ይነጋል በላቸው
ሕወሓት ካበሰበሳት ትግራይ፣ ሕወሓት ከኢትዮጵያዊነት የክብር ሠገነት አውርዶ ወደጥልቁ የሣጥናኤል መንግሥት ከፈጠፈጣት ትግራይ፣ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን እንዲጠየፍ ከተደረገ ትግራዋይ፣ በስደት አውስትራሊያ ይኖር የነበረ አስመሳይ የሃይማኖት አባት የኦርቶዶክስን መከፋፈል ተጠቅሞ ሃይማኖቱን እንዳሻው ከሚያጨመላለቅበት የተጋሩ ምድር፣ የኢትዮጵያን ባንዲራ ንቀት በተሞላበት ድምፀት “ጨርቅ ነው” ከማለት ጀምሮ በእግሩ እስኪረጋግጣትና ወደእስትራቾነት ከለወጣት ትግራዋይ ይህን ወጣት ማግኘት ለመላ ኢትዮጵያውያን እንደገና የመፈጠር ያህል ነው፡፡
እግዚአብሔር ማዳን ሲፈልግ ዕብሪተኛና ትዕቢተኛ ታላላቆችን ያገማና ማለትም ያበክትና ታናናሾችን ይሾማል፤ ከፍ ከፍም ያደርጋቸዋል፡፡ አሁን ያሉን የሃይማኖት እረኞች ገንዘብን ማምለክና በኃጢኣት መመላለስን ስለወደዱ ፈጣሪ ይህን መሰል ወጣት እንዲነሣና የመርገምት ጨርቃችን እንዲቀደድ በሩን እየከፈተልን ነው፡፡ እናድምጠው፡፡ ሃይማኖትና ፖለቲካ ተጣምረው አገርና ሕዝብ እየፈጁ ባሉበት በአሁኑ ወቅት ይህን መሰል የማኅበረሰብ ድልድይ ማግኘት መታደል ነው፡፡ በዞረብን የድንዛዜ ትብታብ ሳቢያ ብዙዎቻችን አልተረዳነው ይሆናል እንጂ ጠፍተናል፤ ከሞቱት በላይ ካሉት በታች እየተንጠራወዝን መኖር ከጀመርን ድፍን ሰባት ዓመት ሊሆን 12 ቀናት ብቻ ይቀሩናል – (ዛሬ መጋቢት ሚካኤል 2017 መሆኑን ልብ ይሏል ታዲያ)፡፡ እግዚአብሔር ግን ያድነናል፡፡
ለመዳን ደግሞ እርሱ የሚልካቸውን ያልተጠበቁ ታናናሾችን ማድመጥ አለብን፡፡ ጵጵስናና ምንኩስና ገደል በገባበትና ማጭበርበሪያ በሆነበት በዚህ የመጨረሻ ዘመን ከላይ መጠበቅ የዋህነት ነው – ከታች እንጂ፡፡ ሃሳዊ መሲህ በዝቷል፤ አጭበርባሪውና ዋሾው ገኗል፡፡ በልብሰ ተክህኖ የተጀቦነው የአጋንንት ብዛት ለቁጥር ያታክታል፡፡ ፀብና ሁከትን የሚዘራው ውሉደ አጋንንት ቤተ እምነቱንና ቤተ መንግሥቱን ሞልቶት ዕርቅ እንዳይፈጠር የሚደረገው ደባና ተንል ልዩ ነው፡፡
ዕርቅ ብለህ ገና ቃሉን ስትጠራ የሚያስርህና የሚገድልህ መንግሥትና የሚገዝትህ ካህን በሞላባት ሀገር ትንሣኤን ለማብሰር የሚከፈለው መስዋዕትነት ከባድ ነው፡፡ አስብ እስኪ – ይህ ሁሉ ሰው ሠራሽ መቅሰፍት፣ ይህ ሁሉ የአቢይ አህመድ ሤራና ተንኮል የሚያራምደው ዕልቂት ኢትዮጵያ ውስጥ እየወረደ ሀገራዊ ምህላ ወይም ዱኣ እንዲያዝ የጠየቀ አንድ የሃይማኖት አባት አለ? የለም፡፡ ቢጠይቅ ምቾትና ድሎቱ ይቃወሳላ! ቢጠይቅ በየመበለቷ የደቀለውን የልጅ ውሪ በሚዘርፈውና በሚቧግተው ገንዘብ ማሳደግ አይችልማ! ቢጠይቅ ከተንደላቀቀ ኑሮው ይፈናቀላላ! ይሄ ችግራችን ሁሉ ግና ለአንድዬ ቀላል ነውና አጥብቀን እንጸልይ፡፡ ወደርሱ ከተመለስን በአጭር ጊዜ ውስጥ ምሕረቱን ይልክልናል፡፡
መልካም ማዳመጥ፡፡