
ሁለቱ ኃይሎች “ለሰላም ለሚደረጉ ሀገራዊም ሆነ ዓለም አቀፋዊ ጥሪዎች እና ጥረቶች መሳካት የድርሻቸውን እንዲወጡም” አሳስበዋል።
ዶ/ር ደሳለኝ ይህን ያሉት፤ ዛሬ ሐሙስ መጋቢት 11፤ 2017 እየተካሄደ ባለው የተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብስባ ላይ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጥያቄ ባቀረቡበት ወቅት ነው። የፓርላማ አባሉ ጥያቄያቸውን ከማቅረባቸው አስቀድሞ፤ የኢትዮጵያን ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ የተመለከተ ጠንከር ያለ ግምገማቸውን አስደምጠዋል።
የባህር ዳሩ የፓርላማ ተወካይ በዚሁ ግምገማቸው ማጠቃለያ ላይ ያነሱት ጥያቄ ከዚህ በታች ቀርቧል፦
“ባለፉት ሰባት ዓመታትና ከዚያም በፊት ባሉ አስርት አመታት፤ በኢትዮጵያ ውስጥ በተለይም በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በአፋር፣ በትግራይ፣ በደቡብ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በጋምቤላ እና በሌሎችም አካባቢዎች ለተፈጸሙ ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች (gross human rights violations)፣ በሰብዓዊነት ላይ ለተፈጸሙ ወንጀሎች (crime against humanity)፣ የጦር ወንጀሎች እንዲሁም የዘር ማሳሳት እና የዘር ማጥፋት ወንጀሎች መፈጸማቸውን መንግስት እውቅና የማይሰጠው እና ኃላፊነት የማይወስደው እንዲሁም ገለልተኛ ዓለም አቀፍ ምርመራዎች እንዲካሄድ የሚደረጉ ጥሪዎችን የሚያጣጥለው ለምንድነው?”
“የሽግግር ፍትህ ከመጀመሩ በፊት እነዚህ ወንጀሎች በገለልተኛ ዓለማቀፍ ተቋማት ተመርምረው የተፈጸሙ ወንጀሎች እንዲለዩ እና በስማቸው እንዲጠሩ መደረግ አለበት። ከዚያም ጥፋት ፈጻሚዎችን ለፍርድ ማቅረብ እና ተጎጂዎችን መካስ…ወዘተ፤ የሽግግር ፍትህ ሂደቱ አካል እንዲሆኑ ሊደረግ ይችላል። እንደ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን አይነት ሂደቶች የሀገራችንን ችግሮች እንዲፈቱ ከልብ የምንፈልግ ከሆነ፤ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልል እየተካሄዱ ያሉ ጦርነቶች፤ አውዳሚ ወንድማማች ጦርነቶች በአስቸኳይ እንዲቆሙ፣ silencing the guns መደረግ አለበት።”
“የሰሜኑ ጦርነት እንዲቆም ያደረገው ዋነኛው አካል የፌደራል መንግስቱ ሲሆን አሁንም በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢ ያሉ ጦርነቶችን የማስቆም ተቀዳሚ ኃላፊነቱ፣ የሞራል እና የታሪክ ተጠያቂም የሚወድቀው በፌደራል መንግስቱ ላይ ነው። መንግስታዊ ያልሆኑ ተፋላሚዎች ኃላፊነታቸው በሁለተኛ ደረጃ የሚታይ ነው።
“ዘመናዊ የሀገራችን ታሪክ ብናይ እንኳን ለመቶ አመታት የፖለቲካ ችግሮቻችን በጠመንጃ አፈሙዝ ለመፍታት የሄድንበት እና ዛሬም የቀጠልንበት መንገድ፤ የአለም ጭራ የሌሎች ሀገራት መሳቂያና መሳለቂያ ያደረገን ችግር ሲሆን፤ ከዚህ የግጭትና የጦርነት አዙሪት በአስቸኳይ ካልወጣን እንደ ሀገር ለመቀጠል የምንችልበት ምንም ማስተማመኛ የለንም።”
“በዚህ ረገድ መንግስት ዋነኛ ኃላፊነት ይኑርበት እንጂ፤ የአማራ ፋኖ ኃይሎች እና የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊትም ጦርነቶችን ለማስቆምና የሚታገሉላቸው ዓላማዎች በሰላማዊ መንገድ እንዲመለሱ ማድረግ የሚቻልባቸውን እድሎች ሁሉ አሟጠው እንዲመለከቱ፤ ለሰላም ለሚደረጉ ሀገራዊም ሆነ ዓለም አቀፋዊ ጥሪዎችና ጥረቶች መሳካትም የድርሻቸውን እንዲወጡ በወከለኝ የባህርዳር ከተማ ህዝብ፣ በመላው ኢትዮጵያውያን እና በራሴ ስም ጥሪ ማቅረብ እፈልጋለሁ።”
ኢትዮጵያ ኢንሳይደር