“የጠላት ፍላጎት ኢትዮጵያን በኮንፌዴሬሽን ከፋፍሎ ሁላችንንም ሀገር አልባ ማድረግ ነው” ፦ አርቲስት ቴዎድሮስ ተሾመ

November 25, 2021

የጠላቶቻችን ፍላጎት ኢትዮጵያን በኮንፌዴሬሽን በመከፋፈል ሁላችንንም ሀገር አልባ ማድረግ መሆኑን በመረዳት መላው ኢትዮጵያውያን በአንድነት በመነሣት የሀገር ዘብ መሆን እንደሚገባ አርቲስት ቴዎድሮስ ተሾመ ገለጸ።

ጠላቶቻችን ስንቆራረስ የሚገምጡን ዘጠኝ አሻንጉሊቶችን አሜሪካ ውስጥ አስቀምጠውልናል ብሏል አርቲስት ቴዎድሮስ ተሾመ።

የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዙፋናቸውን ትተው ሀገር ለማዳን ወደ ግንባር ሲዘምቱ እኛ ቆመን ልናይ አይገባም ያለው አርቲስቱ፣ ኢትዮጵያ ላይ የተቃጣውን የኅልውና አደጋ ለመቀልበስ ባለን እውቀት እና ልምድ ሁሉ ለሀገር ዘብ ሆነን መቆም እንደሚገባ ገልጿል።

ወደ ግንባር ልሂድ ወይስ ባለሁበት በሙያዬ እና በልምዴ ዘመቻውን ላግዝ በሚል ከራሱ ጋር ትግል ካደረገ በኋላ በሙያዬና ባለኝ ልምድ ብታገል ይሻላል በሚል በተለያየ መልኩ ትግል ሲያደርግ መቆየቱን ያስታወሰው አርቲስት ቴዎድሮስ ተሾመ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጦሩን በግንባር ሆነው ለመምራት መወሰናቸውን በመግለጽ ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን ለመታደግ አብረዋቸው እንዲዘምቱ ያቀረቡትን ጥሪ ተከትሎ ወደ ግንባር በመሄድ ባለው እውቀት እና ልምድ ለሀገሩ ዘብ ለመቆም መወሰኑን አብራርቷል።

በዚህ ጊዜ መመለስ ያለበት ጥያቄ ጠላቶቻችን እንደተመኙልን በሀገራችን ሁለተኛ ዜጋ ሆነን እንኑር ወይስ በተባበረ ክንድ የሀገራችንን ኅልውና አስጠብቀን የሀገር ባለቤትነታችንን እናረጋግጥ የሚል መሆኑን አመልክቷል።

እየተሠራ ያለው ሁሉም ሰው ሀገር እንዳይኖረውና የሀገሩ ባለቤት እንዳይሆን በመሆኑ የተደቀነብንን የሉዓላዊነት እና የኅልውና አደጋ በመቀልበስ ለልጆቻችን የምናወርሳት ሀገር እንድትኖረን ማድረግ ይገባል ማለቱን ኢፕድ ዘግቧል።

እንደ አርቲስት ቴዎድሮስ ገለጻ፤ የትኛውም ዜጋ ተረጋግቶ ሥራውን የሚሠራው እና ነገውንም ማለም የሚችለው የሀገር ሉዓላዊነት እና ኅልውና ሲረጋገጥ ነው።

ስለሆነም ዛሬ ላይ ባለን አቅም ለሀገራችን ዘብ ቆመን ማዳን ካልቻልን ነገ ለልጆቻችን የምናስረክባት ኢትዮጵያ ስለማትኖር በታሪክ ስንወቀስ እንዳንኖር የጠቅላይ ሚኒስትሩን እና የሌሎችንም ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን አርዓያነት በመከተል በምንችለው ሁሉ የተጣለብንን ሀገር የማዳን እና ትውልድ የማቆየት ኃላፊነት እንወጣ ሲል ጥሪውን አቅርቧል

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Previous Story

“በሰላም የኢትዮጵያ ብልጽግና ሚረጋገጥበትን መንገድ መስራት ብቻ ነው ምፈለገው… ተላላኪ መንግስ ኢትዮጵያ ውስጥ አይፈጠርም።” – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

Next Story

በሰኔ 15ቱ የባለስልጣናት ግድያ ተጠርጥረዋል በሚል ላለፉት 2 ዓመታት ከ6 ወራት የታሰሩት የጦር መኮንኖች በህልውና ዘመቻው ምክንያት አቃቢ ህግ ረዥም ቀጠሮ እንዲሰጥ መጠየቁን ተቃወሙ

Go toTop