ከጎንደሩ የፀጥታ ችግር ጋር በተያያዘ 6 የፖለቲካ እና የፀጥታ መዋቅር አመራሮች በቁጥጥር ስር ዋሉ

May 3, 2022

በጎንደር ከተከሰተው የፀጥታ ችግር በተያያዘ ኃላፊነታቸውን አልተወጡም የተባሉ ስድስት የፖለቲካና የፀጥታ መዋቅር አመራሮች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን የአማራ ክልል ሰላም እና ሕዝብ ደኅንነት ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው በየደረጃው ከሕዝቡ፣ ከፖለቲካ አመራሩ እና ከፀጥታ መዋቅሩ ጋር ውይይት እና ግምገማ ከተካሔደ በኋላ የማስተካከያ እና የእርምት እርምጃ እንደሚወስድም ገልጿል።

ሰሞኑን በጎንደር ከተማ ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ ተቀስቅሶ የነበረውን የፀጥታ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት መንግሥት ከኅብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት ወደ ሥራ መግባቱን የክልሉ መንግሥት አስታውቋል።

በጎንደር ከስድስት ክፍለ ከተሞች የተወጣጡ ወጣቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና ጥሪ የተደረገላቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ተከስቶ በነበረው የፀጥታ ችግር ዙሪያ ተወያይተዋል።

በውይይቱ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ሰላም እና ሕዝብ ደኅንነት ቢሮ ኃላፊ ደሳለኝ ጣሰው የክርስትና እና የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች በመፈቃቀር እና በአንድነት ላይ የተመሠረተ አብሮ የመኖር ባህል ያዳበሩ፣ ጠላትን በጋራ ሲመክቱ የቆዩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በሁለቱ እምነት ተከታዮች መካከል ለዘመናት ተፋቅሮ፣ ተከባብሮ እና ተቻችሎ የመኖር እሴት ለማጠልሸት በውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት የታገዘ የፀጥታ ችግር እንዲነሣ መደረጉን ተናግረዋል።

በችግሩ ምንጭ ዙሪያ፣ ችግሩ በተፈጠረ ጊዜ የሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት በነበራቸው ሚና ዙሪያ መምክሩ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ያለመ መሆኑን ቢሮ ኃላፊው ገልጸዋል።

እስካሁን ኃላፊነታቸውን አልተወጡም የተባሉ 6 የፓለቲካ እና የፀጥታ መዋቅር አመራሮች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው እየታየ መሆኑንም አመልክተዋል።

በየደረጃው ከሕዝቡ፣ ከፖለቲካ አመራሩ እና ከፀጥታ መዋቅሩ ጋር ውይይት እና ግምገማ ከተካሔደ በኋላ የማስተካከያ እና የእርምት እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል።

ነዋሪዎቹ በውይይቱ ላይ የውጭ ኃይሎች ጣልቃ-ገብነት የተስተዋለ፣ የፀጥታ መዋቅሩ ሥራዎች መላላት፣ የቀበሌ መታወቂያ አሰጣጥ ሥርዓት ክፍተት መኖሩ፣ የኅብረተሰቡ ተሳትፎ አደረጃጀት አለመጠናከር፣ የጦር የመሣሪያ አያያዝ ሥርዓት ችግሮች መኖሩ፣ አወዛጋቢ የቤተ-እምነት ቦታዎች ይዞታ ላይ አፋጣኝ ውሳኔ አለመሰጠቱ ዋና ዋና ችግሮች መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ከውይይቱ ተሳታፊዎች ግጭቱ ጠላቶቻችን ከተማችንን ለማጥፋት የሸረቡት ሴራ ነው፤ ስለዚህ ሕዝቡ አንድነቱን እና የቆየ አብሮነቱን ሊፈታተኑ ከሚችሉ ጠላቶቹ ራሱን ሊጠብቅ ይገባል ብለዋል።

“ጎንደርን ስናፈርስ ኢትዮጵያን እናፈርሳለን” ብለው እየተንቀሳቀሱ ያሉ ኃይሎች በሃይማኖት ሽፋን አንድነታችንን ለማፍረስ እየተንቀሳቀሱ ናቸው ያሉት ነዋሪዎቹ እነዚህን አፍራሽ ኃይሎች በተጠናከረ የደኅንነት ሥራ እና በሕዝብ ተሳትፎ ማጋለጥ እና ለሕግ ማቅረብ ይገባል ብለዋል።

ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ የሚንቀሳቀሱ አፍራሽ ተልዕኮ ያላቸውን አካላትን በሕዝብ ተሳትፎ ማጋለጥ እና ለሕግ ማቅረብ እንደሚገባም ነዋሪዎቹ አሳስበዋል።

የጎንደር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዘውዱ ማለደ በበኩላቸው በሁለቱ ሃይማኖቶች ሽፋን የተከሰተውን የፀጥታ ችግር ለመፍታት የሃይማኖት አባቶች፣ ወጣቶች እና አመራሩ ችግሩን ለመፍታት ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል።

የመተሳሰብ፣ አንድነት እና ተከባብሮ የመኖር እሴታችንን በመጠበቅ በከተማችን የተጀመረውን ልማት መደገፍ ይገባናል ሲሉም ከንቲባው ማሳሰባቸውን የአማራ ክልል መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን መረጃ አመላክቷል።

ዋልታ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Previous Story

ኢትዮጵያን የሚወክለው ማነዉ?

Next Story

ጠቅላይ ሚኒስትሩን ያናደደ የፓትርያርኩ ንግግር ይፋ ሆነ! ሀብታሙ አያሌው አቡነ ማትያስ @Ahaz tube አኃዝ

Go toTop