ኢትዮጵያ፣ ማሊ እና ጊኒ ከአጎዋ የንግድ ሥምምነት ተሰረዙ

January 2, 2022

የኢትዮጵያ፣ የማሊና የጊኒ መንግሥታት “የአጎዋን ደንብ የሚጥሱ እርምጃዎች በመውሰዳቸው” ከታኅሳስ 23 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ከአጎዋ የንግድ ሥምምነት ውጪ መሆናቸውን የፕሬዝደንት ጆ ባይደን አስተዳደር አስታወቀ። ኢትዮጵያ ተፈጽመዋል የሚባሉ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች፤ ማሊና ጊኒ መፈንቅለ-መንግሥት በአጎዋ በኩል የነበራቸውን ዕድል አሳጥቷቸዋል

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር ኢትዮጵያን ከአጎዋ የንግድ ሥምምነት መሠረዙን አስታወቀ። የአሜሪካ የንግድ ተወካይ መሥሪያ ቤት ትናንት ቅዳሜ ባወጣው መግለጫ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ማሊ እና ጊኒ ከሥምምነቱ መሠረዛቸውን ይፋ እንዳደረገ የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።

በመግለጫው መሠረት የኢትዮጵያ፣ የማሊ እና የጊኒ መንግሥታት “የአጎዋን ደንብ የሚጥሱ እርምጃዎች በመውሰዳቸው” ከትናንት ታኅሳስ 23 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ አሜሪካ ለአፍሪካ አገራት ከ22 አመታት በፊት ካበጀችው የንግድ ሥምምነት ውጪ ሆነዋል።

አጎዋ የተወሰኑ የብቃት መሥፈርቶች የሚያሟሉ ከሰሐራ በርሐ በታች የሚገኙ የአፍሪካ አገራት ከ1 ሺሕ 800 በላይ የሸቀጥ አይነቶችን ቀረጥ ሳይከፍሉ በአሜሪካ ገበያ እንዲሸጡ የሚፈቅድ የግብይት ሥርዓት ነው።

የአፍሪካ አገራት ከሥምምነቱ ተጠቃሚ ለመሆን ማሟላት ከሚጠበቁባቸው ቅድመ-ሁኔታዎች መካከል ሰብዓዊ መብቶችን መጠበቅ የሚለው ይገኝበታል።

የአሜሪካ የንግድ ተወካይ መሥሪያ ቤት ትናንት ቅዳሜ ባወጣው መግለጫ “በሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት ምክንያት በመንግሥት እና ሌሎች አካላት ዓለም አቀፍ እውቅና የተሰጣቸው ሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ጥሰት” አሜሪካን እንደሚያሳስብ ገልጿል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ከአንድ ሣምንት በፊት አሜሪካ ውሳኔዋን እንድታጤን ጠይቆ ነበር። የኢትዮጵያ የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ታኅሳስ 18 ቀን 2014 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ “ኢትዮጵያን ከአጎዋ የንግድ ሥምምነት ማስወጣት አሁን በአገሪቱ ከተፈጠረው ቀውስ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸው ንጹኃን ሰዎች ሕይወት እና ኑሮ ላይ የሚያሳድረው ጉዳት ከፍተኛ እንደሚሆን” አስጠንቅቋል።

DW

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Previous Story

የጦቢያ ዘመን አቆጣጠር ከፈረንጅ ዘመን አቆጣጠር አንጻር – መስፍን አረጋ

Next Story

አዲሱ የህወሓት-ህዝብ እብደት!

Go toTop