በሰለሞን ኃይለማርያም (ዶ/ር)
መግቢያ
የዚህ ጽሑፍ ዓላማ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል በኢትዮጵያ አጠቃላይ ዕድገት ላይ ምን ያህል በጐ ያልሆነ ተጽዕኖ እንዳሳደረና ይህም በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ፤ ፖለቲካና ማኅበራዊ እንደዚሁም የሕዝቡ የዕለት ተዕለት ኑሮ እየተሻሻለ ከመምጣት ይልቅ እየደቀቀ እየማቀቀና እየኮሰሰ እንዲሄድ ማድረጉን በማመላከት የፖለቲካ ባህላችንን ለማረቅ፤ ለማስተካከል፤ ብሎም ለመቀየር ምን ማድረግ እንደምንችል ለመወያየትነው፡፡ በተጨማሪም የፖለቲካ ባህል ለሰላም ወይንም ለግጭት ዋና መንስኤ በመሆኑ የፖለቲካ ባህላችንን ማረቅና ማስተካከል ጊዜ የሚሰጠው አይደለም፡፡ላለፉት 10 ዓመታት በተለይም ደግሞ ከለውጡ በኋላ በኢትዮጵያ ልሂቃን መካከል ለኢትዮጵያ የፖለቲካ ቀውስ ከዋና ዋናዎች ምክንያቶች መካከል የኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል አንዱ እየተደረገ ሲነሳ ይስተዋላል፡፡ ለመሆኑ የፖለቲካ ባህል ምንድነው? የፖለቲካ ባህልን መቀየር ይቻላል? ከተቻለስ በምን ፍጥነት? ሌሎች የዓለም ሀገራት የተሳሳተ ያሉትን የፖለቲካ ባህል እንዴት ነው የቀየሩት? በመቀየራቸውስ ምን አገኙ? በማለት የመወያያ ሃሳበ ለማቅረብ ነው፡፡
የፖለቲካ ባህል ምንድን ነው ?
የፖለቲካ ባህል በፖለቲካ ሳይንስ ውስጥ የቆየ ፅንሰ ሃሳብ ነው፡፡ ጥንታዊ ፈላስፎች እነሞንተስኬ ፤ ፕሌቶ፤ ሶቅራጦስ ፤ አርስቶትልና ሌሎችም ስለፖለቲካ ባህል የራሳቸውን ሃሳብ አስቀምጠዋል፡፡ ይሁንና የፖለቲካ ባህልን በፖለቲካ ሳይንስ ውስጥ በስፋት ጥናትና ምርምር ማድረግ የተጀመረው እ.ኤ.አ በ1963 አሜሪካዊ የፖለቲካ ሳይንስ ሊቆች አልመንድ እና ቬርባ በእንግሊዝ፤ በአሜሪካ፤ በጣሊያን፤ በምዕራብ ጀርመንና በሜክሲኮ የፖለቲካ ባህል ላይ ጥናት በማድረግ በተለይም ዲሞክራሲ ላይ በማተኮር ዳጐስ ያለ መጽሐፍ ካሳተሙ በኋላ ነው፡፡
የፖለቲካ ባህል ማኅበረሰቡ በሀገሪቱ ስላለው የፖለቲካ ሥርዓት የሚጋራው አስተሳሰብ፤ ምልከታ፤ ጠቅላላ ዕይታ ነው፡፡ የፖለቲካ ባህል አንድ ማኅበረሰብ የፖለቲካ ሥርዓቱ እንዲህ ነው፤ እንደዛ ነው በማለት የሚሰጠው ብያኔ ነው፡፡ ለምሳሌ ሉሲያን ፓይ የተባለው የአሜሪካ ፖለቲካ ባህል ተመራማሪ የፖለቲካ ባህል የአንድ ማህበረሰብ መሠረታዊ እምነት፤ ስሜትና ልማድ እንዲሁም ዕውቀት የተጣመረበት በአንድ ሀገር ያለው የፖለቲካ ሂደት መደላድል ነው በማለት ፖለቲካ ባህልን ይተረጉማል በመጨመርም የፖለቲካ ባህል ዜጐች በሀገራቸው ስላለው የፖለቲካ ሥርዓት ያላቸው እምነት ፤ ልማድ ፤ አስተሳሰብና ስሜት ነው በማለት ያጠቃልላል፡
የፖለቲካ ባህል በሁለት አልፎ አልፎም በሦስት ይከፈላል፡ የአጠቃላይ የማህበረሰቡ የፖለቲካ ባህል ፤ የልሒቃን የፖለቲካ ባህል እንዲሁም የተቋማት የፖለቲካ ባህል በማለት መክፈል ይቻላል፡፡ በዚህ ጽሑፍ የሚነሱ ጉዳዮች ባጠቃላይ ወይንም ባብዛኛው የልሒቃን የፖለቲካ ባህል ናቸው፡፡ ይህንን በአጽንኦት አንባብቢያን ልብ እንዲሉልኝ እሻለሁ፡፡ በልሒቃን የፖለቲካ ባህልና ባጠቃላይ የህዝቡ የፖለቲካ ባህል መካከል የሰፋ ልዩነት እንዳለ መገንዘብ ያሻል፡፡
