ድርጅታችን መኢአድ ለሶስት አስርት አመታትና ከዚያ በላይ በሰላማዊ ትግል ረገድ ትክክለኛ የህዝብ ድምጽ ሆኖ መቆየቱ የታየና እየታየ ያለ እውነታ ነው። ስለሆነም፤ ከሦስት አስርት ዓመታት በፊት ጀምሮ የኢትዮጲያ ችግር የሚፈታው ሁሉን አቀፍ ሃገራዊ ውይይት በማድረግ ነው ብሎ በጽኑ ያምናል። ከማመን ባሻገርም፤ በተግባር አሳይቷል፤ እያሳየም ይገኛል። ስለሆነም ህዝባዊ ምክክር ስለማድረግ በጽኑ አቋም ሲሞግት ነበር እየሞገተም ይገኛል።
ሆኖም፤ የኢትዮጲያን ሰላም በማይፈልጉና ኢትዮጲያዊነትን በማይቀበሉ እንዲሁም በብሄርተኝነትና ዘረኝነት በታወሩ ፖለቲከኞች እየተመራች ከእሩብ ክፍለ ዘመን በላይ ዴሞክራሲ የራቃት እንደነበረች ህዝባችን የሚያውቀው ሃቅ ነው።
ያሁኗ ኢትዮጲያ ደግሞ ዜጎቿን የምታስር፤ የምታፈናቅልና የምትገድል የስቃይ ማምረቻ ሆናለች። ለዚህ ምክኒያቱ ደግሞ፤ በዋናነት ገዥው ፓርቲ ሲሆን፤ በተጨማሪም እድሉን ያላገኙ ቢያገኙ አሁናዊዩን ቀውስ አባብሰው መቀጠልን ግብ አድርገው የተነሱ ዘረኛ ፖለቲከኞች ናቸው።
ለዚህ ትልቁ ማሳያ ሰሞነኛው የኦሮሞ ፌደራሊስት [ኦፌኮ] እና የኦሮሞ ነጻነት ግንባር[ኦነግ] መግለጫ ነው። ኦፌኮና ኦነግ በመግለጫቸው፤ ለአራት ቀናት የቆየና የሃይማኖት አባቶችን፣ አባ ገዳዎችንና በኦሮሞ ህዝብ ጉዳይ የሚመለከታቸውን ሁሉ ያካተተ ስብሰባ ማድረጋቸውን አሳውቀዋል፡፡
በመጨረሻም በኦሮሚያ ክልል የሽግግር መንግስት ሊያቋቁሙ ስምምነት ላይ መድረሳቸውንና ኃላፊነቱም ለኦፌኮና ለኦነግ መሰጠቱን ገልጸዋል። የስምምነታቸው አካል አድርገው ያነሷቸውም፤ ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት መሆናቸውን በአቋም መግለጫቸው አሳውቀውናል። በክልሉ የሽግግር መንግስት ማቋቋም፣ ለዚህም የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊትን እንደ ወታደራዊ አቅም መጠቀም
አዲስ አበባን ወደኦሮሚያ ማጠቃለል፣ መተከል፣ ወሎ፣ ድሬደዋ፣ ሞያሌና ሐረርን የኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ ከሆኑ ክልሎች በወረራ ለመያዝና ለመስፋፋት ማሰባቸውንና በክልሉ ውስጥ የሚደረጉ ሁሉም እንቅስቃሴዎች በገዳና በስንቄ ስርአት ብቻ እንደሚተገበሩ መስማማታቸውን አሳውቀዋል።
መኢአድም እነኝህን ለአንድ ወገን ብቻ የቆሙና ሃገር አፍራሽ ውሳኔዎችን በብዙ አሳማኝና ተጨባጭ ሃገራዊ መመዘኛዎች ይቃወማል፡፡
1ኛ. ሃገራችን ኢትዮጲያ በአራቱም አቅጣጫ ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ባለችበት ወቅት፤ በኦሮሚያ ክልል ብቻ የሽግግር መንግስት ለማቋቋምና ሰላም ለማስፈን መወሰን፤ ፖለቲከኞቹ ለሌሎች ኢትዮጲያዊያን ግድ የማይላቸው ከመሆኑ በስተጀርባ፤ ሀገር ወዳዱን የኦሮሞ ህዝብ ከሌሎች ኢትዮጲያዊያን የመነጠል አንድምታ ያለው በመሆኑ፤ መኢአድ በጽኑ ይቃወማል።
