
የዛሬ አንድ ወር ተኩል ገደማ በመሠረት ሚድያ አማካኝነት ከፍተኛ ምዝበራ እየተፈፀመበት እንደሆነ ተጋልጦ የነበረው የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከግማሽ ቢልዮን ብር በላይ ጉድለት እንደተገኘበት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ዛሬ አስታውቋል።
ቋሚ ኮሚቴው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አላግባብ የህዝብና የመንግሥት ሀብት እንዲባክን ማድረጉን ጠቅሶ የሚያከናውናቸው ፕሮጀክቶች ወደ ትግበራ ከመግባታቸው በፊት የቅድመ አዋጭነት ጥናት ግምገማ ተደርጎላቸው እንዲከናወኑ አልተደረገም ብለዋል።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የሺመቤት ደምሴ እንደተናገሩት በመንግሥት በጀትና በዓለም አቀፍ ድጋፍና ብድር የሚከናወኑ ፕሮጀክቶች የትግበራ ቅደም ተከተል ተሰጥቷቸው ለምክረ ሀሳብ ለሚመለከታቸው አካለት አለማቅረቡ ተገቢነት የሌለው መሆኑንም ገልፀዋል።
ለትራንስፖርት ኪራይ፣ ለዳታ ማዕከል ግንባታ፣ ለሳይንስ ካፌና ለሰራተኛ ደሞዝ ያለአግባብ የወጣውን ወጪ ኦዲት በማድረግ በ15 ቀናት ውስጥ ለቋሚ ኮሚቴው ሪፖርት እንዲያደርግ አሳስበዋል።
በተጨማሪም ለተገኘበት ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ የበጀት ጉድለት የአሰራር ሂደቶችን በማረምና ለጉድለቱ መንስኤ የሆኑ ግለሰቦችን የህግ ተጠያቂ በማድረግ ለምክር ቤቱ እንዲያሳውቅ ቋሚ ኮሚቴው ማሳሰቡን ኢፕድ ዘግቧል።
የፌዴራል ዋና ኦዲተር ወይዘሮ መሰረት ደምጤ በበኩላቸው ተቋሙ የተገኘበትን የኦዲት ግኝት ማስተካከያ ለማድረግ ዝግጁነት የለውም ብለዋል፣ ተጀምሮ ላልተጠናቀቀ ፕሮጀክት ገንዘብ ወጪ ተደርጓል ብለዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ተቋሙ የሚሰራቸው ሥራዎች ዘርፈ ብዙ በመሆናቸው በአንዳንድ ዘርፎች የኦዲት ጉድለት መከሰቱን ተናግረዋል። ችግሮቹን ለመፍታት የድርጊት መርሐግብር በማዘጋጀት የተወሰዱ እርምጃዎችን ለቋሚ ኮሚቴው እናቀርባለን ብለዋል።
መሠረት ሚድያ ከሳምንታት በፊት በሰራው የምርመራ ዘገባው በኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ስር በግል አማካሪነት በአመት 120 ሺህ ዶላር የሚከፈለው ግለሰብ እንዳለ እንዲሁም ለአነስተኛ ስራዎች በሚልዮን የሚቆጠር ገንዘብ ለግለሰቦች እና ለድርጅቶች ሲከፋፈል እንደነበር አጋልጦ ነበር።
በተለይ የአለም ባንክ የዛሬ አራት አመት 200 ሚልዮን ዶላር መድቦለት ስራ በጀመረው የዲጂታል ፋውንዴሽን ውስጥ በአማካሪነት ተቀጥረው እየሰሩ ከሚገኙት መሀል ዶ/ር ስሜነው ቀስስ ሲሆኑ የትምህርት መስካቸው የእንስሳት ህክምና ቢሆንም በዚህ የዲጂታል ዘርፍ በአማካሪነት ተቀጥረው በወር 130,000 ብር በአማካሪነት እንደሚከፈላቸው ለመሠረት ሚድያ የደረሰው መረጃ ያሳያል።
በሌላ በኩል አቶ ሰለሞን ካሳ፣ ወይም ኢቢኤስ ቴሌቭዥን ላይ ‘ቴክ ቶክ’ በሚል ስያሜው የሚታወቀው ግለሰብ በተመሳሳይ በማማከር ቅጥር በአመት 120,000 የአሜሪካ ዶላር መቀጠሩ አነጋጋሪ እንደሆነባቸው ጉዳዩን የሚያውቁ ምንጮች ለመሠረት ሚድያ በወቅቱ ተናግረዋል፣ ሰለሞን በአመት በርካታ ወራትን በአሜሪካ የሚያሳልፍ መሆኑ ጉዳዩን ይበልጥ አስገራሚ እንደሚያደርገው ይገልፃሉ።
ይህ ብቻ ሳይሆን የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር “Internet Exchange Point” በተባለ ፕሮግራም የኢንተርኔት ፍሰት በሀገር ውስጥ የዳታ ማእከል እንዲያልፍ የሚያደርገው ፕሮጀክት በጀት ተይዞ የነበረ ቢሆንም ስራውን ይዞ የነበረው ተቋም ከቢሮው እንዲለቅ ተደርጎ በሌላ እንዲተካ እንደተደረገ እና ይህም ከገንዘብ ጥቅም ጋር የተያያዘ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ።
“አይቲ ፓርክ” ተብሎ በሚጠራው ማእከል ውስጥ በዶላር እየከፈሉ የተከራዩ በርካታ ተቋማት እንዳሉ የሚታወቅ ሲሆን ይህ ገቢ ግን ወደየት እየገባ እንደሆነም እንደማይታወቅ እነዚህ ምንጮች ያስረዳሉ።
“በሸገር ከተማ ቡራዩ ውስጥ ለሚገኝ አንድ የአዳሪ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ‘የቴክኖሎጂ ክህሎት ስልጠና ለመስጠት’ በሚል ፋሪስ ለተባለ ድርጅት 21 ሚልዮን ብር በዲጂታል ፋውንዴሽን በኩል ተከፍሏል” የሚሉት እነዚሁ ምንጮች ይህም የተከናወነው በጨረታ ስም ሆኖ ሌሎች አቅም ያላቸው ተቋማት ገለል ተደርገው መሆኑን ጠቁመዋል።
የፋሪስ ድርጅት ባለቤት በቅርቡ የቴስላ ‘ሳይበርትራክ’ መኪና ካለቀረጥ ወደ ሀገር በማስገባቱ የሚታወቅ ሲሆን የዚህን መኪና ወደ ኢትዮጵያ መግባት ባለቤቱ አቶ ኤልያስ ይርዳው ማህበራዊ ሚድያ ላይ ለሀገሪቱ ትልቅ “የኢኖቬሽን” እምርታ ብሎ የገለፀበት መንገድ ብዙዎችን አነጋግሮ ነበር።
መረጃን ከመሠረት!