የፖለቲካ ባህልም ሆነ በአጠቃላይ ባህል የምንለው በጊዜ ሂደት የተሠራና እየዳበረ የሚሄድ ነው፡፡ ባህል ስንፈጠር አብሮን የተወለደ አይደለም፡፡ በታሪክ በፖለቲካ ክስተቶች፤ በሀገሪቱ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ እውነቶችና ሁነቶች ላይ ተመሥርቶ የፖለቲካ ባህል ይሠራል፡፡ ማንኛውም ባህል ሰው ሰራሽ ነው፡፡ ተፈጥሮአዊ የሚባል ባህል የለም፡፡ በርግጥ የፖለቲካ ባህልን ለመፍጠር፤ በኅብረተሰቡ ውስጥ ለማስረጽና የፖለቲካ ባህል ሆኖ እንዲወጣ ጊዜ ይፈልጋል፡፡ ነገር ግን አዲስ የፖለቲካ ባህል መፍጠር የማይቻል ነገር አይደለም፡፡ በቻይና ፤ በህንድ አዲስ የፖለቲካ ባህል መፍጠር እንደሚቻል ታይቷል፡፡ በአሜሪካና ካናዳም በተመረጡ ጉዳዮች የተፈጠሩ የፖለቲካ ባህሎች አሉ፡፡ በጥልቀት ሲታይ በኒውዚላንድ፤ አውስትሪሊያ ፣ በጃፓን፤ አሜሪካና ካናዳ አዳዲስ የፖለቲካ ባህሎች ተፈጥረዋል፡፡ ሲንጋፑር በዕድገት ማማ የወጣችው በአዲስ የፖለቲካ ባህል ነው፡፡
በሀገራችንም ቢሆን ነጋድራስ ገብረሕይወት ባይከዳኝ “መንግስትና የሕዝብ አስተዳደር ” በሚለው መጽሐፋቸው ቀጣይነት ያለው የመንግስት አስተዳደር መጥፋት ለኢትዮጵያ ኋላቀርነት መንስኤ ነው የሚል ሃሳብ ሲያንጸባርቁ ስለፖለቲካ ባህላችን መናገራቸው ነበር፡፡ የቀደሙ ምሁራኖቻችንና አስተዋይ ኢትዮጵያዊያን ለኢትዮጵያ መጐሳቆል የማያባራ የእርስ በርስ ጦርነት፤ መቆሚያ ላጣው ግጭትና እልቂት የኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል መሆኑን በገደምዳሚው ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል ለሀገራችን ሕዝቦች ነቀርሳ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ነገር ግን ይህ ነቀርሳ የማይነቀል የማይታወቅ፤ ፈጽሞ የማይቻል አይደለም፡፡ ችግሩ ከታወቀ መፍትሔው የማይቻል አይደለምና፡፡
በዌስተርን ኬፕ ዩኒቨርሲቲ ድረ ገጽ ላይ Amhara, Oromo, and Tigray political cultures and challenges of political stability in Ethiopia: 1991–2017 በሚል ርዕስ በዚህ ዓመትበታተመው የጥናት ጽሑፍ መሠረት የኢትዮጵያ ልሒቃን የፖለቲካ ባህል ተብለው ከሚለዩት መካከል ባለፈ ታሪክ አለመግባባት ፤ እርስ በርስ መወነጃጀል፤ ኃላፊነት አለመወሰድ ፤ ሁሉንም ችግር የሌላው አድርጐ ማቅረብ ፤ የመንግስት ሥልጣን ለማግኘት ሕግን መጣስ፤ የመንግስት ሀብት ዝርፊያ ፤ የአስተዳደር በደል፤ የተሳሳተ ፖሊሲ ላይ ድርቅ ማለት፤ ከፋፍለህ ግዛ የፖለቲካ መሣሪያን መጠቀም፤ ገዥ ልሂቃን የመንግስትና የሕዝብ ሀብትን እንደግል ንብረት መጠቀም፤ ስም ማጥፋት ፤ የፖለቲካ ሥልጣን ተቀናቃኝን እንደጠላት ማጥቃት፤ የመደራደርና የሰጥቶ መቀበል ባህል አለመኖር፤ የፖለቲካ ሥልጣን ለማግኘት ወይንም በፖለቲካ ሥልጣን