወት ወዲያውኑ አልፏል። ይህን ተከትሎ በዳላስ ያሉ ኢትዮጵያውያን በወገናቸው ሕልፈት የተሰማቸውን ሃዘን በመግለጽ ላይ ይገኛሉ።
እንደፖሊስ መረጃ ባቡሩ 24 ሰዎችን ይዞ ይጓዝ የነበረ ሲሆን ማንም ሰው ወደ ሆስፒታል ባይወሰድም 4 ሰዎች ጉዳት ደርሶብናል ብለዋል።
ሜላት ሃገሯን እና ወገኗን ወዳድ እንደነበረች የሚያውቋት የሚመሰክሩ ሲሆን በቅርቡ በሳዑዲ አረቢያ በወገኖቻችን ላይ የደረሰን ጥቃት ተከትሎ በዳላስ በተደረገው የተቃውሞ ሰልፍ ላይ ከኢትዮጵያውያን ጋር በመሆን ድምጿን ስታሰማ ነበር። (ፎቶው ከታች አያይዘነዋል)።
ፈጣሪ ነብሷን በገነት እንዲያኖረው ዘ-ሐበሻ በዚህ አጋጣሚ ሃዘኗን ትገልጻለች።