
አማራ ሕዝብ የገጠመውን መንግሥት መር የዘር ጭፍጨፋ ለማስቆም የኅልውና ትግል ከጀመረ ሃያ ወራትን አስቆጥሯል።
በእነዚህ ወራት በተበታተነ መልኩ ይሁን እንጅ በጠላት ላይ ቁሳዊ፣ ሰዋዊ፣ አዕምሯዊና መሰል ኪሳራዎችን ማድረስ ተችሏል። በስም መከላከያ የሚባለውን ወራሪ ሠራዊት በማፍረስ በኩልም አስደናቂ ተግባራት ተከናውነዋል። አማራውን በማጥፋት እብደት ውስጥ ቀጥተኛ ሱታፌ እያደረገ የሚገኘው የአብይ አሕመድ ደንገጡር የክልሉ ካድሬ መዋቅር ብትንትኑ ወጥቶ እንቅልፍ አልባ የዛፍ ላይ ሕይወትን በመግፋት ላይ ይገኛል፤ ጥቂት የማይባሉትም እጃቸውን ሰጥተዋል።
“ኅልውናችን በተባበረ ክንዳችን” ነውና ከቀጠናዊ አደረጃጀቶች የተሻገረ ወጥ የሆነ አንድ ተቋም በመቋጨት ዋዜማ ላይ አንድ አማራዊ ተቋም መገንባት ያለውን ፋይዳ አመላካች ተግባርን ዛሬ መጋቢት 10/2017 ዓ.ም ላይ በመላው የአማራ ግዛቶች ጠላት በሚገኝባቸው ካምፖችና ምሽጎች ሁሉ ከሌሊቱ 10:00 ጀምሮ ማጥቃት ጀምረናል። ይህ በአንድነት እየተከናወነ የሚገኘው የማጥቃት ኦፕሬሽን በቀጣይ ገቢራዊ ለምናደርገው አንድ አማራዊ ተቋም እንደመስፈንጠሪያ ጉልበት ይሆነናል።
የድላችን መቋጠሪያ፣ የኅልውናችን ማረጋገጫ መንገዱም ስልተ ጥበቡም አንድ ነው፤ እሱም አንድነት። መታገያ ጉዳያችን “ኅልውናችን” ዓለማና ግባችንም የታወቀ አንድ ጉዳይ እንደያዘ አካል አንድ አታጋይ ተቋምን ገቢራዊ ማድረግ ለነገ የማንለው ቁልፍ ጉዳይ እንደሆነ ብናምንም በትግል ሜዳችን የተሰገሰጉ ከኅልውና ትግላችን በተቃራኒ የቆሙ በታጋይነት ጭንብል የተጀቦኑ አስተሳሰቦች፣ ቡድኖችና አደረጃጀቶች ገቢራዊ ከምናደርገው አንድነታችን እንድንዘገይ አደረገን እንጅ አማራዊ አንድነቱን ገቢራዊ ከማድረግ አያስቆሙንም። በአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል የሚቆምሩትን፣ የሚቀልዱትን ግብራቸው፣ እኔነት አስተሳሰባቸው፣ ከፋፋይነታቸው፣ ግጭት ጠማቂነታቸው፣ ከሥርዓቱ ጋር ድብቅ ጋብቻቸው፣ የሥልጣንና የገንዘብ ፍትወታቸው ሕዝባችንም ታጋዩም በውል የተረዳበት ሰዓት ላይ እንገኛለን።
እንደዚህ ያሉትን ጸረ አንድነት ኃይሎችን እያራገፍን የሕዝባችንን ኅልውና በአንድ ተቋምነት ማረጋገጥ ደግሞ በየቀጠናችን የተወሸቁ እንቅፋቶችን ተራምደን፣ ሳይረዱ በጠላት ጎራ የተሰለፉትን ጉዳዩንም መርምረው እንዲመለሱ ጥሪ እናቀርባለን።
በአጠቃላይ ከዛሬ መጋቢት 10/2017 ዓ.ም ጀምሮ በጠላት ላይ ጥቃት የመሰንዘር ወታደራዊ ኦፕሬሽን በአራቱ ጠቅላይ ግዛቶች በሚገኙ ወታደራዊ አዛዦች ቅንጅት እየተከናወነ የሚገኝ አኩሪ ተግባር ነው። በዚህ ተናባቢና የአንድነት ዘመቻ የአማራ ፋኖ በወሎ (ቤተ-አማራ)፣ የአማራ ፋኖ አንድነት በጎንደር፣ የአማራ ፋኖ በሸዋ እና የአማራ ፋኖ በጎጃም ቀጥተኛ ተሳታፊዎች ናቸው።
ዛሬ በወታደራዊ አዛዦች ፊታውራሪነት አፈሙዛችንን በአንድ እለት፣ በአንድ ሰዓት የማስተባበርና የማቀናጀት ተግባር ብርቱ ጉልበታችንን ከማሳዬት ባሻገር አንድ አስተሳሰብ ያለን መሆናችንን በገቢር ያሳየንበት የሠራዊታችንን እንዲሁም የሕዝባችንን ተስፋ ያለመለምንበት ድንቅ ሥራ መሆኑ ሥራችን ምስክር ነው። “ዘመቻ አንድነት” ዛሬን ጨምሮ ለሚቀጥሉት ተከታታይ ቀናት ተጠናክሮ የሚቀጥል ሆኖ አንድ አማራዊ ተቋም በመገንባትም የሕዝባችንን ኅልውና ያረጋግጣል።
ኅልውናችን በተባበረ ክንዳችን!!!
“ዘመቻ አንድነት”
የአማራ ፋኖ አንድነት በጎንደር
የአማራ ፋኖ በሸዋ
የአማራ ፋኖ በጎጃም
የአማራ ፋኖ በወሎ