ለመቆየት የኃይል አማራጭን መጠቀም፤ በፖለቲካ ጉይዳ የእርስ በርስ ጦርነት ቢነሳ፤ አንዱ ጎሳ፤ በሌላው ላይ ቢነሳ ያበጠው ይፈንዳ ማለት፡፡ ሥልጣን ለመያዝ አንዱን ዘውጌ በሌላው ዘውጌ ላይ ማነሳሳት፤ አንዱን ሀይማኖት በሌላው ላይ ማስነሳት ፤ ዜሮ ሰም ጊም ወይንም ሁሉንም ለብቻዬ በማለት ሌላውን ማግለል ፤ የኔ ለኔ የናንተ ለኛ በሚል የፖለቲካ ቀመር መንቀሳቀስ ናቸው፡፡ በዚህ ጽሑፍ የምናየው ስም ማጥፋትን ፤ ተቀናቃኝን ማጥቃትንና የመደራደርና የሰጥቶ መቀበል ባህል አለመኖርን ይሆናል፡፡
ፊታውራሪ ተክለሀዋርያት ተክለማርያም የሕይወት ታሪካቸውን ባሰፈሩበት መጽሐፍ፤ በቅርቡ እንኳ ታደለች ኃ/ሚካኤል “ዳኛው ማነው?” በሚለው መጽሐፏ ፤ ዶ/ር መላኩ ተገኝ “ ከሰንጋ ተራ እስከ አምስተርዳም”፤ “ዶ/ር አማረ ተግባሩ” “ኃይሌ ፊዳ እና የግሌ ትዝታ” በሚለው ፤ ቡልቻ ደመቅሳ ደግሞ “My life My Vision for the Oromo and Other Peoples of Ethiopia” በሚለው የእንግሊዝኛ መጽሐፋቸው፤ ሕይወት ተፈራ” ማማ በሰማይ ” እና ሌሎችም ብዙ መጽሐፎች አስከፊ የፖለቲካ ባህላችን ዋጋ እንዳስከፈለንና መቀየር እንዳለበት በቀጥታ ባይሆን በተዘዋዋሪ አስገንዝበዋል፡፡ በሕይወት ተፈራ መጽሐፍ ላይ የደራሲዋ ዋና ጀግና የሆነው ጌታቸው ማሩ ከፓርቲው የተለየ ሃሳብ በመያዙ ብቻ መገደሉ፤ ኃይሌ ፊዳ የገበሬ ልጅ ሆኖ ሳለ የፊውዳል ልጅ ነው እየተባለ ከፍተኛ የስም ማጥፋት እንደደረሰበት ዶ/ር አማረ ያብራራሉ፡፡ እንዲህ ያሉ ፖለቲካዊ ግድያዎችና ስም ማጥፋቶች በኢትዮጵያ ታሪክ ተዘርዝረው አያልቁም፡፡ ይህንን የሀገራችን የዕድገት መሰናክል የሆነ የፖለቲካ ባህላችንን ነቅለን ካላስወገድነው እንዴት ከረሃብ ፤ ከልመና ፤ ከድህነትና ከኋላቀርነት ልንገላገል እንችላለን ? ብሩህ፤ ብርቱና በሳል የፖለቲካ መሪዎችን ስም እያጠፋን እየገደልንና ባጭሩ እየቀጨን ምን ዓይነት የፖለቲካ መሪ ልንፈጥር ነው? ከላይ አንደተገለጸው የፖለቲካ ባህል ሰፊና ውስብስብ ነው፡፡ ወደ ሰፊውና ውስብስቡ ገብቼ ቀልጬ ሳልቀር ወደተነሳሁበት አንድ ፍሬ ወደ ሆነው ለዛሬ ወደማቀርበው የፖለቲካ ባህላችን ላይ ላተኩር፡፡
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል ስር የሰደደና የቆየ ቢሆንም ከቅርቡ ተነስተን ወደፊትም ወደኋላም እያልን እናያለን፡ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል ስንልም እጅግ ሰፊና ፈርጀ ብዙ በመሆኑ የየትኛው ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ ባህል የሚል ጥያቄም የሚያስነሳ በመሆኑ በማዕከላዊ መንግስት የፖለቲካ ባህል እሱም ቢሆን የልሂቃን የፖለቲካ ባህል ላይ አተኩረን አንኳር አንኳሩን ለማየት አንሞክራለን፡፡ ከነዚህ አንኳር ጉዳዮችም መካከል ሥልጣን ይዞ ለመቆየትና ወደ ሥልጣን ለመምጣት በሚደረገው ትግል ላይ እንዴት መቻቻል የጐደለው አርቆ አስተዋይነት የሌለበት ስለሀገሪቱ፤ ስለሕዝቡ ሰላም የዕለት ተዕለት ኑሮና ዕድገት ላይ ደንታ የለሽ ትንቅንቅ እንደሚደረግ ይህም ያስከተለው ጥፋት እልቂትና መከራን ለማየት፤ ለመዳሰስና ለመወያየት እንሞክራለን፡፡
