“ ክብር ሰው ለሆኑ መሪዎቻችን ! “
እንኳን ለ126 የአደዋ ድል በዓል አደረሰን
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ
የግራዝማች ዮሴፍ ምሁራዊ ጀግንነት ወደ አደዋ ጦርነት እና ድል ከወሰዱን ገፊ ምክንያቶች አንዱ ና ዋንኛው ነው ብዬ አምናለሁ ። ግለሰቡ ሆን ብለው አመቺ ጊዜን በመጠቀም ” የ17 ኛው አንቀፅ ይሰረዝ ። ይቅር ። ” ብሏል የኢጣሊያ ተወካዩ አንቶሊኒ ኮንቴ ብለው በሐሰት ባያሥተረጉሙ ኗሮ የዛሬው የአደዋ ድል በእንዲህ ዓይነት መልኩ አይከሰትም ነበር ። ክብር ለጀግናው ምሁር ለግራዝማች ዮሴፍ ይሁንልን ። እያልኩ ከአፈወርቅ ገብረኢየሱስ መፀሐፍ ይኽንን እውነት የሚገልፅ ፅሑፍ በዚህ በታሪካዊ የጥቁር ህዝብ ሁሉ የድል ቀን ” እንሆ በረከት !” እላችኋለሁ ።
” የኢጣሊያ መንግስት መልክተኛ ኮንቴ ሳልምቤኒ …( ለተለመደ የጊዜ መግዢያ ዲፕሎማሲ ) እንጦጦ በሀምሌ ወር ወደ አገር ቤት መጣ ፡ አጤ ምኒልክ በክብር አሳምረው ተቀበሉት ፡፡ ከዚህ ወዲያ የውጫሌ ውል እንደገና ተነሳ ፡፡ አጤ ምኒልክ ” ኢትዮጵያ እራሷን ቀጥ ለበጥ አድርጋ ችላ ፤ በመንግስቷ አዝዛ ትኖራለች እንጂ ፡፤ በማንም በማን መንግስት ጥግ ትኖር ዘንድ ፤ ከዛሬ በፊትም በታሪክ አልተገኘ ፡፡ ” አሉ ፡፡ “ደግሞም ኢትዮጵያ በኢጣሊያን ጥግ ትኖራለች የሚል ቃል ታማርኛው ጽሕፈት አይገኝበትም ፡፡ አሁንም ፍቅራችን እንዳይበላሽ ባስራሰባተኛው ክፍል ያ ለውን ውላችን እናንተ አጥፍታችኋልና ወዲያ ተው ፡፡ እኔ ያጠፋሁት ነገር የለኝም ፡፡ በ17ኛው ክፍል ያለው ውላችን ፤ እትዮጵያ በኢጣሊያ ጥግ ትኖራለች ፡፡ የሚል ነገር እንኳን በውኔ በህልሜ አላሰብሁት ፡፡ ” ብለው ተናገሩ ፡፡ ወድያውም ለአውሮፓ ነገሥታት ሁሉ ፤ “ኢትጵያ ራሷን ችላ ትኖራለች ፤ እንጂ በኢጣሊያ ጥግ ልትኖር ምንም ውል አላደረግሁ አውቁልኝ ፡፡ “ብለው ላኩ ፡፡ የጀርመን ንጉሥ ለኢጣልያ የመርዳት ነገር ላከ ፡፡ እንግሊዝም ደግሞ ክፉም በጎም ሳይናገር መካከለኛ ቃል መለሰ ፡፡ ነገሩ ለኢጣሊያ ለማድላት ነበረ ፡፡ መስኮብና ፈረንሳይ ለኢጣሊያ ጠላት ነበሩና ለአበሻ የረዱ መስለው ላኩ ፡፡ መስኮብስ እስቲ ፈረንሳይ ግን ምንም ላበሻ ሰው ነገሩ ባይገበው በኢጣሊያ መቅናት ና ለሌላ ብልሃት ነበረ ፡፡