2ኛ. የሁሉም ኢትዮጲያዊያን ከተማ የሆነችውን አዲስ አበባን ጨምሮ መተከል፣ ወሎ፣ ድሬደዋ፤ ሐረርንና ሞያሌን ወደኦሮሚያ ለማጠቃለል መወሰን፤ ግልጽ ወረራ በመሆኑ አጥብቀን እንቃወማለን፡፡
3ኛ. በኮሪደር ልማት ስም ማፈናቀላቸው የዚህ ፕሮጀክት አካል መሆኑን ያመላክታል። ይህ ተግባርም፤ ለከፋ ግጭት የሚጋብዝ ስለሆነ በአስቸኳይ የማስተካከያ እርምት እንዲወሰድ ስንል እንጠይቃለን፡፡
4ኛ. “ሁለት እግር አለኝ ብሎ ሁለት ዛፍ አይወጣም” እንዲሉ በሰላማዊ ትግል የሕዝብን ሀብትና የሀገርን በጀት እየተጠቀሙ በገባው መጠን ለነፃነቱ ነፍጥ ያነሳውን አካልም መጠቀሚያ ለማድረግ መሞከር እስካሁን ላለው ቀውስ እና ከዚህ በኋላም ለሚፈጠረው ችግር የሞራል፣ የስብዕና፤ እንዲሁም የሕግ ተጠያቂ እንደሚያደርግ ማስገንዘብ እንወዳለን፡
5ኛ. ዓለም አቀፍ እና አገር አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች፣ ፓርቲዎች፣ የዲሞክራሲ ተቋማት በተለይም ፓርቲዎችን እንዲያስተዳድር በአዋጅ የተሰጠው ምርጫ ቦርድ በዚህ ቀቢፀ ተስፋ ምኞት ለሚፈጠረው የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ማንኛውንም ተጓዳኝ ችግሮች ከመፈጠራቸው በፊት አጥብቀው እንዲያወግዙ ስንል ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
6ኛ. እነዚህ ግጭት ጠማቂ ፓርቲዎች በሰላማዊ ታጋይ ስም ያሉ ነገር ግን የትጥቅ ትግልን እንደሚያበረታቱ ያሳየ መግለጫ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ በመሆኑም እስካሁን በክልሉ ለተፈፀሙት ብሔርና ኃይማኖት ተኮር ግድያዎች ተጠያቂ ሊሆኑ ይገባል፡፡ ስለሆነም ይሄን በሰላማዊ ታጋይ ስም ከተማ ተቀምጦ እርስ በእርስ የሚያጫርስ የወረራ ድርጊት እንዲተገበር የሚያመቻቹ ተቋማትና ግለሰቦችን አጥብቀን እናወግዛለን፡፡
6ኛ. የአባ ገዳ እና ሀዳ ሲንቄ የኦሮሚያ ሕዝብ ባህል አቃፊ እና አካታችነቱን ወደ ጎን በመተው እኩይ ተግባራቸውን ማስፈፀሚያ ለማድረግ መሞከር በሌላውም ላይ በግድ ለመጫን ማሰብ በክልሉ ውስጥ ነዋሪ የሆኑትን ሌላውን ማህበረሰብ በኃይማኖታቸው፤ በባህላቸው ምክንያት እንዲፈናቀሉ፤ እንዲገደሉ፤ ጦርነት ያወጀ ስለሆነ ሰፊው የኦሮሞ ሕዝብ እንዳይቀበለውና ድርጊቱን በአስቸኳይ እንዲያስቆም እንጠይቃለን፡፡
“አንዲት ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!”
የካቲት 20 ቀን 2017 ዓ.ም.
አዲስ አበባ