ስም ማጥፋትና የማጥቃት የልሒቃን የፖለቲካ ባህል
በኢትዮጵያ የልሒቃን የፖለቲካ ባህል ወደ ፖለቲካ ሥልጣን ለመምጣት ወይንም ደግሞ ሥልጣንን ይዞ ለመቆየት እንደመሳሪያ ከሚጠቀሙባቸው ብዙ ነገሮች መካከል የፖለቲካ ባላንጣን ፤ የፖለቲካ ተቀናቃኝን ስም ማጥፋት አንዱ ነው፡፡ አንደኛውን ከሰው ፍጡር አሳንሶ ማሳየት ፤ አውሬ ማድረግ፤ ማጥላላትና ይውደም “ ቀይሽብር ይፋፋምበት “ ፤”ፀረ“ እንደዚህ ነው ማለት “ውጉዝ ከመአሪዎስ” ማለትና እሱ እንደዚህ ነው አሸባሪ ወዘተ በማለትና አሉታዊ ፍረጃ በመስጠት ከጨዋታው ውጭ እንዲሆን ማድረግ ይባስ ብሎም መግደል ፤ ማስወገድ፤ እንዳይሞት እንዳይሽር ማድረግ የተለመዱ ናቸው፡፡ ታዲያ ይህንን የልሒቃን የፖለቲካ ባህል በሕግ ለመከላከል አለመቻል፤ ሕግ ወይንም የፍትህ ተቋማት ነፃ፤ ገለልተኛና በከፍተኛ የሞራል ልዕልና መመራት አለመቻላቸው ትልቁ ስብራት ሆኖ ቆይቷል፡ ልሒቃን ወደ ፖለቲካ ለመምጣት ወይንም በፖለቲካ ሥልጣን ለመቆየት የማያደርጉት ነገር የለም፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ በሕጋዊ መንገድ የሥልጣን የሸግግር በርግጥ ተደርጐ አያውቅም በማለት የሚከራከሩ ሰዎች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ሕጋዊነት ራሱን ችሎ ሌላ ውይይት የሚያስፈልገው በመሆኑ አሁን ወደተነሳሁበት ስም ማጥፋት ልመለስ፡፡
ልጅ እያሱ ሕጋዊ የምኒልክ ወራሽ ሆነው ሳለ ልጅነታቸው ፤ ምክር አልሰማ ማለታቸው ፤ ለፖለቲካ ባላንጣዎቻቸው አጋልጦ ሰጥቷቸው ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ የሚሆን የማይሆን ስም በመስጠት ከሥልጣናቸው እንዲሰናበቱ ይህም አልበቃ ብሎአቸው ጨርሰው እንዲጠፋ አድርገዋቸዋል፡፡ የሳቸው ከሥልጣን መነሳት ብቻ ሳይሆን በዚህ ሳቢያ ጦርነት ተደርጐ የሰው ሕይወት ጠፍቷል፡፡ የሀገር ንብረት ወድሟል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን በኃይል ሥልጣንን መንጠቅ ወደ ሥልጣን መፈናጠጥ እንደሚቻል ቀጣይ በሆነ ሁኔታ ስር እንዲሰድ ሌላ የፖለቲካ ባህል ችካል ሆኗል፡፡ ይህ የቅርብ ታሪካችን ሕጋዊ መሪን ቦታ ለመውሰድ የፖለቲካ ተቃናቃኞች ስም በማጥፋት፤ ሰውን ስም በማጠልሸትና በማንቋሸሽ የፖለቲካ ድጋፍ በማሰባሰብ ሥልጣንን ባቋራጭ የማግኘት የፖለቲካ ባህል እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንደተቻለ አመላካች ነው፡፡ በተጨማሪም ይህንን ሕጋዊ ያልሆነ አካሄድ የሚከላከል፤ በሥርዓት የሚዳኝ የሚጠብቅ ይህ ነው የሚባል ነፃ፤ ገለልተኛ ፤ የተጠናከረ ዘላቂ የሆነ መንግስታዊም ሆነ ማህበረሰባዊ ተቋም በኢትዮጵያ የሌለ መሆኑ ይህ የግጭት አዙሪት የሆነ የልሂቃን የፖለቲካ ባህል ያለከልካይ እንዲቀጥል ዕድሉ ተከፍቶለት ቆይቷል፡፡ ወደ ፖለቲካ ሥልጣን ለመምጣት ወይንም የፖለቲካ ሥልጣን ይዞ ለመቆየት በሚደረገው ትግል ላይ የሚደረጉ ስም ማጥፋት ባብዛኛው በሀሰት፤ በውሸት ላይ ተመርኩዘው የሚደረጉ ናቸው፡፡