የኢጣሊያ መንግስት በአስራሰባተኛው ክፍል የነበረው ቃል እንደተመኘው ሳይሆን ሊቀርበት በሆነ ግዜ ተናደደና ኮንት አንቶኔሊን እንጦጦ ሄደህ የዚህን ነገር አንተ እንደጀመርህ ተነጋግረህ ብልሃቱን አስታውቀን ብሎ ላከው ፡፡ …ገስግሶ እንጦጦ ደረሰ ፡፡…አጤ ምኒልክ ግን አንድ ግዜ በተናገሩት ቃል ፤ ” ኢትዮጵያ ምንም ቢሆን በሌላ መንግስት ጥግ አትኖርም ፡፡ በፍቅር እንኑር ትሉ እንደሆነ የዚህን ነገር ልቀቁ ። መልቀቃችሁንም ለድፍን አውሮፓ መንግስታት አስተውቁ ፡፡ ብለው አስጨንቀው ያዙ ፡፡ ኮንት አንቶኔሊ ግን የተዋዋል ነውም ውል ለአመስት ዓመት ብቻ ነው ፡፡ ….ከአምስት ዓመቱ ሁለቱ አለፈ ፡፡…ሦሥቱን ዓመት ይጨርስ አለ ፡፡ አጤ ምኒልክ ግን …” እንኳን ሶስት ዓመት ሶስት ቀንም ቢሆን አየድርም ፡፡ይልቁነስ አሁኑ ቶሎ ነገሩ ይልቅ ፡፡ “ብለው ሰቀዘው ያዙ ፡፡ በዚህ መካከል …(አንባቢ ሆይ ለጥቆ ያለውን የመፅሐፉን ወሬ መጥቀሱ አላሥፈላጊ በመሆኑ ትቼዋለሁ ። ነገርን በሚዛን አይቶ መፃፉ መልካም ነው ።ደሞም የሰው ፍፁም የለውምና ግለሰቦች በታሪክ አጋጣሚ የፈፀሙትን እንከን ከበጎ ሥራቸው አንፃር በማሥተያየተ ይኽንን የመሠለውን አፉ ማለት ተገቢ ነው ። ኋላ በአደዋ ጦርነትም ያደረጉትን ተጋድሎ መዘንጋቱ መልካም ጥቅም አያመጣምና ! መፀሐፉን ግን አንባቢ አንብቦ እንዲረዳ ምንጬን በፅሑፊ መጨረሻ እጠቅሳለሁ ። …)
እናም በራሳችን ወገን እገዛ ፣ የኢጣሊያ ጦር በለሳ ሙና ድረስ ዘለቀ ፡፡…ምኒልክ በዚህ የኢጣሊያን ( ሃይ ባይ የሌለው ወረራ ) በጣም ተናደዱ ፡፡በታላቅ ቁጣም ” ከሰጠኋችሁ አገር ሳትዛነፉ ተቀመጡ ! ..መስፋፋታችሁን አቁሙ ! ” ብለው መልክት ሰደዱ.፡፡ኮንት አንቶኔሊና ኮንቴ ሳልምቤኒ ነገሩን ያላወቁ መስለው” እንጃ! አናውቅም ! ” አሉ ( አሳምረው ያውቁ ነበር ። አጤ ምኒልክ ወደ ኢጣሊያ መልክት መላካቸውንም ሆነ የኢጣሊን ተስፋፊነት ያውቃሉ ፡፡ ሲያብሉ ነበር ። )
…ኮንት አንቶኔሊ ችክአለ ፡፡ እየደጋገመም ውሉ የቀረው 3 ዓመት ነውና ለጥቂት ጊዜያት ብለን አንነታረክ ይቅር ንትርኩ ፡፡ ” ይህንን ይቅርን ትርክ “የሚለውን ሐረግ ብቻ ወስዶ ፤ የኢትዮጵያ አስተርጓሚ ግራዝማች ዮሴፍ ለአጤምኒልክ “አስራሰባተኘው አንቀጽ ይቅር ብሏል ፡፡ “በማለት ሆን ብሎ አስተረጎመ ፡፡ ወረቀቱም ተፃፈ ፡፡ ( እንግዲህ እነሱ እንዳታለሉን እኛም እናታላቸው እንጂ እነዚህ ሰዎች ፣ በማጭበርበር ለሁለተኛ ጊዜ ድል ሊያደርጉን አንፈቅድላቸውም ። በማለት ይመሥላል ግራዝማች ዮሴፍ ብልጣ ብልጡን አንቶሊን በትርጉም የሸወደው ፡፡ ) አንቶኖሊ በሴራ የተሞላው አስራሰባተኛው አንቀጽ ፣ ያልተሰረዘ መስሎት ደስ ብሎት ወጣና ፤ ለማረጋገጥ ለሌላ አስተርጓሚ ፤ የአማርኛውን ትርጉም ሲያሳይ ከውሉ ውስጥ 17ኛውን አንቀፅ መውጣቱን ተረዳና እሳት ለብሶ እሳት ጎርሶ ወደ ዐጤ ምኒሊክ እልፍኝ ዘለቀ፡፡ እናም እነዲህ አለ –
