File Photo
BBN News – በአዲስ አበባ የሚገኙ ነጋዴዎች አዲስ የግብር ተመን ሊወጣብን ነው የሚል ስጋት እንዳላቸው ተጠቆመ፡፡በኢትዮጵያ ገቢዎች እና ጉምሩክ ባለሥልጣን የአዲስ አበባ ታክስና ፕሮግራም ሥራዎች መስሪያ ቤት ያሰማራቸው ሰራተኞች በየንግድ መደብሩ በመዞር አዲስ የቀን ገቢ የዋጋ ተመን እያወጡ እንደሚገኙ ታውቋል፡፡ መስሪያ ቤቱ ያሰማራቸው ሰራተኞች ተመን እያወጡ የሚገኙት በነጋዴዎች ላይ ግብር ለመጨመር አለመሆኑን ቢገልጹም፣ ተዓማኒነት ማግኘት አልቻሉም፡፡ በዚህ የተነሳም የአዲስ አበባ ነጋዴዎች ስጋት እንደገባቸው ለመረዳት ተችሏል፡፡
ከዚህ ቀደም መንግስት በየንግድ መደብሩ ሰራተኞችን አሰማርቶ የግብር ተመን መሰብሰቡን የሚያስታውሱት ነጋዴዎቹ፣ በወቅቱም ተመኑ የሚሰራው ግብር ለመጨመር አለመሆኑ ተገልጾላቸው እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ሆኖም በወቅቱ የተደረገውን የቀን ገቢ የግብር ትመና መሰረት በማድረግ መንግስት በነጋዴዎች ላይ አዲስ የግብር ጭማሪ አድርጎ እንደነበር አስተያየት ሰጨዎቹ ተናግረዋል፡፡ ከዚህ አንጻር አሁን በየንግድ ማዕከሉ እየተካሔደ ያለው የቀን ገቢ ግምት አዲስ የግብር መክፈያ ተመን ለማውጣት እንደሆነ ስጋት የገባቸው ነጋዴዎች ስጋታቸውን በመግለጽ ላይ ናቸው፡፡
ስጋት የገባቸው ነጋዴዎች እንደገለጹት ከሆነ፣ ከዚህ ቀደም ማለትም በ2003 ተመሳሳይ የቀን ገቢ ግምት ተሰርቶ የነበረ ሲሆን፣ በኋላ ላይም በነጋዴው ማኅበረሰብ ላይ ከፍተኛ የግብር ጫና ተቆልሎ ነበር፡፡ የአሁኑ እንቅስቃሴም የዚያ አካል መሆኑን የሚገልጹት ነጋዴዎቹ፣ በተለይ ደግሞ ከ2003 ወዲህ የቀን ገቢ ግምት አለመሰራቱ፣ መንግስት በነጋዴው ላይ ጫን ያለ ግብር ለመጣል እንዳነሳሰው ይገልጻሉ፡፡ ከሚያዝያ 17 ቀን 2009 ጀምሮ ሰፋ ያለ የቀን ገቢን የማስተመን ዘመቻ እየተካሔደ እንደሚገኝ የተገኘው መረጃ አመልክቷል፡፡
ሌላው አስገራሚው ነገር ደግሞ፣ የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ የሚጠቀሙ ነጋዴዎች ጭምር የቀን ገቢ ግምት እንዲሰራባቸው መታዘዙ ነው፡፡ የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ ያላቸው ነጋዴዎች ለደንበኞቻቸው የሚሸጡት ማንኛውም ዕቃ ገቢ በሚቆርጡት ደረሰኝ ሊታወቅ ቢችልም፣ ነገር ግን የቀን ገቢ ትመናው እነሱን ጭምር ያካተተ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ ይህም በርካታ ነጋዴዎችን ግራ እንዳጋባ ተነግሯል፡፡ የመመዝገቢያ ማሽን እንዳላቸው በመግለጽ የቀን ገቢያቸውን ለማስተመን ፈቃደኛ ያልሆኑ ነጋዴዎች፣ በፌደራል ፖሊሶች ጣልቃ ገብነት ጭምር የቀን ገቢያቸውን እንዲናገሩ መደረጉን የዓይን እማኞች ለቢቢኤን ጠቁመዋል፡፡ በገንዘብ እጥረት ከፍተኛ ስቃይ ላይ የሚገኘው የህወሓት መንግስት፣ በአዲስ አበባ ነጋዴዎች ላይ ከፍ ያለ ግብር ለመጣል እየተሰናዳ እንደሚገኝ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