ተፈሪ ወደ ሥልጣን መንበር ለመምጣት እየተደላደሉ ባሉበት ወቅት አሁንም ቦታው ይገባኛል በማለት ክርክሩ ቀጥሎ ነበር፡፡ ልጅ እያሱ ተሽረው ወይዘሮ ዘውዲቱ ንግሰተ ነገስታት ሲባሉ ባለቤታቸውም ጉግሳ ወሌ ወደ ንግስናው ይጠጋሉ የሚል ግምት ነበር፡፡ ይሁንና ጉግሳ አዲስ አበባ ሲመጡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ባህል እንደገና በይፋ ተከሰተ፡፡ ንግስቲቱ ያላሉትን “እግዚአብሔር እኔን ሴቲቱ መርጦ በዚህ ክብርና ዙፋን ካበቃኝ ለብቻዬ እንጂ ከባል ጋር መኖር የለብኝም” ብለዋል ተብሎ ንግስቲቱ ከራስ ጉግሣ እንዲለያዩ ተሴረ፡፡ ራስ ጉግሣም ወደ አባታቸው ሀገርና ግዘታቸው ወደ ጎንደር ከመመለስ ይልቅ ወደ አማራሳይንት በሹመት ተላኩ፡፡ የሸዋ መኳንንት ሸር ያስቀየማቸው ራስ ጉግሣ ለበቀል መነሳሳታቸው የጊዜ ጉዳይ ነበር፡፡ ተፈሪ ወደ ሥልጣን መንበር ለመምጣት እየተደላደሉ ባሉበት ወቅት ራስ ጉግሣ ወደ አመጹ ገቡ፡፡ በኢትዮጵያ ያሉ የጣሊያን ወኪሎች ፤ በኋላ ሸርተት ቢሉም የትግራይ መሳፍንቶች ፤ የጐጃሙ ራስ ኃይሉ ጭምር የአመጹ ተባባሪ ለመሆን ተዘጋጅተው ነበር፡፡ እዚህ ላይ ቆም ብለን እንድናስብ የሚያስፈልገው ሁልጊዜ ሕግና ሥርዓት ሲጣስ፤ አመፅ ሲነሳ የውጭ ጠላቶቻችን ለአመፁ ገንዘብና መሳሪያ ለማቀበል ዝግጁ መሆናቸውንና የሀገራችን የፖለቲካ ባላንጣዎችም ስለሀገሪቷ ስለሕዝቡ፤ ስለውጭ ጠላቶቻችን የተደበቀ ሴራ ደንታ ሳይኖራቸው መተባበራቸው፤ መሣሪያውንም ገንዘቡንም መቀበላቸው ነው፡፡
የሆኖ ሆኖ ራስ ጉግሣ ወሌ (አባ ደልድል) ልክ ተፈሪና የተፈሪ ደጋፊዎች በእያሱ ላይ እንዳደረጉት ሁሉ በተፈሪ ላይ ከአመፃቸው በፊት የስም ማጥፋት ዘመቻ ጀመሩ፡፡ “ራስ ተፈሪ የካቶሊክን ሃይማኖት በፈረንሳይ ሀገር ተቀብሏል፡፡ በዚህ የተነሳ የጥንቱ የጠዋቱ የሆነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ለማፍረስ እየሠራ ነው፤ ራስ ተፈሪ አህያና ውሻ እያሳረደ ግብር ያበላል፡፡ እንደውም አጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ አህያና ውሻ እያረደ እንዲበላ አዋጅ እየተዘጋጀ ነው” በሚል የስም ማጥፋታቸውን አጧጧፉት ራስ ጉግሣ ወሎ የወጠኑት አመፃ በወሎ ደላንታ አንቺም በሚባል ቦታ ላይ በተፈሪ የታዘዙትን ራስ ሙሌጌታን መቋቋም ባለመቻላቸው ተሸነፉ፡፡ ይህንን ታሪክ እዚህ ላይ ማንሳቴ ስም ማጥፋት የፖለቲካ ባህላችን ሆኖ መሰንበቱን ለማሳየት ነው፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ይበልጥ ለማወቅ አምባሳደር ዘውዴ “ተፈሪ መኰንን ረዥሙ የሥልጣን ጉዞ” በሚል ያሳተሙት መጽሐፍ ማንበብ ይጠቅማል፡፡
ይህ ስም ማጥፋት ፋሺስት ጣሊያን ኢትዮጵያን ባጠቃበት ወቅት ኃይለሥላሴ ወደ እንግሊዝ ስደት ባቀኑበት ወቅት፤ ሲመለሱ እንደዚሁም ደርግ ከሥልጣን ሲያወርዳቸው ተጠናክሮ የቀጠለ የልሂቃን የፖለቲካ ባህል ሆኖ ቆይቷል፡፡