” ምነው 17ኘው ክፍል ተሰረዘ ። ይቅር ተብሎ ተጣፈ ? በማለት በንዴት ጠየቀ ፡፡ ጃንሆይም ” ሁለታችን… ተነጋግረን አንተም ወደህ የተጣፈ ቃል ነው ፡፡ ሌላ አልታከለበት ስለምን ነው መጠየቅህ ? ጠጠት አደረብህን ? ” አሉት ፡፡ አንቶኔሊም ” እኔ ለጊዜው አይነሳ ይቅር ፡፡ አልሁኝ ፡፡ እንጂ ለጭራሹ ይሰረዝ አላልሁኝም አለ ፡፡ ጃንሆይም ” ካንተ ቃል ያገኘሁትን አልለወጥሁም ፣ ባስተርጓሚ የተናገር ይኀው ቃል …እነደተጻፈው ነው ፡፡ ” አሉት ፡፡ ኮንት አንቶኔሊ ወደ አስተርጓሚው ዞሮ ፤ “ይህንን ሁሉ የምታዘናኩር ፣ ቀጣፊ አንተ ነህ !ብሎ አስተርጓሚውን ግራዝማች ዮሴፍን ተሳደበ ፡፡ እዚህ ላይ የእቴጌ ጣይቱ በሳል እና እጅግ የመጠቀ ዲፕሎማሲያዊ የጨዋነት መልስ ና ኋላ አንቶኔሊ በንዴት የድፍረት ማሥፈራርቾ ሲናገር የሰጡትን ምላሽ ከመፀሐፉ መጥቀሱ ተገቢ ነው ።
” አስተረጓሚያችን ቢያጠፋ እንኳን የምንቀጠው እኛ ሆነን ሳለ ፤ በስድነት እኛ ፊት መስደብ አልነበረብህም ፡፡ ከጅምሩ ያጭበረበራችሁት እናንተ ናቸሁ ፡፡ በአማርኛው የውጫሌ ውልም ላይ ኢትዮጵያ በጣሊያን ውስጥ ታድራለች የሚል የለም ፡፡ … ” አሉት ፡፡ እናም አንቶኒሊ ነገሩ ሁሉ እንዳልሆነለት አይቶ ፤ በንዴት ብው አለና ፣ ያን የታተመውን ደብዳቤ ብጭቅጭቅ አድርጎ ቀዳዶ ፊታቸው ጣለና ፣ ” እንግዴህ ፍቅራችን ፈረሰ ! ” በማለት የጦርነቱን ነገር ገልጦ ሲናገር እቴጌ ጣይቱ ከትክ ብለው ስቀው ፤ ” የዛሬሳምነት አድርገው ፡፡ በዚህ የሚደነግጥልህ የለም ፡፡ ሒድ ! ሒድ ! የፎከረክበትን አድርግ ፡፡ እናም የመጣውን እናነሣዋለን ! እግሩን ለጠጠር ! ደረቱን ለጦር ! ሰጥቶ አገሩን የማያድን ሰው ከዚህ ያለ አይምሰለህ ! የገዛ ደሙን ገብሮ ! ለገዛ አገሩ መሞት ጌጥ ነው እንጂ ፤ ሞት አይባልም ፡፡ አሁንም ሂድ ! አይምሽብህ ፡፡ የፎከርክበትን በፈቀደህ ጊዜ አድርገው ፡፡ እኛም ከዚሁ እንቆይሃለን ፡፡ ”
( አንባቢ ሆይ ፤ ይህ የታሪክ እውነት በአፈወርቅ ገብረኢየሱስ ከተጻፈው ” ዳግማዊ አጤ ምኒልክ ከተሰኘ መጽሓፍ ከገጽ 72 እስከ 79 የተወሰደነው ፡፡ በተወሰነ ደረጃ አሳጥሬዋለሁ )