“ዲሲን ለቀው መሄዳቸው ለእኛ ኢትዮጵያውያን ትልቅ ድል ነው”
– በዲሲ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን
(በዲሲ አላሙዲንን ለመቃወም በከተማው ሲዘዋወር የነበረው መኪና ይህን ይመስል ነበር)
(ዜና ትንታኔ) ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን የተሰባሰቡበትን ፌዴሬሽን ለሁለት ለመክፈል ተንቀሳቅሷል የሚባለው የወያኔ/ኢሕአዴግ ሥርዓት በአላሙዲ ስፖንሰርነት የሰሜን አሜሪካውን አመታዊ የስፖርት ፌስቲቫል ለመክፈል ቢጥርም ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ነባሩን ፌዴሬሽን በማመከተል አሸናፊ መሆናቸው ባለፉት ሁለት ዓመታት በዳላስ እና በዋሽንግተን ዲሲ ታይቷል።
በሼህ መሃመድ አላሙዲ የሚደገፈውና የወያኔ ፌዴሬሽን እየተባለ የሚጠቀሰው aesaone ራሱን ተለጣፊ አድርጎ ሌሎች ኢትዮጵያውያን ዓመታዊ ዝግጅታቸውን በሚያደርጉበት ሳምንት ላለፉት 2 ዓመታት ሲያደርግ ባዶ ስታዲየም ከመታቀፍ ውጭ የሕዝብን ቀልብ ሊያገኝ እንዳልቻለ በግልጽ የታየ ጉዳይ ነው። እንደ ዋሽንግተን ፖስት ያሉ ሚዲያዎች ሳይቀሩ 2 ሚሊዮን ዶላር የወጣበት ዝግጅት የተገኘው ሰው ቁጥር ያስገርማል እስከማለት ዘግበው ነበር። ኢትዮጵያውያኑ ይህንን የአላሙዲ እግር ኳስ ቦይኮት በማድረጋቸው በስታዲየሙ ከሚገኘው ሰው ይልቅ ከውጭ ሆኖ የሚቃወመው ሰው ይበልጥ እንደነበር በተደጋጋሚ በሚዲያዎች መዘገቡም አይዘነጋም።
በሼህ አላሙዲ የሚደገፈው ፌዴሬሽን ለ3 ተከታታይ ዓመታት በዋሽንግተን ዲሲ የኳስ ውድድሩን እንደሚያደርግ ቀድሞ የገለጸ ቢሆንም፤ በተለይ አምና በዲሲ በተደረገው ዝግጅት ኢትዮጵያዊያኑ የአላሙዲ አፍ በደም ተጨማልቆ የሚያሳይ ፎቶ በትልቅ መኪና ተሰቅሎ በከተማዋ ሲንቀሳቀስ፤ አላሙዲ ባረፉበት ሆቴል አጠገብ ቆሞ ሲውል፤ ሆቴላቸው ውስጥ ሳይቀር ሕዝቡ አላሙዲንን እየተቃወመ የኳስ ውድድራቸውን “በደማችን ጨዋታ ይብቃ” በሚል ስያሜ በመስጠት ከተቃወማቸው በኋላ አላሙዲ ያልጠበቁት ጉዳይ ስለሆነ ወዲያውኑ ውድድሩን አቋርጠው ወደ መጡበት አፍረው እንደተመለሱ በወቅቱ በተለያዩ ሚዲያዎች ተዘግቧል።
አሜሪካ ያለን ኢትዮጵያውያን በገንዘብ አንገዛም፤ እኛ የደም ገንዘብ አንበላም፤ ከደም ገንዘብ ጋርም አንተባበርም በሚል ይህን የስፖርት ፌስቲቫል ቦይኮት ካደረጉ በኋላ የአላሙዲው ፌዴሬሽን ኳሱን ለ3 ዓመት ከከፈለበት የዋሽንግተን ዲሲው RFK ስታዲየም በመቀየር ወደ ሚኒሶታ እንደተዟዟረ የዘ-ሐበሻ ታማኝ ምንጮች አስታውቀዋል።
ከውስጥ አዋቂዎች መረጃ እንደተረዳነው አላሙዲ እንዲህ ያለ ተቃውሞ ይደርስብኛል ብለው ሳያስቡ በዋሽንግተን ዲሲ አፍረው ተመልሰዋል፤ ይህን ተከትሎም ዋናውን የኢትዮጵያውያን ፌዴሬሽኑ ገንጥለው የወጡትን አመራሮች ይኸው የአላሙዲ ፌዴሬሽን ያባረረ ሲሆን በዲሲ ላለፉት 2 ዓመት የታየውን ባዶ ስታዲየምና ተቃውሞ በሚኒሶታ አያጋጥመንም በሚል ኳሱ ዘንድሮ በሚኒሶታ ይደረጋል። በዚህም መሠረት ከጁን 29 እስከ ጁላይ 5 በሚኒሶታ ይህ ቶርናመንት እንደሚካሄድ ለማረጋገጥ ተችሏል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በዲሲ የአላሙዲንን ኳስ ቦይኮት በማድረግ “ላለፉት 2 ዓመታት ያስተባበሩ ወገኖች ይህ ለኢትዮጵያውያን ትልቅ ድል ነው፤ የኛን ቦይኮት ፈርተው መፈርጠጣቸው ያስደስታል፤ በሚኒሶታም ተመሳሳይ ቦይኮት እንደሚገጥማቸው እንተማመናለን” በሚል በሶሻል ሚዲያዎች እየገለጹ ነው። እንደነዚህ አስተያየት ሰጪዎች “ለ3 ዓመት ኮንትራት ፈርመው በ2 ዓመታቸው ለቀው መውጣታቸው የኢትዮጵያውያን የትግል ውጤት ነው።”