ደርግም በኃይለሥላሴ ላይ የሆነውን ያልሆነውን እየለጠፈ ሥርዓቱን ደብዛው እንዲጠፋ ካደረገ በኋላ እሱም በተራው በፖለቲካ ባህላችን የተለመደውን የስም ማጥፋት ማዝነብ ጀመረ፡፡ የደርግ ተቃዋሚዎችም ደርግን በቀላሉ አልለቀቁትም፡፡ “ሀይማኖት የለሽ” “መሀይም” “ያ ሰው በላ” እና የመሳሰሉትን በደርግ ላይ በመለጠፍ የሚችሉትን ሁሉ አድርገዋል፡፡ ህወሀት ጫካ እያለ ደርግን “ያ ሰው በላ” ሥርዓት በማለት የቻለውን ያህል ሲያወግዝ ደርግ በበኩሉ “ገንጣይ አስገንጣይ” “ የእናት ጡት ነካሽ” በማለት በሰፊው የፕሮፓጋንዳ ሥራ ሲሰራ ቆይቷል፡፡ ህወሀት/ ኢሕአዴግ ሥልጣን ይዞ የፖለቲካ ባላንጣዎቹ እየፈረጠሙና እየተጠናከሩ በሂዱበት በ1997ቱ ምርጫ የቅንጀት ደጋፊዎች ሰላማዊ ሰልፍ በሚያደርጉበት ወቅት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በጠራራ ፀሐይ በተገደሉበት ጊዜ ህወሀት/ ኢሕአዴግ ካድሬዎች አይናቸውን በጨው ታጥበው “የተገድሉት ወጣቶች ባንክ ሊዘርፉ ሲሉ ነው” በማለት የተለመደ የልሂቃን የፖለቲካ ባህል ተጠናክሮ እንዲቀጥል አድርገዋል፡፡ ተቃዋሚ የሆኑትን ሁሉ “አሸባሪ” በማለት ከሷል፡፡ ስም ማጥፋት ወይንም ፕሮፓጋንዳ አለቅጥ ሲጋነንና አላማውን ሲስት በጀርመን በሁለተኛው የዓለም ጦርነት አይሁዳዊያን ላይ በመጨረሻም በራሳቸው በጀርመኖች ምን እንዳስከተለ ሁላችንም የምናውቀው ነው፡፡ በሀገራችንም በቅርቡ ለረጅም ጊዜ በተነሳው ስም ማጥፋት በመጨረሻ የተዘጋጀለትን ሕወሀትን ስቶ ወይም አትርፎ ሕዝቡን ሊጐዳ ችሏል፡፡ አሁንም በዘመናችን የጀርመን አክራሪዎች ስደተኞች መጤዎች፤ የኛን የአኗኗር ባህርይ የማይቀበሉ ተጠራርገው ከሀገር ይውጡ በማለት ማሴራቸው እንደተደረሰበት ጀርመን ከሁለተኛው የአለም ጦርነት ተምረው ነፃ ፤ ገለልተኛ ፤ በሐቅና በፍትህ ላይ ብቻ ተመሥርተው ያቋቋማቸው ተቋማት ጀርመን ገና በእንጭጩ የአክራሪዎችን ሴራ በመበጣጠስ በትክክለኛው የዕድገት ግስጋሴ እንድትቀጥል ሆናለች፡፡
በሀገራችን ያለው የልሂቃን የፖለቲካ ባህል ካለፈው ስህተት ፤ ካለፈው ውድቀት ተምሮ እንደጀርመን ነፃ፤ ገለልተኛ፤ በሐቅና በፍትህ ላይ ብቻ የተመሠረተ ጠንካራ ተቋም ለመመሥረት ባለመቻሉ የፖለቲካ ሥልጣን ለማግኘት በሚፈልጉና የፖለቲካውን ሥልጣን ይዘው ለማቆየት በሚታገሉ የፖለቲካ ልሂቃን መካከል የሚደረገው ትግል አቅጣጫውን ሲስትና መጠፋፋት፤ ጥሎ ማለፍ፤ ውጉዝ ከመአርዮስ ፤ በለው፤ ግደለው፤ ፀረ-እንትን ፀረ-እንትን ሲባል ሀይ የሚል፤ በሕግ አግባብ፤ በሥርዓት ፤ በወግና በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት ባለው መልኩ አደብ የሚያስገዛ ሁኔታ ሊጠፋ ችሏል፡፡
ይሁንና በቅርቡ በምርጫ ቦርድ፤ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን፤ የሀገር መከላከያ የታየው ለውጥ ይበል የሚባልና ሊበረታታ የሚገባው ተግባር ነው፡፡ ይህም ዕውቅና ሊሰጠውና ሊቀጥል የሚገባ አርአያነት ያለው አቅጣጫ ነው፡፡
ላለመደራደርና ላለመወያየት ምክንያት ከየት መጣ ?
