የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ (ሸንጎ)
Ethiopian People’s Congress for United Struggle (Shengo) www.ethioshengo.org [email protected]
መጋቢት 7፣ 2008፣ ማርች 14፣ 2016
ጠቅላይ ሚኒስቴር ሐይለማርአም ደሳለኝ ከጥቂት ቀናት በፊት ለፓርላማው ባቀረቡት ዘገባ ውስጥ ጨምረው በሀገራችን ባሁኑ ሰአት በተለይም በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ጎልቶ የሚታየውን የህዝን መነሳሳት ከመልካም አስተዳደር መጥፋትና ከስርአቱ ብልሽት ጋር የተያያዘ እንደሆነ ለተፈጸመው በደል ተጠያቂ እንደሆኑም አምነው “ይቅርታ “ ጠይቀዋል።
እጅግ የዘገየ ቢሆንም ሀላፊነት እወስዳለሁ ፣ ለተሰራው ወንጀልም ተጠያቂ ነን ማለትና ይቅርታ መጠየቅ አበረታች ነው። ሆኖም ይሀ ተራ ቃል ብቻ እንዳይሆን በግልጽ በተግባር ሊታገዝ ይገባዋል።
ሁሉም እንደሚያውቀው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከተቀሰቀሰው የህዝብ መነሳሳት ጋር በተያያዘ ሰበብ ወደ እስር የተወረወሩ የፖለቲካ መሪወች ለምሳሌ አቶ በቀለ ገርባ እና በሽወች የሚቆጠሩ ዜጎች ይገኛሉ። በወልቃይትና ጠገዴም እንዲሁ ተመሳሳይ ሁኔታወች ተከስተዋል። ስህተተኛ ነን ካሉ፣ ጠቅላይ ሚኒስቴሩ እነዚህን ያላግባብ ታሰረው የሚማቅቁ ወገኖቻችንን ሁሉ ባስቸኳይ ከእስር መፍታት ይጠበቅባቸዋል። የተፈጠረው ስህተትና ቀውስ ከራሱ ከስርአቱ ፖሊሲና አሰራር የመነጨ መሆኑን ካመነ ፣ መሰረታዊ መብታቸውን በመግለጽ ላይ እያሉ የታሰሩ ሁሉ አሁኑኑ ከእስር መለቀቅ አለባቸው።ቀጣይ የመብት ረገጣውንም አሁኑኑ ማስቆም ያሰፈልጋል።
ደጋግመን እንዳልነው ሁሉ ከዚህም በተጨማሪ በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች ህይወታቸው ለጠፋው ፣ ንብረታቸው ለወደመው ሁሉ አስፈላጊውን ካሳ መክፈል የግድ ይላል። ከሁሉም በላይ ደግሞ ፍትህን ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ ነውና የዚህን ወንጀል ሁኔታ በነጻ የሚመረምር ከተለያዩ ህብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጣ አጣሪ አካል መስርቶ ያለአንዳች ጣልቃ ገብነት ተግባሩን እንዲያከናውን ውጤቱንም ባጭር ጊዜ በይፋ ለህዝብ እንዲያሳውቅ ማድረግ ትእዛዙን የሰጡም ሆኑ በስላማዊው ህዝብ ላይ ጥቃት የፈጸሙ ሁሉ በይፋ ለፍርድ ባስቸኻይ እንዲቀርቡ ማድረግ ያሰፋልጋል።
ይህ ሳይሆን “ይቅርታ ጠይቀናል፣ ሀላፊነት እንወስዳለን “ ወዘተ የሚሉ ቃላቶች ተራ ቃላት ብቻ ሆነው ይቀራሉ። ያለፉት 24 አመታት ከስርአቱ መሪወች ተመሳሳይ በተግባር ያልተደገፈ ንግግርን በተደጋጋሚ እንደሰማን የሚዘነጋ አይደለም። ይህ ደግሞ የህዝባችንም ቁጣ ይበልጥ ያብሰዋል እንጂ ሊያበርደው ከቶውንም አይችልም።
በመጨረሻም በተደጋጋሚ እንደገለጽነው ስርአቱ ለ24 አመታት እንዳደረገው በማፈን፣ በመግደል፣ በመከፋፈልና የህዝብን ጥያቄ በማስፈራሪያነት በመጠቀም ለመቀጠል የማይችልበት ሁኔታ ላይ እንደደረሰና ሀገራችንም አስፈሪ ወደሆነ ቀውስ እንደተገፋች ተገንዝቦ ራስን ከማታለል ተላቆ የሀገሪቱን ችግሮች ሁሉን አቀፍ በሆነ በብሄራዊ መግባባትና በብሄራዊ እርቅ ለመፍታት ሳይዘገይ ተጨባጭ እርምጃ መውሰድ አለበት አንላላን። የሀገራችን ውስብስብ ችግሮች ባንድ ድርጅት ብቻ ሊፈታ እንደማይችል መገንዘብ የግድ ነው።
ለስርአቱ ቅርበት ያላችሁ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ያለውን እውነታ በጊዜ ተገንዝባችሁ አደጋውን ለመቀነስና የኢትዮጵያን ህዝብ የነጻነት ፍላጎት ተግባራዊ ለማድረግ ከህዝብ ጎን እንድትሰለፉ በድጋሜ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
በተደጋጋሚ እንዳሳየነው ብሄራዊ መግባባትና እርቅ እንዲሁም ሀላፊነት እወስዳለሁ ማለት ካንገት በላይ ሳይሆን ከልብ መሆን አለበት።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ
Tel: 44 7937600756 , +1 9168486790 E-mail : [email protected]