አጋቹ

ያምናው ጆሮ ጠቢ
የታቻምናው ሰላይ
ሲደረግ የበላይ
ሁሉንም አግቶ
ወህኒ አድርጎታል አገሩን ለሕዝቡ፤
ከእርሱ በቀር የለም
ወደዚህ ወደዚያ የሚል እንደልቡ።
ብስክሌት ቢነዳ፣
እግር ኳስ ቢጫወት፣
ሩጫ ቢወዳደር ፣
የልጅነት ሕልሙን
ሲቀጭ ቢተዳደር፤
መውጣትና መግባት፣
መታየት መሽቀርቀር
የተፈቀደለት
የለም ከርሱ በቀር።
በጠገበ ድመት
እንደተያዘች አይጥ ሁለት ዓይኑ ጠፍቶ
መጫወቻ ሁኗል ሰው ሁሉ ታግቶ።
የሰባ አመት ጓይላ
በሸገር
በሀገር
ምንድነው ይህ ዘፈን?
ሰባት አመት ሙሉ ጆሯችን የሰማው
ቁርቁዝና ቃሉ ብልጽግና ዜማው
ጠረፍ አገር ወድቆ ርስቱን የተቀማው
ቁርጥ ቤት ሲጋፋ ደላላው አሳማው
አመቱ ሲመለስ ኡደቱን ተጎዞ
ካምናውም የባሰ እልቂት ፍጅት ይዞ
የዘር ግጭት ጽፈው
በጎራ አሰልፈው
ካፈጃጁት ወጣት በእድል የተረፈው
ኦሮሞና ትግሬ አፋሩ አማራው
እየተሰደደ እግሩ ወዳመራው
ሸገር ደሞ ማማው
ሴትኛ አዳሪኛ
ላይ ላዩን ተቀብቶ በርቶበት ከተማው
በቻይና ፌካ ፌክ ሲታይ አሸብርቆ
መንገዱ በውሃ
ምሽቱ በብርሃን ሳለ ተጥለቅልቆ
በየጓዳው ግና
ጨለማ ውስጥ ያለው ሕፃን አፉ ደርቆ
ሴፍቲኔት ሰልፈኛው
በልቡ ተራግሞ በአፉ ግን መርቆ
የበሻሻው አጭቤ
መያዣ የሌለው የተሙለጨለጨ
እንደ ሴት አዳሪ እያብለጨለጨ
ብቻውን ሲበላ እያቁለጨለጨ
አከራይ ተከራይ
በጠኔ ሲበራይ
ጉዳይ ያለው ሁሉ በጉቦ ታግቶ
በዘረፋ እንጂ
መኖር ብርቅ ሲሆን በላብ በወዝ ሠርቶ
እንደሰው አይተነው ሲሆን እንዳራዊት
ቁንጫና ትኋን የተባይ ሠራዊት
የጨፈሩበትን ያኔ በበሻሻ
ቂም በቀል ሲወጣ ዛሬ በሀበሻ
ሰባት አመት ብቻ አይመስልም ዘመኑ
በጭንቅ በጣር በጋር ተጎትቶ ቀኑ
ሰባ አመት አርጅቷል አካልም ልቡና
ስብርብር/ብር ብለን በሰበሩ ዜና
የት አግኝተን ሰላም የት አግኝተን ጤና
የዘመን ታማሚ የዘመን ታካሚው
አላፊ አግዳሚው
ገጹ ተጨራምቶ
ተርቦ ተጠምቶ
ወዙ ሙጥጥ ብሎ ጠፍቶ የበፊቱ
አቧራ ነፍቶበት አመድ መስሎ ፊቱ
ታቻምና ተቅሞ ዘንድሮ ሲገረብ
ርስቱ እስከነነፍሱ ተሽጦ ለአረብ
ሞተ እንዳይባል አለ በቁመና
አለ እንዳይባል ተስፋው ሆኗል መና
በቀቢጸ ተስፋ
ኑሮን እየገፋ
አይመጣብኝም ሲል ከዛሬ የከፋ
በነጋው ሰማዩ ላዩ ላይ ሲደፋ
ታግቶ ሲጠፋ መኪና ሙሉ ሰው
ጉድጓድ ሙሉ አስከሬን ሲቀብሩ አልቅሰው
ከመድረክ ፊት ለፊት
ትኩረት ማዘናጊያው ጩኸት ነክቶ ጣራ
መድረክ በስተጀርባ
ለባዕዳን ተሽጦ የሀገር አንጡራ
ገልታ ገልታ ሚለው
በመከራው ጓይላ
ሞተ እንዳይባል አለ አልሞተም ገና
አለም እንዳይባል
አይለማም አይሰማም ነፍስያው በድና
እንዲህ ነው ሚመስለው
ሰባቱን ሰባ አመት ስናጠቃልለው።