ከፍተኛ የስም ማጥፋት በሚካሄድበት ወቅት ስሙ በሀሰት ወይንም በከፍተኛ ማጋነን ተዋረድኩ፤ ተሰደብኩ፤ ክብሬ ተነካ የሚለው መንግስትም ሆነ የተቃዋሚ አካል ከስም አጥፊው ጋር ላመነጋገር፤ አይን ለአይን ላለመተያየት፤ ላለመደራደርና ላለመወያየት ምክንያት ያገኛል፡፡ በዚህ ሳንካ የተነሳ በውይይትና በመነጋገር የሀሪቱን የጋራ ችግሮች ለመፍታት ከመጣር ይልቅ ቂም መቋጠር፤ ጊዜ ጠብቆ ለማጥቃት ለመበቀልና ሌላ አዙሪት ግጭት ለመፍጠር መመስጠርና መሸመቅ ይጀመራል፡፡ ይህ አዙሪት ለረጅም ዘመን የቀጠለ አሁንም ያለና አንድ ቦታ ካልተሰበረና ካልቆመ እስካሁን ያለውን ማብቂያና ማለቂያ የሌለው የግጭት አዙሪት በፍጥነት እያሽከረከረ በመጨረሻ ወደ መበታተንና ወደ መፍረስ ይወስደናል፡፡ ይህም ባይሆን ሀገራችን እንዳታድግ፤ ባለችበት እንዳትቀጥል ሁሌ ወደኋላ የድህነት ምሳሌና አረንቋ እንድትሆን የሚያደርገን የፖለቲካ ባህል ነው፡፡
የፖለቲካ ችግሮችን በመወያየት፤ በመነጋገር ፤ ሰጥቶ በመቀበልና በመነጋገር መፍታት ካልተቻለ ማህበረሰቡ ዕድሜ ልኩን ለፍቶ ያፈራውን በስንት መከራ በብድርና በልመና የተገኘውን ሀብት በማቃጠል፤ በማውደም በመበተን ዕድገትና ልማት፤ ሰላምና መረጋጋት ማምጣት አይቻልም፡፡ የውይይት ባህልን በፅኑ መሠረት ላይ መትከል ካልቻልን በፍቅር ወልደን ተንከባክበን ያሳደግናቸውን ከአብራካችን የወጡ ብርቅ ልጆቻችንን ለጦርነትና ለግጭት መዳረጋችን አይቀርም፡፡ ልጆቻችን በግጭት፤ በጦርነት ሲያልቁ ወደሌላ ግጭትና ጦርነት መግቢያ ምክንያት ተፈጠረ ማለት ነው፡፡ የግጭት አዙሪት ማለት ይኸው ነው፡፡
በመወያየት፤ በመነጋገር ፤ በመደራደር፤ ሰጥቶ በመቀበል፤ ከኔ ይቅር ከኔ ይቅር፤ በመባባል አለም እንደሚያደርገው የሠለጠኑ ሀገሮች እንደሚጠቀሙበት በመወያየት የፖለቲካ ችግሮቻችንን መፍታት ካልቻልን፡፡ እኔ ያልኩት ብቻ መሆን አለበት ካልን፤ ከአቋማችን ትንሽ አንኳ ለመንቀሳቀስ ፈቃደኛ ካልሆነ ሁሉን ነገር በኃይል፤ በጉልበት፤ በንዴት፤ በጥላቻ፤ በቂም፤ በክፋትና በእኔ እበልጥ፤ እኔ እበልጥ ካልን ዘለቄታ ያለው ሰላም፤ ዘላቄታ የለው ልማት ማምጣት ስለማይቻል በውጤቱ ወጣቶች የሥራ ዕድል ስለማይኖራቸው ፤ ስራ ቢያገኙም የሚረባ ደሞዝ አግኝተው የተሻለ ሕይወት መኖር ስለማይችሉ በዚህም የተነሳ ስደት፤ ሥራ አጥነትና ወደ አልባሌ ሱስ መግባት፤ ባጠቃላይ ማህበራዊ ቀውስ ይፈጠራል፡፡
ፕሮፌሰር ሀረገወይን የተባሉ ተወዳጅ የሀገራችን ሊቅ “ጠመንጃ አንስቶ ወደ ጫካ ገብቶ እየዘረፈ መብላት ቀላልና የሰነፍ ስራ ነው ፡፡ እንደ አንድ ገበሬ ጠዋት ተነስቶ አርሶ፤ ጐልጉሎ ፤ አርሞና ኮትኩቶ የዘራውን አጭዶ ፤ ከምሮ የገበሬ ኑሮ መኖር እውነተኛው ጀግንነትና የሚያኮራ ሕይወት” መሆኑን አሳይተዋል፡፡ ይህንን አስተሳሰብ በጥልቀት በመመልከትና በማስረፅ የ”ገዳይ እወዳለሁ ፤ የዘራፍ”፤ ወዘተ ኋላቀር የፖለቲካ ባህላችንን ማለዘብ ቀስበቀስም የኋላቀርነታችን፤ ምክንያት መሆኑ በማወቅ የሚገድልን ሳይሆን የሚሠራን፤ የሚያድንን፤ የማድነቅ፤ የማሞካሸት የፖለቲካ ባህል መፍጠር አለብን፡፡
የሰው ስም ማጥፋት፤ ማጠልሸት ምንም ሙያ የማይጠይቅ የሰነፍ ሥራነው፡፡ በሕይወታቸው ይህ ነው የማይባል ሥራ ያልሠሩ ዋና ተግባራቸው የሚሠራን ሰው መሳደብ ነው፡፡ የሚሠራውን የሚደክመውን ፤ የሚተጋውን የኋላ ታሪክ በመምዘዝ የአሁን መልካም ተግባርን ለማንኳሰስ፤ ለማጥላላት ይጥራሉ፡፡ አዲስ ሃሳብ ማመንጨት፤ የሚሠራን ሰው ማበረታታት ፤ የተሻለ መነገድ ማሳየት ቅንነትን፤ ማስተዋልንና ማሰብን ይጠይቃል፡፡ በሀገራችን ያለው የአብዛኛው የልሒቃን የፖለቲካ ባህል መልካም ሃሳብ ከማመንጨት፤ የተሻለ መነገድ ከማመላከት ይልቅ ማንቋሸሽ፤ ማበሻቀጥና ማጥላላትን የሚመርጥ ይመስላል፡፡ እዚህ ላይ አንባቢያን ልብ እንዲሉ የምሻው ትክክለኛ ያልሆነና አቅጣጫውን የሳተ ሃሳብና ተግባርን መተቸትና እንዲታረም ሃሳብ በማቅረብና በስድብና በማንቋሸሽ መካከል ትልቅ ልዩነት መኖሩን ነው፡፡ በቅን ልቦና ተነሳስቶ “ይህ አቅጣጫ፤ተግባር ትክክል አይደለም” በማለትና በመተቸትና ፤ በክፋትና ተንኮል ተነሳስቶ “ይህ አቅጣጫ፤ ይህ ተግባር ቆሻሻ ነው፤ ይህንን አቅጣጫ ያስቀመጠው ድሮ እንዲህ ነበር” በማለት መካከል የሰፋ ልዩነት አለ፡፡ አንደኛው ተግባሩ ሃሳቡ እንዲሻሻል ሃሳቡና ተግባሩ ላይ ሲያተኩር ሁለተኛው ሃሳቡ እንዲጠፋ፤ ተግባሩ እንዲነቀል እንዲደመሰስ የሚተጋ ነው፡፡ ሁለተኛው ከሃሳቡና ተግባሩም አልፎ ሃሳቡ ያቀረበው ላይ ያነጣጥራል፡፡ እንግዲህ ለሀገራችን ያልበጀው ወደፊትም የማይበጀው የልሒቃን የፖለቲካ ባህል ሁለተኛው ነው፡፡ በተንኰል ፤ በክፋት፤ በግል ጥቅምና ፍላጎት ተነሳስቶ መልካም ለመሥራት የተነሳውን ሰው ስም ማጥፋትና ተግባሩ እንዲኮላሽ የማድረግ ጥረት ሀገራችንን ለዘለዓለም በድህነት፤ በረሃብ፤ በድንቁርናና በኋላቀርነት እንድትታወቅ ያደረገ የፖለቲካ ባህላችን ነው፡፡ እንዲህ ያለው የልሒቃን የፖለቲካ ባህል በሕግ ካልተከለከለ፤ በትምህርት ካልተገራ ስለዕድገትና ልማት ማውራት የማይቻል ነው፡፡ የልሒቃን የአጭር ጊዜ የግል ፍላጐት ከማህበረሰቡ የረጅም ጊዜ ዘለቄታዊ ፍላጐት ጋር ሲጋጭ በአንድ ሀገር ውስጥ ውድቀት፤ ቀውስ ያስከትላል፡፡
በግድያና በስም ማጥፋት የፖለቲካ ሥልጣንን መመኘት ሀገራችን ወደመቀመቅ ያወረደና የደሀ ደሀ ለማኝ ያደረገን የፖለቲካ ባህላ ችንን ነቅለን ሌላው ዓለም የደረሰበት የኢኮኖሚ ዕድገት፤ የልማትና የሰላም የጥበብ እርካብ ላይ ለመድረስ የሚረዳ የተሻለ አዲስ የፖለቲካ ባህል መገንባት ይቻላል፡፡ የግድ በማዋረድ ፤ በመሳደብ በሴራና በመጠፋፋት ሥልጣን ካልያዝኩ ብሎ ሙጥኝ የሚባልበት ምንም ዓይነት አመክንዮ የለም፡፡
በክፍል ሁለት ሌሎች የዓለም ሀገራት የተሳሳተ ያሉትን የፖለቲካ ባህል እንዴት ቀየሩ? በመቀየራቸውስ ምን አገኙ? በማለት የጃፓንና የቺሊን የፖለቲካ ባህል እናያለን ?
ዶ/ር ሰለሞን ኃይለማርያም በዌስተርን ኬፕ ዩኒቨርሲቲ የልሒቃን የፖለቲካ ባህል ላይ ጥናት ያደረገ ሲሆን በዚህ ጽሑፍ ላይ አስተያየት ካላችሁ [email protected] ማግኘት ትችላላችሁ፡፡